Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዓይን አልጠግብ ጆሮ አልሞላ አሉ?

እነሆ መንገድ። ከሜክሲኮ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። መካሪና ተመካሪው በተደበላለቀበት ጎዳና እየተደናበርን እንጓዛለን። ማን በፍቅር? ማን በንቀት? ማን በማናለብኝነት? ማን በትዕቢት? ማን በሞኝነት? መሬቱን እንደሚደበድብ አልጠራልን ብሏል። ነገን በርቀት አሻግሮ ያየ አስተዋይ ሲመክር አድኃሪ፣ ትናንትን በቁጭት አስታዋሽ ሲሸልል ተራማጅ መባሉ ቀጥሏል። በዚያ በኩል ምዕራባውያን የፊልሞቻቸው ማጣፈጫ ቅመም ብቻ ያደረጓቸው፣ በታሪካቸው ደግመው የሚከሰቱባቸው ተላላፊ በሽታዎች እኛ እዚህ ‹ላይቭ› የምናየው የሞት የሽረት ፍልሚያ ሆኗል። በሌላ በኩል አሁንም አንደኛው ዓለም በትካዜና በአስተማሪነታቸው የሚያስታውሳቸው የሰው ልጅ ሰይጣናዊ ባህሪዎች፣ እኛ ዘንድ የባንዳና የአገር ወዳድ መፈራረጃ ነጥብ ሆነዋል። ታክሲያችን ዛሬም ያላቅሟ ከታሪኳ መማር ያቃታቸውን ችኩል ቀንድ ነካሾችን፣ የሰከኑ አርቆ አሳቢዎችን፣ በነፈሰው የሚነፍሱትንና ግራ የተጋቡትን ተሸክማ እንደምታኖረው አገራችን በዓይነት በዓይነት አሰባጥራ አሳፍራናለች።

ከሾፌሩ አጠገብ የተሰየመ ወጣት ተሳፋሪ ሾፌሩን ቀና ብሎ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቸኳይ መልዕክት በፌስቡክ ላስተላልፍ ስለሆነ አንዴ ሙዚቃውን ብትቀንሰው?›› ይለዋል። ‹‹ጉድ ነው ዘንድሮ። ይኼ ፌስቡክ የሚባል ልክ የሌለው ዓለም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የቤተ መንግሥት ባለቤት አድርጎን ሁላችንም የማናየው ዓለም ገዥ ሆንን፤›› ይላል ከጎኑ የተሰየመ ሸበቶ ጎልማሳ። ‹‹እኔ የምፈራው ወደፊት በልጆቻችን ዘመን ከአራት ኪሎ ሳይሆን ከፌስቡክ ቤተ መንግሥታቸው ውጡልን የምንላቸው ገዥዎች እንዳይፈጠሩ ነው፤›› አለች ከሾፈሩ ጀርባ የተሰየመች ቀዘባ። ከጎኗ የተሰየመ ኮስመን ያለ ወጣት ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ድሮ ድሮ የሃሪ ፖተር አንድ ገፀ ባህሪ በመጥረጊያ እንደ አውሮፕላን ሲበር እንደ ተረት ቆጥሬው እዝናና ነበር። የዘንድሮ አልባሰም በፌስቡክ አካውንት አዳሜ በስለት አልባ ሻሞላ የሚጨፋጨፈው?›› ብሎ ዓይን ዓይኗን ሲያይ መነጽሯን ከቦርሳዋ አውጥታ ዓይኗን ከለለችው። ዓይን ጠገብኩ ቢል ዘንድሮ እጅ እጅ በሚሉ ኮሜንቶች ንባብ ታውረን ነበር እኮ!

ታክሲያችን በዝግታ እየተጓዘች ነው። እኛ ግን በዝግታ እያሰብንም እየተሳሰብንም ያለን አንመስልም። መሀል መቀመጫ የተሰየመች ለግላጋ ልጃገረድ በጉቺ መነጽሯ አጋዥነት አልያችሁ ካለችን ቆንጆ አጠገብ የተሰየመውን ቀትረ ቀላል ወጣት ትከሻውን ወዘወዘችው። ዞረ። ‹‹አንዴ ልየው እሱን መጽሐፍ?›› በዓይኗም በአንደበቷም ተለማመጠችው። ‹‹ይቻላል! የማይቻል ነገር የለም። ብቻ አንብበሽ ስትጨርሺው የተቃውሞ ምልክት ማሳየት አይፈቀድም፤›› አላት። ‹‹የጀመረ ሁሉ ይጨርሳል እንዴ?›› ስትለው፣ ‹‹አይ አንዳንዶች ሐሳብ አያስጨርሱም፡፡ እነሱም ተናግረው ሳይጨርሱ የሚቃወሙ አሉ፤›› አላት። ‹‹ምንድነው የፖለቲካ መጸሐፍ ነው እንዴ?›› ብሎ ይኼን ጊዜ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ግራ የገባው ቢጤ ጣልቃ ገባባቸው። ‹‹የለም የሃሪ ፖተር ቀጣይ ክፍል ነው፤›› ስትለው፣ ‹‹ልጅት ማየት ይቻላል?›› እያለ እጁን ዘረጋ። ‹‹ልየውና ታየዋለህ። አውቀሃል ግን? በእንግሊዝኛ ነው የተጻፈው . . .›› ስትለው ሽራፊ ፈገግታ በመንደሪን ሜሮን የወዛ ከመሰለው ከንፈሯ ላይ ሲጨፍር አያለሁ።

ያም ሳቅ ብሎ፣ ‹‹አይዞሽ ለእሱ አታስቢ። እንኳን እዚህ ማንም ሳያየንና ሳይሰማን ይኼው አታይም በታላላቅ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ ሳይቀር በድፍረት እናንበልብለዋለን። ወይ እማማ ኢትዮጵያ?›› ብሎ ለብቻው ሌላ ሐሳብ ውስጥ ሲገባ ጨዋታው ቢጥም ባይገጥም ሆኗል። ‹‹እኔማ አሁን አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ ነው የተባለ ግለሰብ እንኳን አገር ራሱን ወክሎ ቃለ መጠይቅ አደረገ ሲባል ስሰማ ሰውነቴ መራድ ጉልበቴ መንቀጥቀጥ ጀምሯል። ኧበበበበ . . . እያሉ መንተባተብ. . . ኧረ ወዲያ. . .›› ብላ መጨረሻ ወንበር ጥጓን ይዛ የተሰየመች ወይዘሮ አበደች። ‹‹አንቺ እንግሊዝኛውን ትያለሽ እኛ በአማርኛ መግባባት አቅቶናል፤›› ሲላት የምሰማው አጠገቤ የተሰየመ ፂማም ጎልማሳ ነው። ጆሮ የማይሰማው የለ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ሾፌራችን በቀርፋፋው ወያላ እየተብሰለሰለ፣ ‹‹ምናለበት ቶሎ ቶሎ ሒሳብ ብትሰበስብ? ደመናና ገንዘብ እኮ ቆሞ አይጠብቅህም፤›› ይለዋል። ወያላው አርፎ ሥራውን እንደ መሥራት፣ ‹‹እሱ ካለ አብሽር፣ ተጠልለህም ዝናብ ተኝተህም ወርቅ ይዘንባል፤›› ብሎ መለሰ። ‹‹እሰይ! ያንተ ተሻለ። የት ይሆን አገርህ ያንተ? ይኼው እኛማ  ተኝተን ወርቅና ወረቱን አዘረፍነው፤›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ ጨዋታ ነው። ሩጫ እንጂ ጨዋታ በረዥሙ ስንጫወት አያምርብንም። አሁን እስኪ አበሌን አምጡ . . .›› ይል ጀመር። ይኼን ጊዜ የዚያች ልጅ የስልክ ጥሪ በፈረንጅ ሙዚቃ አበደ። ‹‹ሄሎ!›› አለች ስልኳን አንስታ። በዝምታ ተሸብበው ሁላችንን በአንክሮ ሲመለከቱ የቆዩ አዛውንት ከመጨረሻው ረድፍ፣ ‹‹አሁን ባህሩ ቃኜ እያለ፣ ካሳ ተሰማ እያለ፣ አስናቀች ወርቁ በተወለደችበት አገር የባዕድ ሙዚቃ የስልክ መጥሪያ ማድረግ ምን ይባላል?›› አሉ።

‹‹አባት ዓለም እኮ ዛሬ አንድ ሆናለች። አስናቀችም ባህሩም ዛሬ የዓለም ናቸው እንጂ የብቻችን አይደሉም፤›› ሲላቸው አንዱ ተቅለብልቦ፣ ‹‹ዝም አበል። እናንተ የዛሬ ልጆች ሙያ አድርጋችሁ የያዛችሁት ከሰው አፍ እየነጠቃችሁ መልስ መስጠት ሆኗል። ቀኝ ሲሏችሁ ግራ ግራ ሲሏችሁ ቀኝ። ስፉ ሰትባሉ እንጠባለን። ጥበቡ ስትባሉ እንሰፋለን። ምንድነው እንዲህ ተቃርኖ ሃይማኖታችሁ የሆነው?›› ብለው ጮሁበት። ይኼኔ ወያላው ፌስታል ይዞ አዛውንቱ ጋ ደርሷል። ‹‹ምንድነው?›› አሉት ግራ ተጋብተው። ‹‹ራሴን ከኮሌራ ማነው ከአተት ለመከላከል በማደርገው ጥንቃቄ ገንዘብ እጅ በእጅ መቀበል ትቻለሁ፡፡ የፌስታሉ ትርጉም ያ ነው፤›› ቢላቸው፣ ‹‹እህሉ ጨው ሲሆን ውኃው ደረት ሲፍቅ፣ የአንቺን ሆድ እንጃልሽ የእኔ አዲስ አይናፍቅ አለ ባህሩ ቃኜ. . .›› ብለው ሦስት ብር ወደ ፌስታሉ ሆድ ወረወሩ። አደራ መልሱን በጉሉኮስ እንዳትልከው ያለው ተሳፋሪ ማን ነበር?

ታክሲያችን ይዛን እየነጎደች ነው። ወያላችን እየተጠየፈ ሳንቲማችንን ይወረውርልናል። ‹‹ቆይ ግን ኮሌራ ነው አተት ነው እየረፈረፈን ያለው?›› ብላ ቆንጂት ትጠይቃለች። ‹‹እስካሁን ተተኩሶበት እንጂ ታሞ የሞተ ሰው አላውቅም፤›› ይላታል አጠገቧ የተሰየመው ወጣት። ‹‹አሁን እስኪ ኮሌራና ጥይትን ምን ያገናኛቸዋል?›› ጠየቀ ፂማሙ ጎልማሳ። ‹‹ወንድሜ ካገናኘኸው የማይገናኝ ነገር የለም። እንኳን ይኼ ሰማይና ምድርም በሩቁ ሲያዩዋቸው የተጨባበጡ ናቸው፤›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ቆይ ግን መንግሥት አድማ ለመበተን ለምን ጭስ አልተጠቀመም?›› ብሎ ጋቢና የተሰየመው ጠየቀ። ‹‹በጭስ ተደብቆ የሚኖርን ትውልድ ይመስልሃል እንዲህ በቀላሉ በአስለቃሽ ጭስ የምትበትነው? መሪዎቻችን አይታያቸው እንጂ እኮ ከከባቢ አየር ብክለቱ ይልቅ ይቺን አገር የሚያሠጋት ያለመደማመጥ ብክለት ነው፤›› ይላል መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ወጣት ጣራ እስኪቀደድ ጮክ ብሎ።

‹‹ኧረ እባካችሁ እናንተ ልጆች አትዘባርቁ። ምናለባት መጀመርያ የጀመራችሁትን ወሬ ብትጨርሱ?›› ብለው አዛውንቱ ሲቆጡ፣ ‹‹ሳንሱር ዞራ ዞራ ታክሲም ውስጥ ገባች። ይብላኝ ለእነሱ እንጂ እኛስ ፌስቡክን ቢዘጉት ታክሲ ውስጥ እንዘባርቃለን . . .›› አለ ጋቢና የተሰየመው ጎልማሳ። ‹‹ደግሞ እንዲህ እያላችሁ የእንጀራ ገመዳችንን በጥሱት፤›› ሲለው ሾፌሩ፣ ‹‹እንጀራ እየበላህ እንደሆነ በምን እርግጠኛ ነህ?›› አለው መልሶ፡፡ ‹‹ምን ማለት ነው?›› ሲለው፣ ‹‹ሳጋቱራ በጄሶ ያሽሞነሞኑ እንጀራ በአይጥ ዱለት ስልቅጥ አድርገህ አለመብላትህን በምን እርግጠኛ ነህ? ሌሎቻችሁስ?›› ሲል፣ ‹‹ኧረ በቃ ዝም በል። እስከ ዘመን መለወጫ የሰለቀጥነውን ሊያራግፈው ነው እንዴ?›› እየተባባሉ ተሳፋሪዎች ተንጫጩ። አስቡት እንግዲህ ይህቺም ኑሮ ተብላ በጭስ፣ በጥይት፣ በጄሶና በሳጋቱራ ስንጉላላ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላችንና ሾፌራችን እርስ በእርስ መነቋቆር ጀምረዋል። ‹‹ኧረ በገላጋይ. . .›› ብሎ አንዱ መሀላቸው ሲገባ ወያላው ወደ ገላጋዩ ዞሮ ለፀብ ተጋበዘ። ‹‹ከብሔር ጠባብነትና ትምክህተኝነት ወርደን ወርደን ደግሞ እኔነት ጀመርን?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ወትሮስ እኔነት መስሎኝ የሚያጠበንና የሚያስታብየን፤›› አለው። ‹‹ወይ ኢቢሲ፡፡ የማያስተምረን ነገር የለም እኮ?›› አለች ከወጣቶቹ መሀል አንዷ። ‹‹ምን ማስተማር ብቻ? ዘንድሮ እኮ ቀንደኛ ሠልፈኛና ተቃዋሚው ኢቢሲ ሆኗል። ይኼ ራሱ ትልቅ ማሻሻያ ነው፤›› ብሎ ጎልማሳው የተሳፋሪዎችን አፍ አስከፈተ። ‹‹ደግሞ ምን አየህ?›› ሲለው አንዱ፣ ‹‹እንዴት ምን አየህ ይባላል?›› አታዩም እንዴ ሰሞኑን የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ከደበቀበት እያወጣ አደራ ተረካቢዎቹን ላይ ሲያስመሰክርባቸው። ሰውየውና ሰዎቹ የሰማይና የምድር እንደሚራራቁ፣ ሰው ከሞት ተመልሶ መምጣት ቢችል ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በተኳቸው ሰዎች ምን ያህል ሊያዝኑ እንደሚችሉ፣ በሕዝቡ ታጋሽነትና ዴሞክራሲ ናፋቂነት ግን እንደሚደሰቱ ዝም ብላችሁ አልታዘባችሁም? ‹ልማትንና ዴሞክራሲን መነጣጠል የምርጫ ጉዳይ አይደለም፣ የህልውና ጉዳይ ነው› ያሉትን ስሙና ፍረዱኝ. . .›› ሲል በዚያም በዚህም ሹክሹክታው ደራ። ዘንድሮ ዓይን አልጠግብ ጆሮ አልሞላ ብሎ ዘንድሮ ይኼው በተቃርኖ ወሬ አገር ምድሩ ተደበላልቋል። ጊዜ እስኪያጠራው ማዝገም ነዋ። ወያላው ‹መጨረሻ› ብሏል። መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት