በሰላሳ አንደኛው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ አትሌቶቿን ከነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ስታሳትፍ ቆይታለች፡፡ ውድድር ለማድረግ ቀድመው ወደ ሥፍራው ያመሩት አትሌቶችን ጨምሮ በውድድሩ ፕሮግራም መሠረት በተለያዩ ቀናት አትሌቶቹ ወደ ሪዮ ማምራት ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው ውድድሮች ውስጥ አትሌቲክስ፣ ብስክሌትና የውኃ ዋና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ቀን የሪዮ ኦሎምፒክ የአከፋፈት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ባንዲራን ከያዘው አትሌት አነጋጋሪ ጉዳዮች ሲሰሙ ነበር፡፡ ይኸው አትሌት ሮቤል ኪሮስ ኢትዮጵያን ወክሎ ያመጣው ውጤትና ያሳው አቋም በውኃ ዋና የዓለምን ሚዲያ ቀለብ የገዛ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በማራቶን በመወከል 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ርቀቱን በመጨረስ የብር ሜዳለያ ያገኘው ፈይሳ ሌሊሳ ጉዳይ በመዝጊያውም ቀን የብዙ ታላላቅ ሚዲያዎችን ዳግም ቀልብ ገዝቷል፡፡ ሁለት እጆቹና በማጣመር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየተደረገ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመደገፍ ያሳየው ምልክት ውዝግብ አስነስቷል፡፡ አትሌቱ ውድድሩን በማጠናቀቅ እንዲሁም ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተመሳሳይ ድርጊት ሲያደርግ ነበር፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅትም በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ‹‹ወደ አገር ቤት ከተመለስኩ ይገሉኛል ወይም ወደ ዘብጥያ ያወርደኛል፤›› ሲል ተናግሯል፡፡
አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ በኦሊምፒክ ላይ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ጉዳይን በውድድር ላይ ማሳየቱ የብር ሜዳሊያውን ሊያስነጥቀው ይችላል የሚል የብዙዎች ስጋት ነበር፡፡ ነገር ግን የብር ሜዳሊያውን ከመነጠቅ ድኗል፡፡
በጉዳዩ ላይ የተለያየ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት በመስጠት ሲዘግቡ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡
በዚህም መሠረት ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ለጀግና አትሌታችን ሌሊሳ ፈይሳ የጀግና አቀባበል ያደርግለታል፤›› በማለት አቶ ጌታቸው በፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሲመጣ ምንም ዓይነት ችግር ሊያጋጥመውም እንደሚያችል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡
አትሌቱ ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ ለተለያዩ አገሮች የጥገኝነት ጥያቄ እንደሚያቀርብ የተናገረ ሲሆን የገንዘብ መዋጮ በወጪ በሚገኙ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች እየተደረገለት መሆኑን እየተገለጸ ይገኛል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ወደ ብራዚል ያቀኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነሐሴ 17 ቀን 2008 በኢትዮጵያ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በውድድሩ አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብርና አምስት የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳልያዎች ማምጣቷ ይታወሳል፡፡
በዚህ የሜዳሊያ ስብስብ ከ207 አገሮች 44ኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡