በሪዮ ኦሊምፒክ በወንዶች ማራቶን ሁለተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከኦሊምፒክ ቡድኑ ጋር ሳይመለስ ቀርቷል፡፡
አትሌቱ ባለፈው እሑድ በሪዮ ኦሊምፒክ የመዝጊያ ውድድር የተካሄደውን የማራቶን ሩጫ ሊያጠናቅቅ ሲል በኦሮሚያ ክልል ለሚካሄደው የተቃውሞ ድጋፍ እጆቹን ከጭንቅላቱ በላይ በማጣመር ተቃውሞውን በኦሎምፒክ መድረክ ላይ ከገለጸ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹እኔ የኦሮሞ ተወላጅ ነኝ፡፡ ቤተሰቦቼ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዲሞክራሲያዊ መብታቸው ካወሩም ይገደላሉ፤›› ብሏል፡፡ አትሌቱ ይህንን ተቃውሞ በማድረጉ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ ሊታሰር ወይም ሊገደል እንደሚችል ተናግሯል፡፡
ሆኖም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፣ ለአገሩ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ይህ አትሌት በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት የሚደርስበት ነገር አይኖርም፡፡ ምንም እንኳን አቶ ጌታቸው አትሌቱ ወደ አገሩ ሲመለስ ከሌሎቹ የኦሊምፒክ ቡድኑ አባላት ጋር ጥሩ አቀባበል ይደረግለታል ቢሉም፣ አትሌት ፈይሳ ከኦሊምፒክ ቡድኑ ጋር ሳይመለስ ቀርቷል፡፡
የ26 ዓመቱ አትሌት ፈይሳ ያለው እዚያው ብራዚል ውስጥ ሲሆን፣ አትሌቱን ለመርዳት ሦስት ሰዎች ሪዮ መግባታቸውንና 91 ሺሕ ዶላር መሰብሰቡን አስተባባሪዎቹ ለአሜሪካን ድምፅ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
በሪዮ ኦሊምፒክ አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብርና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም 44ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑክ፣ ማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ለኦሊምፒክ ልዑካኑ አቀባበል ያደረጉት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሑሴን ናቸው፡፡ ለኦሊምፒክ ቡድኑ የተደረገው አቀባበል እጅግ የተቀዛቀዘ ሲሆን፣ በአቀባበሉ ላይም በብዛት ጋዜጠኞችና የአየር መንገዱ ሠራተኞች ነበሩ የተገኙት፡፡