Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ሄሎ

ቀን:

በስህተት ብዙም ከማያውቃት አንዲት ሴት ጋር አንሶላ የተጋፈፈው በቅርቡ ነበር፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም ወሲብ ሲፈጽሙ ኮንዶም አልተጠቀሙም ነበር፡፡ ሰለሞን (ስሙ ተቀይሯል) ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ያላስጨነቀው ነገር ምናልባት ልጅቷ ኤችአይቪ ቢኖርባት ብሎ ይረበሽ ጀመር፡፡ የሚያደርገው ጠፍቶት በጭንቀት ተውጦ ሳለ ድንገት አንድ ነገር ትዝ አለውና ስልኩን አነሳ፡፡ የሕክምና ባለሙያ ወደሆኑት ጓደኞቹም ደወለ፡፡ ነገር ግን እንደአጋጣሚ ሆኖ ሁሉም ጥሪውን ሊመልሱለት አልቻሉም፡፡ በአንድ ወቅት ከማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ወዳገኘው ስለጤና መረጃ የሚሰጥ አጭር የስልክ መስመር ደወለ፡፡

ከዚያኛው ጫፍ የነበረችው ባለሙያ ምን ዓይነት ዕርዳታ እንደፈለገ ጠየቀችው፡፡ ያጋጠመውንም ፈራ ተባ እያለ አስረዳት፡፡ ተመሳሳይ ገጠመኞች ሲኖሩ 48 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚወሰደውን መድኃኒት የት ማግኘት እንደሚችልም አከታትሎ ጠየቃት፡፡ እርግጠኛ ባትሆንም ሊኖራቸው ይችላል ብላ የገመተቻቸውን በከተማው የሚገኙ መድኃኒት ቤቶች ጠቆመችው፡፡ መድኃኒቱ ከማዘዣ ውጪ እንደማይሸጥ፣ ስለዚህም የሐኪም ማዘዣ እንደሚያስፈልገው ነግራው ስልኩ ተዘጋ፡፡ እፎይታም ተሰማው፡፡ ለአምስት ደቂቃ ያናገራት ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ክፍያ በደቂቃ ስምንት ብር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አጭር የስልክ ቁጥሮችን በመደወል የሚገኙ አገልግሎቶችን ሲጠቀም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ገንዘብ በቀላሉ መላክና መቀበል የሚያስችለውን የሄሎ ካሽ አካውንት ከፍቷል፡፡

የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ወደ አገሪቱ የገባው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት  ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1894 ከመደበኛ ስልክ በተንቀሳቃሽ (ሞባይል) ስልክ የሚጠቀምበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡

- Advertisement -

የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችም እየተዘጋጁ ተጠቃሚዎች እንዲገለገሉባቸው እየተደረገ ይገኛል፡፡ የሎተሪ ዕጣዎች፣ ዕርዳታዎች እንዲሁም መጠነኛ ገንዘብ አስከፍለው መረጃዎች የሚሰጡ እንደ ሄሎ ዶክተር፣ ሄሎ ገበያ፣ ሄሎ ካሽ፣ አፋላጊ፣ ሄሎ ትዳር ያሉ አገልግሎቶች በስፋት እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በነፃ የሚቀርቡ የኤችአይቪ የምክር አገልግሎት፣ የግብርና መረጃዎች፣ የአደጋ ጊዜ የስልክ ጥሪዎችም አሉ፡፡

እነዚህን የስልክ መስመሮች ምን ያህሎቹ ያውቋቸዋል? ምን ያህሎቹስ በተገቢው መንገድ ይጠቀሙታል የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው፡፡ መስመሮቹን በሚገባ የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ መስመሮቹ ላይ ደውለው የሚቀልዱና ያልተገባ ንግግር የሚያደርጉ አሉ፡፡ ተመሳሳይ አጋጣሚዎች በተለይ በነፃ የስልክ መስመሮች ላይ የሚያጋጥሙ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ በክፍያ በሚሠሩት ላይም ይስተዋላል፡፡

አበባ ዮሴፍ ከአንዱ ውጪ አብዛኛዎቹን የሄሎ አገልግሎቶች በውል አታውቃቸውም፡፡ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘትም ጉግል ማድረግ ትመርጣለች፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት በማይኖርበት ጊዜ በተለይም ቦታዎችንና የድርጅቶችን ስልክ ቁጥር ለማግኘት ከሄሎ አገልግሎቶች አንዱ ወደሆነው አፋላጊ በመደወል የምትፈልጋቸውን መረጃዎች ለማግኘት ትሞክራለች፡፡

‹‹አገልግሎታቸው ፈጣንና ዋጋቸውም ኪስ የማይጐዳ ነው፡፡ ደንበኛን የሚያስተናግዱበት መንገድም ደስ ይላል፤›› የምትለው አበባ፣ በሳምንት በተወሰኑ ቀናት ውስጥ መረጃ ለማግኘት እንደምትደውልላቸው፣ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥም የምትፈልገውን እንደምታገኝ ትናገራለች፡፡

የተለያዩ አገልግሎችን እየሰጡ የሚገኙት የስልክ መስመሮች፣ በደቂቃ የሚያስከፍሉት ክፍያ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በደቂቃ ሁለት ወይም ሦስት ብር የሚያስከፍሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ስምንት ብር ድረስ ያስከፍላሉ፡፡ በደቂቃ ስምንት ብር የሚያስከፍሉት ምንም እንኳን የሚሰጡት መረጃ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ዋጋቸው ውድ ነው፣ ለብዙኃኑም ተደራሽ አይደሉም ሲሉ አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡

ወ/ሮ ሕይወት (ስማቸው ተቀይሯል) ይባላሉ፡፡ በቅርቡ የአፍንጫ አለርጂ ተከስቶባቸው ነበር፡፡ ትኩስ ነገሮችን ጠጥተው እንደሚሻላቸው በማመን ሞክረውታል፡፡ ነገር ግን በቀላሉ ሊድኑ አልቻሉም፡፡ የተሻለ አማራጭ ፍለጋም የጤና መረጃዎችን ወደሚሰጠው ሄሎ ዶክተር ደውለው ነበር፡፡ ህመሙ ያሳደረባቸውን ስሜት ጠይቀዋቸው ስሙን በትክክል የማያስታውሱትን አንድ መድኃኒትም አዘዙላቸው፡፡ አገልግሎቱን ሲገልጹም ‹‹የሰጡኝ መረጃ ትክክል ነው፡፡ በአካባቢያችን በሚገኝ የሕክምና መስጫ ታይቼ የተሰጠኝ እነሱ የነገሩኝ መድኃኒት ነው፡፡ ነገር ግን ያወራሁትን ደቂቃ ባላስታውሰውም 50 ብር ጨርሻለሁ፡፡ በጣም ውድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ገንዘብ በቀላሉ ማስተላለፍ የሚችለው የሄሎ ካሽ አገልግሎትም ገንዘብ በቀላሉ መላክ እንዲቻል፣ ግብይትም እንዲቀላጠፍ ማድረጉን ከተጠቃሚዎች ማወቅ ተችሏል፡፡ ፍቅርተ ተሾመ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆርናሊዝምና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነች፡፡ የሄሎ ካሽ አገልግሎትን ለመጠቀም ከተመዘገበች ዓመት ሆኗታል፡፡በወቅቱ የተመዘገበችው በነፃ ነበር፡፡ እንዴት እንደሚሠራም እውቀቱ ልነበራትም፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን እንዴት እንደሚሠራ ተረድታ ትጠቀምበት ጀመር፡፡

በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ ሱቆች፣ ስቴሽነሪዎች የሄሎ ካሽ ተጠቃሚ በመሆናቸው የሚያስፈልጋትን የትምህርት ግብአቶች ለመግዛት ጥሬ ብር መያዝ አይጠበቅባትም፡፡ የምትፈልገውን ከወሰደች በኋላ ገንዘቡን  በነጋዴው ስልክ ትልክለታለች፡፡ በአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ ምግብ ቤቶችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የምግብ ቤቶቹ ደንበኛ የሆኑት ፍቅርተና ጓደኞቿም ምግብ ከበሉ በኋላ ሒሳብ የሚከፍሉት በሄሎ ካሽ ነው፡፡  

በየፈርጁ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የሄሎ አገልግሎቶች አሰራርና ገበያ በተመለከተ ሪፖርተር አንዳንዶቹን አነጋግሯቸዋል፡፡ በየማስታወቂያ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻለው ሄሎ ትዳር ገበያውን ከተቀላቀለ ዓመት ሆኖታል፡፡በሚሰጠው አገልግሎት  የመወያያ ርዕስ እስከ መሆንም ደርሷል፡፡

የፍቅርና የትዳር ጓደኞችን ማገናኘት፣ የሥራና የጨረታ ጥቆማዎች የመስጠት፣ እንዲሁም አስጠኚ፣ ሠራተኛና አሠሪ የማገናኘት ሥራ ይሠራል፡፡ ምንም እንኳን የሚሰጠው አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ቢሆንም፣ የሄሎ ትዳር አገልግሎት ፈላጊዎች አይለዋል፡፡ ለመጣመድ ፈልገው ወደ ጥሪ ማዕከሉ የሚደውሉ ስለራሳቸው መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን መንገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

 ስም፣ ዕድሜ፣ መልክ፣ ክብደት፣ ሃይማኖት፣ ወርኃዊ ገቢ፣ ቋሚ ንብረት፣ ከዚህ ቀደም የፍቅር ጓደኛ ወይም ትዳር ነበራቸው አልነበራቸውም የሚሉትን ዋና ዋና መረጃዎች በስልክ እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡ አብዛኞቹ የጥሪ ማዕከሉ ደንበኞች ወንዶች ሲሆኑ የሴቷ ዕድሜ፣ የትዳር ሁኔታና መልክ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች ደግሞ የወንድየውን የገቢ ሁኔታ መጠየቅ ይቀናቸዋል፡፡ በቀን እስከ አምስት ሰዎች አገልግሎቱን ፈልገው ይደውላሉ፡፡ እስካሁን 700 ጥንዶችን ያገናኘ ሲሆን፣ 15,000 የሚሆኑ አቻዎቻቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉ ደንበኞችም አሏቸው፡፡

‹‹የደወሉ ሁሉ ደንበኛ ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ የእኛን አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት ከ20 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎች ናቸው፤›› የሚሉት የድርጅቱ ባለቤት ዶ/ር ማዕረግ አማረ፣ ከ20 ዓመት በታች ያሉና ስለማንነታቸው በቂ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ አገልግሎቱን ማግኘት እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡ ይህ የድርጅቱ ሕግ ቢሆንም ሕጉን ተላልፈው የሚደውሉ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች አሉ፡፡ መስፈርቱን እንደማያሟሉ ተነግሯቸው ስልኩን ቢዘጉም፣ ድምፃቸውን ቀይረው በሌላ ስልክ መልሰው ይደውሉላቸዋል፡፡

 ከዚህም ሌላ መስፈርቱን አሟልተው ከሚመዘገቡት ውስጥ ከ20 እስከ 25 የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አብዛኞቹ ወደ ጥሪ ማእከሉ በትክክል አገልግሎቱን  ፈልገውት ሳይሆን ለመቀለድ ነው፡፡ የወሲብ ጓደኛ ፈልገው የሚደውሉ፣ እንዲሁም ሹገር ማሚ ሹገር ዳዲ እንዲያገናኟቸው የሚጠይቁ፣ ባለትዳር ሆነው ተጨማሪ የወሲብ ጓደኛ ፈልገው የሚደውሉም አሉ፡፡

አገልግሎቱን በትክክል ለመቀጠም ፈልገው የሚደውሉም ጥቂት አይባሉም፡፡ በአጋጣሚ ትዳራቸው የፈረሰና የልጅ እናትና አባት የሆኑ፣ ሌሎችም የሕይወት አጋር የሚፈልጉ የጥሪ ማዕከሉ ደንበኞች ናቸው፡፡ ተመሳሳይ ፍላጐት ያላቸውን በሞሏቸው ፎርሞች እያመሳሰሉ እንዲገናኙ ያደርጓቸዋል፡፡ ነገር ግን መስፈርቱን አሟልተው ከሚመዘገቡት መካከል አንዳንዶቹ ትክክለኛ መረጃ ሳይሰጡ ቀርተው ለማጣመድ በሚደረገው ጥረት ላይ የተለያዩ እንቅፋቶች እንደሚያጋጥማቸው ዶ/ር ማዕረግ ይናገራሉ፡፡

በትዳር ፈላጊ መዝገብ ላይ የተመዘገበችው የ30 ዓመት ሴት እንደሆነች በመግለጽ ነበር፡፡ ተመዝግባ ጥቂት ከቆየች በኋላ በዕድሜና በሌሎች ሁኔታዎቿ ይመሳሰላታል ብለው ከገመቱት አንድ ሰው ጋር እንዲገናኙ የጥሪ ማዕከሉ ስልኮቻቸውን አቀያየራቸው፡፡ እነሱም ተቀጣጥረው ተገናኙ፡፡ ሴትዮዋ ግን በስልክና በፎርሙ ላይ ራሷን እንደገለጸችው አልነበረችም፡፡ በአምስት ዓመት የምታንሰውን ሴት ጠብቆ የሄደው ሰው የተገላቢጦሽ ሆነበት፡፡ በሁኔታው ግራ የተጋባው ግለሰብ ወደ አቶ ማዕረግ ስልክ በመደወል ‹‹ቢያንስ በ15 ዓመት ትበልጠኛለች›› ሲል ያልጠበቀው እንዳጋጠመው ነገራቸው፡፡

እስከ ዛሬ ካጣመዷቸው 700 ጥንዶች መካከል በሠርግ የተጋቡ፣ ቃልኪዳን ያሰሩ ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹ሰዎቹን ካጣመድን በኋላ ሥራችን ምን ያህል ውጤታማ መሆኑን ለመገምገም ስልክ ደውለን ስለደረሱበት ሁኔታ እንዲያሳውቁን እናደርጋለን፤›› ያሉት ዶ/ር ማዕረግ ተጣጥመው መኖር በጀመሩ ላይም አንዳንድ ገጠመኞች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

ሴትዮዋ የልጆች እናትና ባለትዳር ነበረች፡፡ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ከባለቤቷ ጋር በፍርድ ቤት ከተለያዩ ቆይተዋል፡፡ ኑሮ በብቸኝነት አልገፋ ብሏት ሄሎ ትዳሮች ጋር ደውላ ከአቻዋ ጋር እንዲያጣምዷትም አድርጋለች፡፡ የልጆች እናትና ፈት መሆኗን ገልጻ ስለነበር ያሳለፈችው ሕይወት ካጣመዷት ሰው ጋር አላጋጫትም፡፡ ግንኙነታቸውም መልካም የሚባል ነበር፡፡ እነሱም በአብሮነታቸው ደስተኛ ነበሩ፡፡

ለስድስት ወራት ያህል በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ ግን የቀድሞ ባለቤቷ እንዲታረቁናሰ ወደ ቤቷ እንድትመለስ ሽማግሌ ያስልክባት ጀመር፡፡ አዲስ ሕይወት መጀመሯን ነግራቸው እንዲተዋት ለማድረግ ብትሞክርም በጀ ብለው አልተዋትም፡፡ ሌላው ቢቀር ለልጆቿ ስትል እንድትመለስ ይማጸኗት ጀመር፡፡ ልመናው ሲበዛበት እሷም በጉዳዩ ማሰብ ጀመረች፡፡ መመለስ እንዳለባትም ተሰማት፡፡ ውሳኔዋንም በሄሎ ትዳር ላገኘችው ጓደኛዋ ነገረችው፡፡ እየከፋውም ቢሆን በሐሳቧ ተስማምቶ ተለያዩ፡፡

በተመሳሳይ አጋጣሚ የሚለያዩ ሰዎች ከተጣመዱት ሰው ጋር መስማማት ያልቻሉ ያጋጠማቸውን ለድርጅቱ በማሳወቅ እንደገና ከሌላ ሰው ጋር እንዲጣመዱ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡ ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ጓደኛው የተለየችው ሰውም በሄሎ ትዳር ተመዝግቦ አቻውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ‹‹የማጣመድ ሥራው 43 በመቶ የሰመረ ነው፡፡ ለአገልግሎቱም በደቂቃ ሦስት ብር እናስከፍላለን፡፡ አንድ ደንበኛም በአማካይ እስከ አምስት ደቂቃ ያህል በመስመር ላይ ስለሚቆይ ገቢው ለክፉ አይሰጥም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በደቂቃ ሁለት ብር የሚያስከፍለውና የተለያዩ ድርጅቶችን አድራሻና ስልክ የሚሰጠው የሄሎ አገልግሎት አፋላጊ ነው፡፡ ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው አፋላጊ አገልግሎቱን የጀመረ አካባቢ ‹‹እናንተ ምንድናችሁ? ቁጥራችሁን ከማስታወቂያ ላይ አግኝተን ነው›› ብለው የሚደውሉ ደንበኞችን በብዛት ያስተናግድ ነበር፡፡

አገልግሎቱ እምብዛም አይታወቅም ነበርና መረጃ ፈልገው የሚደውሉላቸው ሰዎች ቁጥርም ውስን ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀን 8,000 የሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎታቸውን ፈልገው ይደውሉላቸዋል፡፡ የድርጅቱ የጥሪ ማዕከል ኃላፊ ወ/ሮ ሃይማኖት ሥራኒ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ አስፈላጊ መረጃዎችን ሠራተኞቹን በየድርጅቱ በመላክ ያሰባስባል፡፡ እስካሁንም ከ130 ዘርፎች በላይ የተመዘገቡ ድርጅቶች አሉ፡፡ 262 ሆቴሎች፣ 600 ባንኮች በሆቴልና በባንክ ዘርፍ ከተመዘገቡት ድርጅቶች መካከል ናቸው፡፡ አገልግሎቱ ስለአንድ ድርጅት በቂ መረጃ በማቀበል ያለውን ውጣ ውረድ የሚያቀል ቢሆንም፣ አንዳንድ ተቋማት መረጃዎቻቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ‹‹ስለድርጅቱ ያሉትን መረጃ፣ አድራሻና የስልክ ቁጥር ስንጠይቅ ምናገባሽ አንሰጥም የሚሉ ብዙ አሉ፤›› ይላሉ፡፡

አገልግሎቱን ከተዘጋጀለት ዓላማ ውጪ የሚጠቀሙበት ደንበኞች ያጋጥማሉ፡፡ በስካር መንፈስ ደውለው ያልተገባ ነገር የሚናገሩ፣ አላስፈላጊ ድምፅ የሚያሰሙ አሉ፡፡ በሌላ በኩልም በሚያጋጥማቸው ድንገተኛ ክስተት ዕርዳታ ፍለጋ የሚደውሉ ብዙ ናቸው፡፡ የመደፈር፣ የእሳት፣ የመኪና አደጋ ደርሶባቸው ወደ አፋላጊ የሚደውሉ አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የስልክ ጥሪ ሲያጋጥም ወደሚመለከተው አካል በመደወል አደጋው የደረሰባቸው ሰዎች ዕርዳታ እንዲያገኙ እንደሚያደርጉም ኃላፊዋ ይናገራሉ፡፡

ሆቴል ውስጥ ሻወር በመውሰድ ላይ ሳሉ በሩ የተቆለፈባቸው ወደ ጥሪ ማዕከሉ በመደወል በሩ እንዲከፈትላቸው አድርገዋል፡፡ ሊፍት ውስጥ ሆነው ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸውም አፋላጊ ጋር በመደወል ዕርዳታ ማግኘት ችለዋል፡፡

የተለያዩ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲሁም ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል የተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮችም አሉ፡፡ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ ቀይ መስቀል፣ አምቡላንስ፣ የኤችአይቪ ኤድስ የምክር አገልግሎት፣ የግብርና መረጃ ስለአተት ወረርሽኝ መረጃ የሚሰጡት ከነፃ የስልክ ጥሪ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ስለግብርና መረጃ የሚሰጠው ነፃ የስልክ ጥሪ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ በአገሪቱ በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን፣ ስለ ዘር አያያዝና ሌሎችም በግብርና ዙሪያ የተዘጋጁ መረጃዎችን ይሰጣል፡፡ ነገር ግን እንደሌሎቹ የሄሎ አገልግሎቶች መረጃ የሚሰጠው በጥያቄና መልስ መልክ አይደለም፡፡ መረጃውን ማግኘት የሚቻለው ተቀድቶ ከተዘጋጀው ድምፅ ነው፡፡ ጥያቄ ቢኖር እንኳን ለማንሳት አይቻልም፡፡ ወቅታዊ መረጃ በመስጠት ሕዝቡን ከተቃጣ ወረርሽኝ ለመከላከል የተዘጋጁ ነገር ግን የማይሠሩ የስልክ መስመሮችም አሉ፡፡ ሰሞንኛ ስለሆነው የአተት ወረርሽኝ መረጃ የሚገኝባቸው ነፃ የስልክ መስመሮች ቁጥር በአጭር የመልዕክት ሳጥን ከተላከ ቀናት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ሥራ የጀመሩ አይመስልም፡፡ ለቀናት ያደረግነው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...