Monday, July 22, 2024

የአገሪቱ ስፖርት ሥር ነቀል ለውጥ ካልተደረገበት ውድቀቱ ይቀጥላል!

ሰሞኑን በተጠናቀቀው የሪዮ ኦሊምፒክ አገራችን ኢትዮጵያዊያን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ እንድትገባ ላደረጓት አትሌቶቻችን ምሥጋና ይድረሳቸው እንላለን፡፡ በተለይ በአሥር ሺሕ ሜትር የሩጫ ውድድር የዓለምና የኦሊምፒክ ክብር ወሰኖችን በመሰባበር የወርቅ ሜዳሊያ፣ እንዲሁም በአምስት ሺሕ ሜትር ሩጫ ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ አልማዝ አያና ደግሞ ድርብ ምሥጋና ይገባታል፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ ከፍተኛ ፉክክር አድርጎ ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ በስፖርቱ ዓለም የተለመደ ክስተት በመሆኑ፣ የአገሪቷን ሰንደቅ ዓላማ በኦሊምፒክ አደባባይ እንዲውለበለብ ያደረጉ ጀግኖች መወደስ አለባቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በዘንድሮ የሪዮ ኦሊምፒክ ተጋልጠው የወጡ ችግሮቻችን የአገሪቱ ስፖርት ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው ቁልጭ አድርገው አሳይተዋል፡፡ በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡

በአገራችን የተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ውስጥ የሚታዩ ችግሮች በተለያዩ መስኮች ውስጥ የምናያቸው የውድቀት ማሳያ ምልክቶች ናቸው፡፡ በአገሪቷ ውስጥ ካሉ የስፖርት ፌዴሬሽኖች መካከል ብዙዎቹ ዕድሜ ጠገብ ከመሆናቸው በስተቀር፣ የመኖራቸው ትርጉም በራሱ አይገባም፡፡ አገሪቱ የዛሬ 60 ዓመት በሜልቦርን ኦሊምፒክ መወዳደር ስትጀምር ከአትሌቲክስ በተጨማሪ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ነበሯት፡፡ በ60 ዓመታት ውስጥ በሒደት በተለያዩ ስፖርቶች በኦሊምፒክ እየተወዳደርን የውጤት ባለቤት መሆን ሲገባን፣ አንዳንዴ በቦክስና በብስክሌት ከሚደረጉ እጅግ በጣም አናሳ ሙከራዎች ውጪ ሙጥኝ ተብሎ ያለው በመካከለኛና በረጅም የሩጫ ውድድሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአጫጭር ርቀቶች ለመወዳደር አናሳ ሙከራ ቢደረግም፣ ጠንክሮ ስላልተሠራ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አይታይም፡፡ በማራቶን፣ በአሥር ሺሕ፣ በአምስት ሺሕና በመሳሰሉት የሩጫ ውድድሮች የነበረን ጠንካራ ተሳትፎ እያሽቆለቆለ አሳፋሪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡ እንኳን በሌሎች መስኮች ውጤታማ ለመሆን በጀግኖቻችን ተይዘው የነበሩትን አሳልፈን በመስጠት ታሪክ መሥራት ተስኖናል፡፡ ስፖርት ወዳዱ ሕዝባችን በሚገኙት ውጤቶች አንገቱን እየደፋ በቀድሞ ድሎች እየቆዘመ ነው፡፡ በዚህ አሳዛኝና አሳፋሪ ወቅት ለሥር ነቀል ለውጥ መነሳት የግድ ነው፡፡

በስፖርቱ ውስጥ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ዋነኛው የአቅምና የብቃት ማነስ ነው፡፡ በስፖርት መዋቅሩ ውስጥ ሆነው አመራር ከሚሰጡ ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች የተሰማሩ ግለሰቦች ብቃት ከአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎትና ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ በዓለም ሻምፒዮናና በኦሊምፒክ የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለ፡፡ ራዕይ ቢኖር ኖሮ ከሩጫ በተጨማሪ በዝላይ፣ በጦር ውርወራ፣ በውኃ ዋና፣ በቦክስ፣ በመረብ ኳስ፣ በቅርጫት ካስና በመሳሰሉት ዘርፎች ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪዎች ይጠፋሉ? ለታዳጊዎችና ለወጣቶች በጥናትና በምርምር የተደገፈ ሥልጠና ለማካሄድ ዕቅዶችን ነድፎ መንቀሳቀስ ያቅታል? ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ለማብቃት የሚሆን በጀት ጠፍቶ ነው? ጎረቤት ኬንያ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ተሳትፋ ውጤታማ መሆን የቻለችውና እኛ ያቃተን ለምንድነው?  ከወሬ በዘለለ ለተግባር የተሰጠ ቦታ ስለሌለ ብቻ ነው፡፡ ኬንያ የተለያዩ የስፖርት ማሠልጠኛዎችን ገንብታ ውጤታማ ስትሆን እኛ ምን እያደረግን እንደሆነ እኮ ይታወቃል፡፡ በተግባር የማይተረጎሙ ዲስኩሮች ብቻ ናቸው የሞሉት፡፡

ወጣቶች የሚሠለጥኑባቸው አካዴሚዎች ተገነቡ ይባልና ሠልጣኞች የስፖርት ትጥቅ አጣን እያሉ ሲጮሁ በአደባባይ በተደጋጋሚ ይሰማ የለ? ለሥልጠና የሚረዱ ቁሳቁሶች (ቁምጣ፣ ጫማ፣ ኳስ፣ ወዘተ) ማቅረብ እያቃተ አንዱ በሌላው ላይ ሲያሳብብ መስማት የተለመደ የዘወትር እንጉርጉሮ ነው፡፡  በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በተከፈቱበት አገር ውስጥ አሁንም የባለሙያ እጥረት ይነገራል፡፡ ልምድ ያካበቱ ዜጎች በሞሉበት ወሬው ሁሉ ችግር ነው፡፡ በመንደር ልጅነትና በጥቅም ግንኙነት የሚተባበሩ ወገኖች ሁለመናቸውን ሙስና ላይ አድርገው እንዴት ውጤት ይጠበቃል? በስፖርቱ ውስጥ በሚታየው ቡድንተኝነትና ሙስና ምክንያት ራዕይ ያላቸው ባለሙያዎች እየተገፉ፣ ስፖርቱ የቪዛና የተለያዩ ጥቅሞች ማጋበሻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአጋጣሚ በሚገኙ ድሎች ውስጥ የተወሸቁ የተጠራቀሙ ውድቀቶች በዘንድሮ ኦሊምፒክ ተጋልጠው የወጡት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የአገሪቱ ስፖርት ምን ያህል መቀለጃና መጫወቻ እንደሆነ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲያሳየን ለሥር ነቀል ለውጥ አለመዘጋጀት፣ ውድቀትን ያባብሰዋል እንጂ ማንንም አይጠቅምም፡፡

በአትሌቲክሱ ገናና ስም ያላቸው ነባር አትሌቶችና አሠልጣኞች እየተገፉ በሩ ሲዘጋባቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ወጣት አትሌቶችን ካካበቱት ልምድና የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ማካፈል የሚገባቸው እነዚህ ወገኖች ድርሽ እንዳይሉ የሚደረገው ለምን ነበር? የሚሰጡትን ነፃ ወገናዊ አገልግሎት ከምሥጋና ጋር ተቀብሎ ለወጣት አትሌቶች ተጨማሪ ብርታት መጠቀም ሲገባ እንደ ጠላት እያገለሉ ምን ተገኘ? በነፃ የሥልጠና  ማኑዋል ከመስጠት ጀምሮ በመስክና በትራክ ላይ እየተገኙ የእርማት ድጋፍ እንዲሰጡ መጋበዝ ሲገባ ሲደረግ የነበረው ተቃራኒው ነው፡፡ በአገሪቱ የአትሌቲክስ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አትሌቶቻችን አንድ አገር መወከላቸውን ረስተው ባላንጣ ይመስል ዓይን ላይን መተያየት እንኳ እንደማይፈልጉ በገሃድ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሳይሆን የተለያየ አገር ያላቸው ይመስል ያ የመረዳዳት አኩሪ ባህል ጠፍቶ የታየው ለምን ይሆን? በአገሪቱ ለውጤት የሚያበቁ አሠልጣኞች የሌሉ ይመስል አትሌቶች በራሳቸው ፈቃድ እንደፈለጉ ወጣ ገባ እያሉ መሮጥ የጀመሩት ለምንድነው?  የግል አሠልጣኝ ላይ ሙጭጭ በማለት ለብሔራዊ አሠልጣኞች አለመታዘዝ ንቀት የመጣው ለምንድነው? ይኼ መናናቅ የሚያሳየው የአመራር ውድቀትን ብቻ ነው፡፡ አገርን ለኃፍረትና ለውድቀት የዳረገ ውጤት ሲመዘገብ ሥር ነቀል ለውጥ መደረግ አለበት የሚባለው ለዚህ ጭምር ነው፡፡ አሁን ባለው አያያዝና አመራር መቀጠል አይቻልም፡፡

በሪዮ ኦሊምፒክ በውኃ ዋና የታየው ቅሌት አገሪቱ ምን ያህል ችግር ውስጥ እንዳለች ብቻ ሳይሆን፣ ፌዴሬሽኖቻችን እንዴት ዓይነት ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ማሳያ ጭምር ነው፡፡ የውኃ ስፖርቶች ከሚባለው ፌዴሬሽን ጀምሮ ሁሉም ፌዴሬሽኖች ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የተዝረከረኩና ብልሹ አሠራሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድም መነሻ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ለዘመናት የተደበቁ ብልሹ አሠራሮች በጠንካራ ግምገማ ተነቅሰው ወጥተው መሠረታዊ ለውጥ ካልተደረገ ውድቀቱ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ ዕድሜ ጠገቡ እግር ኳስ ከሴካፋ አልዘል ብሎ ማጥ ውስጥ የሚገኘው  ከክለቦች ጀምሮ እስከ ፌዴሬሽኑ ድረስ ሥር ነቀል ለውጥ ባለመካሄዱ ነው፡፡ እግር ኳስ የሚወደው ሕዝባችንና የእግር ኳሱ ደረጃ የማይመጣጠኑት ራዕይ አልባና አርቆ አሳቢ መሪዎች በመጥፋታቸው ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ ስፖርቶች የእንፉቅቅ የሚጓዙት በብልሹ አስተዳደርና በራዕይ አልባዎች በመወረራቸው ነው፡፡ በፍፁም የማያስተባብሉት ብልሽት ሰፍኗል፡፡ ይኼ ብልሽትም የአገሪቷንና የሕዝቧን አንገት አስደፍቷል፡፡

በስፖርቱ ዘርፍ የምናየው ውድቀት የበርካታ ችግሮቻችን ማሳያ ነው፡፡ ምሬት የሚፈጥሩና ብሶት የሚቀሰቅሱ ችግሮች እየፈጠሩ ያሉትን ነውጥ እያየን ነው፡፡ አሁን ደግሞ በስፖርቱ ውስጥ የሚታዩ የተበለሻሹ አሠራሮች በኦሊምፒኩ ፍጥጥ ብለው ወጥተዋል፡፡ በስፖርቱ ዘርፍ መደበቅ የማይቻለው ውድቀት እንዲህ በአደባባይ ተጋልጦ ሲታይ፣ በሁሉም ፌዴሬሽኖች ውስጥ ምን ያህል አሳሳቢ ችግሮች እንዳሉ በቀላሉ መታዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህም የስፖርቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ተቆርቋሪ ባለድርሻ አካላትና ዜጎች በሙሉ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ብርቱ ጫና መፍጠር አለባቸው፡፡ ብቃት ሳይኖራቸው አመራር ላይ የተሰየሙም ሆነ ተሹለክልከው የገቡ በሙሉ ራሳቸውን በራሳቸው ያግልሉ፡፡ ሥር ነቀሉ ለውጥ በውጤታማ ዜጎች እንዲከናወን ያላንዳች ኃፍረት ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ ሰበብ መደርደርና የቆይታ ዕድሜን ለማራዘም የሚደረጉ አጉልና አሰልቺ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ ካሁን በኋላ ከፊታችን የዓለም ሻምፒዮናና የቶኪዮ ኦሊምፒክን በማሰብ ለዝግጅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አስተማማኝ መሠረት በብቁ ባለሙያዎች ይጣልላቸው፡፡ ኢትዮጵያችን ወደ ቀድሞ ክብሯ ትመለስ ዘንድ ኃላፊነትና ባለቤትነት የሚሰማቸው ወገኖች በሙሉ ለሥር ነቀሉ ለውጥ መምጣት ይነሱ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተለመደው አሰልቺና ብልሹ አሠራር መቀጠል ከተፈለገ ግን የስፖርቱ ውድቀት ይፋጠናል!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...