በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ባሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ የሚመክር ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡
ጉባዔው ዓመታዊ የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ትኩረቱን በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያደረገ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉባዔ በታኅሳስ 2009 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ ስብሰባውን በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው፡፡
የአይ ካፒታል ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሒደት ላይ የምትገኝ አገር እንደመሆኗ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጓ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በመጪው ታኅሳስ ወር የሚካሄደው የፋይናንስ ጉባዔ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ዝግጁ ነው ወይ? የሚለውን እንደሚመለከት ዶ/ር ገመቹ ተናግረዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ከመሆኑ በፊት ሊወሰዱ በሚገባቸው ዕርምጃዎች ዙሪያ የፋይናንስ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀርባሉ፡፡ አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን የገለጹት ዶ/ር ገመቹ፣ ዘርፉ የተለያዩ ችግሮች እንደሚታዩበት ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በርካታ የግል ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቢከፈቱም አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆነ የገለጹት ዶ/ር ገመቹ፣ ይህን የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ዘርፉ ለማምጣት ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ውይይት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከባንክ ብድር ማግኘት ከፍተኛ ውጣ ውረድ የሚጠይቅ ሒደት እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ገመቹ፣ ባንኮች የሚከተሉዋቸው አሠራሮች የተለመዱ መሆናቸውን ጠቅሰው ከተለመዱት ውጪ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን መጀመር እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡
‹‹ባንኮች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የገዙዋቸውን ቴክኖሎጂዎች ሙሉ በሙሉ እየተጠቀሙባቸው አይደሉም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀትና የሠለጠነ ሰው ኃይል ውስንነት አለባቸው፤›› ያሉት ዶ/ር ገመቹ፣ ባንኮች ባለው ውስን የባንክ ባለሙያ ምክንያት ባለሙያ እንደሚቀማሙ ጠቁመዋል፡፡ የፋይናንስ ጉባዔው ለሰው ኃይል ልማት፣ ለባንክ ቴክኖሎጂና ለፋይናንስ ሕግና ደንቦች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ተቆጣጣሪዎች፣ የፋይናንስ ዘርፍ ተመራማሪዎችና የውጭ ባንኮችና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች የሚካፈሉበት የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አይ ካፒታል ኢንስቲትዩት በመጋቢት 2008 ዓ.ም. የምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ፣ ኮንክሪትና ኢነርጂ ጉባዔ በአዲስ አበባ ማዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡