Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትራንስፖርት ሚኒስቴር የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር አገልግሎት በመስከረም ይጀመራል አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከመስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ተመርቆ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ይህንን የተናገሩት፣ ማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ፉሪ ለቡ ጣቢያ እስከ አዳማ ድረስ ያለውን 100 ኪሎ ሜትር በኤሌክትሪክ የሚሠራውንና ለሰው ማጓጓዣ የሚያገለግለውን መስመር፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለሙከራ ለጋዜጠኞች ባስጎበኘበት ወቅት ነው፡፡

1,170 የሚሆኑ የባቡር ፉርጎዎች የሰው፣ የእንስሳ፣ የፈሳሽ፣ የብረትና የከሰል ማጓጓዝ አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ 30 የሚሆኑት ደግሞ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ አንዱ ተጎታች ፉርጎ እስከ 118 መንገደኞች የመያዝ አቅም ሲኖረው፣ በውስጡም ራሱን የቻለ የካፊቴሪያና የመፀዳጃ አገልግሎት ተገጥሞለታል፡፡ ፉርጎዎቹ በውስጣቸው ከበሬታ ለሚሰጣቸው መንገደኞች (VIP) የሚሆኑ ራሳቸውን የቻሉ የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አንድ መንገደኛ ምቾቱ ሳይጓደል እንዲጓጓዝ በማሰብ ዘመናዊነትን እንዲላበሱ ሆነው የተሠሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህ የመንገደኞች ማጓጓዣ ባቡሮች በሰዓት እስከ 120 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለመድረስ ከሰባት ሰዓት ትንሽ ከፍ ያለ ጊዜ ይወስድበታል፡፡

ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ያለውን 656 ኪሎ ሜትር የባቡር ሐዲድ እንደ አዲስ ለመገንባት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መጠየቁ ታውቋል፡፡ 70 በመቶ ከቻይና መንግሥት 30 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ መሆኑም እንዲሁ፡፡ ግንባታው የተከናወነው በሁለት ኮንትራክተሮች ሲሆን ከሰበታ-ሚኤሶ-ደወሌ ድረስ በሲአርሲ፣ እንዲሁም ከደወሌ- ጂቡቲ-ነጋድ ድረስ ደግሞ ሲሲሲሲ በተባሉ የቻይና ኩባንያዎች ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡ አሥራ ስድስት የሰው፣ የዕቃ ማውረጃና መጫኛ ጣቢያዎችም አሉት፡፡ እንዲሁም የሠራተኞች ማደሪያና ለእነሱ የሚያገለግሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው ተጠናቀዋል፡፡

ለዚህ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ 1,170 ሎኮሞቲቮችና ተጎታች ዋገኖች ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 41 ባቡሩን ለመጎተት የሚውሉ ሎኮሞቲቮች ናቸው፡፡ 35 በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ናቸው ተብሏል፡፡ ስድስቱ ሻንቲንግ ሎኮሞቲቮች ደግሞ ሐዲድ ማቀነባበሪያና ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ ባቡሩን በመግፋት ወደ ጣቢያ የሚያደርሱ ናቸው፡፡ ይህ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀምር እስከ 3,500 ቶን ደረቅና ፈሳሽ ጭነት፣ እንዲሁም እስከ 3,000 መንገደኞች በአንድ ጊዜ የማጓጓዝ አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የፍጻሜ ሙከራ ማድረጉ አስደሳች ነው፡፡ ባቡሮቹ የሚያስፈልጋቸውን ስድስት ሺሕ የፈረስ ጉልበት የሚያህል የኤሌክትሪክ ኃይል በሁለት አቅጣጫዎች የሚያገኙ ሲሆን፣ አንዱ ቢጠፋ ከአንዱ ስለሚያገኙ የኃይል መቆራረጥ ምንም እንደማያሠጋቸውም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሌሎች ያደጉ አገሮች የደረሱበት ለመድረስ አንደኛውና ትልቁ ይህን መስመር መጨረስ ነበር፡፡ ምክንያቱም በርካሽ፣ በብዛትና በፍጥነት በቶን የሚለኩ ቁሳቁሶች ስናስገባና ስናወጣ ነው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የምንመደበው፡፡ ስለዚህ ይህ መጠናቀቁ ትልቁ ስኬት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ-ጂቡቲ ለሚገነባው የባቡር መስመር ለ16 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ ሥራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ደግሞ ለ2,500 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች