Tuesday, February 27, 2024

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሊገባደድ የቀናት ዕድሜ ብቻ በቀረው 2008 ዓ.ም. ለገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እጅግ ፈታኝ ዓመት እንደነበር ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በተለይ ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች የተፈጠሩት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችና የተቃውሞ ሠልፎች፣ የብዙ ዜጐችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ ድርጅቱን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተቱት ይነገራል፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዕቅድን መነሻ ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መፍትሔ ሳያገኝ፣ በአማራ ክልል ደግሞ በቅማንትና በወልቃይት የማንነት ጥያቄዎች የተነሳ አድማሱን ወደ አማራ ክልል አስፍቷል፡፡ አሁንም መፍትሔ ያላገኙ በርካታ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በክልሎቹ የተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ነው፡፡ ለአብነትም በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ከነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ እየተካሄደ ሲሆን፣ እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡ 

ከዚህ ችግር በተጨማሪ ሕዝቡ የተለያዩ የመልካም አስተዳደርና የፍትሐዊነት ጥያቄዎችን የሚያቀርብ ሲሆን፣ መንግሥት በበኩሉ የጥያቄዎቹን መኖር ቢያምንም እየተካሄዱ ካሉት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ጀርባ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች እጃቸው አለበት በማለት ይወነጅላል፡፡

በሌሎች አገሮች እንደሚስተዋለው እንዲህ ያለ ሕዝባዊ ጥያቄ ገንፍሎ በሚወጣበት ወቅት ድምፃቸው የሚሰማው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ፣ ጉዳዩን ብለን ነበር በሚል አንድምታ እየታዘቡት ይገኛሉ፡፡

እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ነገር ሊከሰት እንደሚችል በተደጋጋሚ ለመንግሥት አሳውቀን የነበረ ቢሆንም መንግሥት ሊሰማን ባለመቻሉ ሕዝቡ ችግሩን ራሱ ወደ አደባባይ ይዞት መጥቷል በማለት፣ አሁን የተከሰተው ችግር ሥር የሰደደና ሲንከባለል የመጣ ነው በማለት አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች መንግሥትን ክፉኛ ይተቻሉ፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት ዋናው ቁም ነገር መንግሥት ችግሩ ምንድነው? የችግሩ መፍትሔስ ምንድነው? እነዚህ ችግሮች በየቦታው የሚፈጠሩት ለምንድን ነው? ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል የሚሉት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ ናቸው፡፡

ይህን ሲያደርግም ተጠያቂውን ሌላ አካል ማድረግ ሳይሆን በእኔስ በኩል መሟላት ያለበት ምንድነው? የሚለውን አትኩሮ መመልከት አለበት በማለት ያሳስባሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሁልጊዜ ሌላውን ስህተተኛ ራሱን ደግሞ ምንም ስህተት የማይሠራ እያስመሰለ ነው ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክረው፡፡ ይህ ደግሞ እንደማይሠራ የሰሞኑ የአገሪቱ ሁኔታ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፤›› በማለትም ኢሕአዴግ የሌሎችንም ሐሳብ እንዲያዳምጥና የመፍትሔው አካል ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ የሕዝቡ ጥያቄ በተለያየ መልኩ ሲንከባለል እንደመጣ የሚስማሙት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ችግሮቹን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ ቆም ብሎ ጉዳዩን ማጤንና መመርመር ይሻል ይላሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡ የሕዝቡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጨፈለቁና የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም በሚባል ሁኔታ እንዲጠፉ ላለፉት 25 ዓመታት ከፍተኛ ሥራ በመንግሥት በኩል ተሠርቷል፤›› በማለትም የተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከምና የሕዝቡ ሁሉን አቀፍ ጥያቄዎች አለመመለስ አገሪቷን መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትሆን እንዳደረጓት ይገልጻሉ፡፡

የተለያዩ አካላትና ፓርቲዎች አሁን ለተፈጠረው አለመረጋጋት የተለያዩ ምክንያቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነገሠ ተፈረደኝም የችግሩ መንስዔ ነው ብሎ ፓርቲያቸው የሚያምነውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡  

መንግሥት በተለያዩ ወቅቶች ለተነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች የሰጠው የኃይል ምላሽ ለችግሮቹ መባባስ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አቶ ነገሠ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ችግሮችን ለመፍታት የኃይል ዕርምጃ መውሰድ የለበትም፡፡ በሕዝብ ላይ የተለያየ ሽብር መድረስ የለበትም፡፡ መንግሥት ዜጐችን መግደል ይቅርና ማሰርና መደበደብ የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት የወሰዳቸው የኃይል ዕርምጃዎች ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ዜጐች የማንንም ዕርዳታ ሳይገኙ አደባባይ እንዲወጡ እንዳደረጋቸው በመጥቀስ፣ አሁንም መንግሥት ሰከን ብሎ ጉዳዩን በቅጡ እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ይህ አሁን ገንፍሎ የወጣው እስከ እምቢተኝነት የደረሰው የሕዝብ ቁጣ ባለፈው ዓመት ምርጫ ኢሕአዴግ ቀልዶበትና ወንጀል ሠርቶበት መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ማለቱ ያስከተለው ቀውስ ነው፡፡ የችግሩ ሁሉ እናት እርሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ የመብት፣ የማንነትና ሌሎች ጥያቄዎች ሁሉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደማይፈቱ ማረጋገጫ ነው፤›› በማለት ተቃውሞውን ከምርጫ ውጤት ጋር የሚያያይዙት ደግሞ የወቅቱ የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡

አገሪቱ እየሄደችበት ያለውን ችግር አስመልክቶ ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ጥያቄ እንዳቀረቡ የሚገልጹት የየፓርቲው አመራሮች፣ መንግሥት ጥያቄውን በወቅቱና በአግባቡ ሊመልስ ባለመቻሉ ሕዝቡ ቁጣው ተቀስቅሶ አደባባይ መውጣቱንም ያሰምሩበታል፡፡

ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው ኢዴፓ የችግሮቹን አሳሳቢነትና ጥልቀት በመመልከት ለጋራ ምክር ቤቱ የብሔራዊ እርቅ ሰነድ እንዳቀረበ አቶ ዋስይሁን ይገልጻሉ፡፡

የብሔራዊ እርቅ ሰነዱን ከአንድ ወር በፊት ለምክር ቤቱ እንደቀረበ የሚገልጹት አቶ ዋስይሁን፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ በመግለጽ ጉዳዩ በፍጥነት መታየት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

‹‹ባቀረብነው የብሔራዊ እርቅ ሰነድ ላይ ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡ ነገር ግን በዋናነት አሁን ካለው ሁኔታ ጋር በሚመጥን ደረጃ ውይይቱ ፍጥነት የለውም፡፡ ሁኔታዎች ደግሞ በፍጥነት ከቀን ወደ ቀን እየተቀያየሩ ነው፡፡ ሆኖም ግን በተጨባጭ በጋራ ምክር ቤቱ በኩል የመፍትሔ ሐሳቦች እያቀረብን ነው፤›› በማለት በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳይ ላይ ፓርቲው እየሠራው ያለውን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ መንግሥት የኃይል ዕርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብና ለዘላቂ መፍትሔው ደግሞ የሕዝብ ወይም የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሰማያዊ ፓርቲ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን የሚገልጹት አቶ ነገሠ፣ ‹‹እስካሁን ግን የተገኘ ምላሽ የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን የተነሱትን የሕዝብ ጥያቄዎች መምራት አይችሉም፡፡ አቅሙም የላቸውም፡፡ ሕዝቡም ራሱን ለብቻው ነጥሏል፤›› ሲሉ ችግሮችን ለመፍታት ፓርቲው ያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ገዥው ፓርቲና መንግሥት ከእኛ ጋር ተገናኝቶ ለመፍትሔ ፍለጋ መነጋገርም ሆነ መደራደር እንዳለበት፣ የምንነጋገርባቸውን የድርድር ነጥቦች ይፋ አድርገን በተደጋጋሚ ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ስለዚህ ከኢሕአዴግ ጋር ለመነጋገር ሰሞኑን የተከሰተው ሁኔታ ብቻውን መነሻ አይሆንም፤›› በማለት የሚገልጹት ደግሞ ፕሮፌሰር በየነ ናቸው፡፡

‹‹የዚህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይከሰት መንግሥት ቀደም ብሎ ሊነጋገርና መፍትሔ ሊፈልግ ይገባል የሚል አቋም ላለፉት አሥር ዓመታት በላይ ስናራምድ ቆይተናል፡፡ ስለዚህ ይህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አዲስ የድርድር ወይም የንግግር አጀንዳ ነው ብለን ጥያቄያችንን እንድናጠናክር ወይም እንድናዘጋጅ ምክንያት የሚሆነን አይደለም፤›› በማለት ኢሕአዴግ ግትር አቋም አለው ሲሉ ተችተዋል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች

‹‹ቀደም ብለን እንደተነበይነው ኢሕአዴግ በሚለው ዓይነት ነገሮች ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ እንዲቀጥልም ካስገደደ ነገሮቹ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ከራሱም ቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ ሕዝቡ እጅ ይገባሉ፡፡ አመራር የሌለው አብዮታዊ ሁኔታም ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ተበደልኩባቸው የሚላቸውን ጉዳዮች በአግባቡ ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› በማለት ፕሮፌሰር በየነ የተፈጠረውን ችግር ሊፈታው ይችላል የሚሉትን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ ሕዝቡን ያሳተፈ የመፍትሔ ሐሳብ እንደሚያስፈልግ የሚስማሙት አቶ ነገሠ፣ ‹‹የሕዝብ ጥያቄ መታፈን ሁልጊዜ የሚያስከትለው ጣጣ አለው፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ መታፈን፣ የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ከዚያም ከበድ ሲል የማንነት ጥያቄዎችን በአግባቡ አለመመለስ ከባድ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዳችን ፕሮግራም መሠረት ቁጭ ብለን ተደራድረንና ተወያይተን ለሕዝቡ የሚበጀውን መወሰን አስፈላጊ ነው፤›› በማለት መድረክ ያለውን የመፍትሔ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

ብሔራዊ እርቅ የሚለው መሠረታዊ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሆነ የሚገልጹት ደግሞ ዶ/ር በዛብህ ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹ወቅታዊ ጉዳይን በተመለከተ ሁሉን የሚወክል አካል ከመንግሥት ጋር እንዲነጋገርና ሕዝቡን የሚወክል የሽግግር መንግሥት ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብሔራዊ እርቅ የሚለውን ሐሳብ ወደ ጠረጴዛ የምናቀርበው፤›› ሲሉ የመኢአድን አቋም አስረድተዋል፡፡

በዋናነት ሁሉንም የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ባለድርሻ አካላትን ሊያስማማና ሊያግባባ የሚችል መደላድል መፈጠር እንዳለበት የሚገልጹት ደግሞ አቶ ዋስይሁን ሲሆኑ፣ መደላድሉን ሊፈጥር የሚችል አንድ ተቋም እንዲሁ መቋቋም እንዳለበት ኢዴፓ እንደሚያምን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይህ የሚቋቋመው ተቋም ሁሉም ያገባኛል የሚሉ አካላት ሁሉ የተወከሉበትና የሚሳተፉበት መድረክ ያመቻቻል፡፡ ዓላማው የምርጫ ሕጉን ጨምሮ ሌሎች ሕጐችን ማሻሻል ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ እንዲወስን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በእኛ እምነት ብቸኛው መፍትሔ ይህ ነው፡፡ ይህን ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ያሉትን ችግሮች መፍታት የምንችልበት ዕድል አይኖርም፤›› በማለት ሁሉን አቀፍ ውይይት የመፍትሔው ቁንጮ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡  

   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -