Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምቀን የጨለመባቸው የሶሪያ ሕፃናት

ቀን የጨለመባቸው የሶሪያ ሕፃናት

ቀን:

ፊቱ ላይ ምንም የማይነበብበትና ፈጽሞ ሊታመን የማይችል መደንዘዝ የሚታይበት የአምስት ዓመት ሕፃን የማይረሳ ትውስታ ፈጥሮ አተኩሮ ይመለከታል፡፡ ከተቀመጠበት አምቡላንስ ውስጥ ሆኖ የአምስት ዓመቱን ሕፃን ለተመለከተው፣ እንደ አምስት ዓመት ሕፃን ሳይሆን ያለዕድሜው በብዙ ነገሮች ውስጥ ያለፈ መስሏል፡፡ ፀጉሩ፣ ፊቱ፣ እግሩና እጆቹ አቧራ ጠግበዋል፡፡ በግራ ዓይኑ በኩል ፊቱ በመጐዳቱ ደም ይታያል፡፡ ጉስቁልናው፣ እግሩ ላይ የሚታዩ ጉዳቶች ሕፃኑ ከአንዳች አደጋ በአጋጣሚ እንደተረፈ ይመሰክራሉ፡፡ የአምስት ዓመቱ ሶሪያዊ ኦምራን ዳክኔሽ በዕድሜው ሙሉ ጦርነት፣ የተኩስ እሩምታ፣ የአውሮፕላን ጋጋታና የቦምብ ፍንዳታ እንጂ የሰላም አየርን፣ ቡረቃንና ደስታን አያውቅም፡፡ አስፈሪና ልብ ሰባሪ የሆነው ጦርነት ሰለባ ነው፡፡ አስተሳሰቡና ልጅነቱ ገና በጨቅላነቱ በጦርነት ተሰልቧል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ የከረመው ዳክኔሽ፣ የሶሪያና የሩሲያ ጦር አሌፖ በሚገኙ ሸማቂዎች ላይ አድርገውት በነበረው ድብደባ ሳቢያ ከፍርስራሽ ሥር ከወጡ ሕፃናት አንዱ ነው፡፡ የ10 ዓመቱ ታላቅ ወንድሙ አሊ ዳክኔሽ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ ሲያልፍ ኦምራን ግን ተርፏል፡፡

በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተከሰተ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እንኳን ለሕፃናቱ ለአዋቂዎቹም መግቢያ መውጫ ጠፍቷል፡፡ ዕድል የቀናቸው ሲሰደዱ ያልቀናቸው ብዙዎች የጥይትና የቦምብ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕፃናት ተጐድተዋል፡፡ ለሶሪያውያኑ ቤት ውስጥ መሆንም ሆነ ደጅ መቀመጥ ሁለቱም ከአየር ድብደባና ከጥይት እሩምታ አያስጥሉም፡፡ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን መጣ ብለው ውጭ ሲወጡ የጥይት፣ ጥይት ተተኮሰ ብለው ቤት ሲገቡ የአውሮፕላን ድብደባ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በእንግሊዝ በጐ ፈቃደኞች ከፍርስራሽ ሥር ወጥቶ በአምቡላንስ ተጭኖ ወደ ሕክምና ሲወሰድ ፎቶ የተነሳው ኦምራን፣ የዓለምን ቀልብ ሳበ እንጂ፣ ሶሪያውያኑ ሕፃናት ከዚህም የከፋ መከራን እያሳለፉ፣ እየተራቡ፣ በፍርኃት እየተናጡና ሕይወታቸውን እየገበሩ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴም፣ አሌፖን በሠለጠነው ዘመን ዘግናኝ ጦርነት ከሚካሄድባቸው ሥፍራዎች አንዷ ናት ሲል ይመድባታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሶሪያ አማፅያን፣ በሩሲያ የሚታገዘው የሶሪያ መንግሥት፣ እንዲሁም ሽብርተኛው አይኤስ የሚያደርጉት ፍልሚያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጐች መግቢያ እንዲያጡ አድርጓል፡፡ በነሐሴ መጀመሪያ ላይ መግለጫ የሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲም፣ ከሰኔ ጀምሮ 250,000 ያህል ሰላማዊ ሰዎች በአማፅያኑ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ምሥራቃዊ አሌፖ መፈናፈኛ አጥተው መቀመጣቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩትም በመስኪዶች፣ በሕዝብ መናፈሻዎችና በየጐዳናው መጠለላቸውን ገልጿል፡፡ ባለፈው ወር ከተማዋ የውኃ እጥረተ ገጥሟታል፡፡ ሴቭ ዘ ችልድረን በከተማዋ ለሚደርሱ ችግሮች ተጋላጭ ከሆኑት አንድ ሦስተኛው ሕፃናት ናቸው ሲል፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምም በሕፃናቱ ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን አካላዊና አዕምሮአዊ ጉዳት ‹‹የቀን ጨለማ›› ሲል ይገልጸዋል፡፡

‹‹ሕፃናት በቦምብ ፍንዳታ ውስጥ መኖርን ለምደዋል፡፡ መጫወቻቸውን ፍርስራሽ ላይ፣ የሚጫወቱት ደግሞ በቀለሃና በጦር መሣሪያ ውድቅዳቂዎች ሆኗል፡፡ ይህ ለሶሪያ ሕፃናት ሕይወታቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለቀየረ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከሕፃናቱ የተወሰኑት እጃቸውን፣ ሌሎች ደግሞ እግራቸውን በጦርነቱ አጥተዋል፡፡ የወደፊት ሕይወታቸውም ሙሉ ለሙሉ በችግር የተተበተበ ይሆናል፤›› ሲሉ የእንግሊዝ የዕርዳታ ሠራተኛ ታኪር ሸሪፍ በስካይፒ ለኤንቢሲ ኒውስ ተናግረዋል፡፡

በአሌፖ ሕክምና በመስጠት ላይ የሚገኙ 15 ዶክተሮች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በላኩት ግልጽ ደብዳቤ በሶሪያ ያለውን ቀውስ እንዲታደጉ፣ ዜጎችንም ከሞት አፋፍ እንዲያወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሐምሌ ብቻ በሕክምና ተቋማት ላይ 42 የአውሮፕላን ድብደባዎች መፈጸማቸውን ቢያንስ በ17 ሰዓት ውስጥ አንዴ ድብደባ እንደሚኖር አሳውቀዋል፡፡ ይህም በጦርነቱ የተጐዱ አዋቂዎችንም ለማከም ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡

በአሌፖ የተሰማሩ የዕርዳታ ሠራተኞች በአሌፖ ያሉ ዜጐች ሞትን እየጠበቁ እንደሚኖሩ፣ አንዳንዶቹ ምንም የሚረዳቸው ወገን እንደሌላቸውና ብቸኛ እንደሆኑ፣ ሆኖም ሴቶቹም ሆኑ ሕፃናቱ ጠንካራ መሆናቸው እንደሚገርማቸው ይናገራሉ፡፡

ሕፃናት የጦርነት ሰለባ ከመሆን ባለፈም ጦረኛና አጥፍቶ ጠፊ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች በዓለማችን እየተስተዋሉ ነው፡፡ አይኤስ የሕፃናት አጥፍቶ ጠፊዎችና አንገት ቀይዎች ሲያሠለጥን፣ ቦኮ ሐራምም ሕፃናትን ለአጥፍቶ ማጥፋት ይጠቀማል፡፡ አልሽባብ ደግሞ የሕፃናት ተዋጊዎችን በጦር አውድማ ያሠልፋል፡፡ በሶሪያ ሕፃናት ለውትድርና ተሠልፈው ባይታዩም የጦርነት ሰለባ ሆነዋል፡፡

በሩሲያ የሚታገዘው የሶሪያ መንግሥት ጦር አማፅያንንና አይኤስን ለማጥፋት ጦርነት ሲያካሂድ አሜሪካ፣ ቱርክና የባህረ ሰላጤው ዓረብ አገሮች አማፂ ቡድኖችን ይረዳሉ፡፡ የኢራን ሚሊሻ ተዋጊዎችና የሊባኖስ ሒዝቦላህ አባላት የሶሪያውን ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን ይረዳሉ፡፡ ሮይተርስ እንደሚለው ጦርነቱ በየፊናው የውጭ ጣልቃ ገብነት ቢኖርበትም፣ በአብዛኛው ጉዳት እየደረሰ ያለው በአማፅያን ይዞታ በሆኑ ሥፍራዎች ነው፡፡ በዚህም ሕፃናት ተጐድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አል አሳድ ባለፈው ወር ከኤንቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በየጊዜው በጦርነቱ ስለሚሞቱ ሕፃናት ተጠይቀው ነበር፡፡ አል አሳድ እንደሚሉት፣ የማን ልጆች? የት? መቼ? እንዴት? ተገደሉ የሚለው ሁሉ ከፕሮፓጋንዳ ያልዘለለ የውሸት ወሬ ነው፡፡ በየኢንተርኔቱ የሚለቀቁ ምሥሎችም የተቀነባበሩ ናቸው ይላሉ፡፡ ‹‹ስለእውነት እናውራ ካልን እውነት እናውራ፡፡ ባልተጨበጠ ውንጀላ ላይ ማውራት አልፈልግም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስላለቀስክ ጥሩ ሰው ነህ ማለት አይደለም፡፡ ውስጥህም ስቃይ አለ ማለት አይደለም፡፡ ጉዳዩ ሁሉ ስለማንነት አይደለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የተለያዩ ዘገባዎች የሚያሳዩት ግን በሶሪያ ሕፃናት የጦርነት ሰለባ መሆናቸውን፣ ተስፋ ማጣታቸውን፣ በጦርነት ውስጥ ተወልደው ጦርነት እያዩ ያደጉ መኖራቸውን ነው፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...