Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያ በፖለቲካ መንታ መንገድ

ኢትዮጵያ በፖለቲካ መንታ መንገድ

ቀን:

በአይተን ጂ.

የኢሕአዴግ መንግሥት አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ታይቶ የማያውቅ በሚመስል ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች ተከታታይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ  የተቀሰቀሱት የተቃውሞ ሠልፎች ምንም እንኳን ማስተር ፕላኑ በመንግሥት የተሰረዘ ቢሆንም አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የወልቃይትን የማንነት/የአስተዳደር ጥያቄ መነሻ በማድረግ ተከታታይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በአማራ ክልል እየተደረጉ ናቸው፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰዱ ዕርምጃዎችና ከተቃውሞ ሠልፎቹና እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ሁከትና ብጥብጦች የአገሪቱ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ብዙዎች ለእስር ተዳርገዋል፣ ለድብደባና ለአካል መጉደል ተጋልጠዋል፣ ቤት ንብረታቸውም ወድሟል፡፡ የተቃውሞው እንቅስቃሴዎቹን ለማቀጣጠልም ሆነ ለማብረድ በሁሉም ወገኖች አሁን የሚወሰዱ ዕርምጃዎችና ቀጣይ ውሳኔዎች የአገሪቱን ዕጣ ፋንታና የዜጎቿን መፃኢ ዕድል በበጎም ሆነ በመጥፎ የመወሰን ዕድል የሚኖራቸው ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ነው ይኼንን ጽሑፍ ኢትዮጵያ በፖለቲካ መንታ መንገድ የሚል አርዕስት የሰጠሁት፡፡

አዲስ ትውልድ – የከረመ ፍረጃ

የተቃውሞዎቹ መነሻ ምክንያቶችን በሚመለከት ብዙዎች ጽፈዋል፣ ተንትነዋል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም በአንድ በኩል ተቃውሞው ሕጋዊና ተገቢ እንደሆነና በዋነኝነት መልካም አስተዳደርን ባለማስፈኑና ሙስናን በአግባቡ ባለመዋጋቱ ምክንያት በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ እንደተፈጠረ በተደጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡ ሥርዓቱ ጠያቂ ትውልድ በመፍጠሩና በወጣቱ ዘንድ የፖለቲካ ንቃት በማደጉ ነው ይለኛል፡፡ በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙ ፀረ ሰላም ኃይሎችና በሽብርተኛነት የተፈረጁ ጠባብና ትምክህተኛ ኃይሎች በሻዕቢያ መንግሥት አሰማሪነት የፈጠሩት ነው ሲል ይደመጣል፡፡ ይኼ ፍረጃ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ መሠረታዊ ልዩነት አለኝ የሚላቸው በአገሪቱ ያሉ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችና አስተሳሰቦችን፣ አንዳንዴም በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የራሱ አባላትን ጭምር ለማጥላላት የሚጠቀምባቸው ታፔላዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ ኢሕአዴግ ገነባሁት በሚለው የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የተቀበለና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በሕገ መንግሥት ባረጋገጠ ሥርዓት ውስጥ፣ ሁለቱንም አስተሳሰቦች በሕጋዊ መንገድ አቅርቦ መታገል ሕገ መንግሥታዊ መብት እንጂ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የሚያስችል ሕጋዊ አግባብ የለም፡፡

በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት ወጣቶች ናቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 60 በመቶው ከ30 ዓመት በታች የሚሆኑ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በኢሕአዴግ ዘመን የተወለዱ፣ ነፍስ ያወቁ፣ የተማሩና የጎረመሱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የፖለቲካ ንቃታቸውና አስተሳሰባቸው ከዚህ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ነው፡፡  ትውልዱ በዕለት ተዕለት ኑሮው የሚያጋጥመውን የሥራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ ጥያቄዎች ባቀረበ ቁጥር የከረሙ ፍረጃዎችን መለጠፍ ትውልዱን የተናቀ እንዲመስለው ከማድረግ የዘለለ ሚና አይኖረውም፡፡ እነዚህን አስተሳሰቦችም አምኖ ለተቀበለው ዜጋም ቢሆን ሐሳቦቹን በሐሳብና በፖለቲካ ትግል ለማሸነፍ መሞከር እንጂ፣ ዘለፋና ፍረጃ መደጋገም ጭራሽ ጽንፈኝነትን ያባብስ እንደሆነ እንጂ በምንም ተዓምር ብሔራዊ መግባባትን አይፈጥርም፡፡

የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ – ‘ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው’

ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን የበለጠ ያጠበቡ ሕጎችንና ዕርምጃዎችን በመውሰድ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአገሪቱን የፓርላማ መቀመጫ መቶ በመቶ በመቆጣጠር ደካማ፣ ተፅዕኖ መፍጠር የማይችሉና በመዝናኛና በስፖርት ወሬዎች የተሞሉ ሚዲያዎችን፣ የተዳከሙ የሲቪል ማኅበራትንና እዚህ ግባ የሚባል ሚና የማይጫወቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ በአገሪቱ ጉዳይ ራሱን ብቸኛ አሳቢና ፈጻሚ አድርጓል፡፡ ከወዳጅ መንግሥታት፣ ከምሁራንና ከራሱ የቀድሞ አባላትና አመራሮች ጭምር ይህ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይሠራና አገሪቱንም ወደ ከፋ አለመረጋጋት ሊያደርሳት እንደሚችል፣ የሌሎች አገሮችን ልምድ ጭምር በማንሳት ሲወተውቱና ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ምርጫውን በዝረራ ባሸነፈ በማግሥቱ ከተነሱት ተቃውሞዎች ውጪ ማብራሪያ ማስፈለግ አልነበረበትም፡፡ በአገሪቱ ያሉ መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ በትንሹ እንኳን ክፍት ቢሆን አሁን እየያዙ ካለው ጽንፈኝነትና ኢ-ምክንያታዊነት መዳን ይችሉ ነበር፡፡ ዜጎች በየጓዳው የሚያነሷቸው የፖለቲካ ጥያቄዎች በግልጽ ተቀምጠው ክርክር አይደረግባቸውም፡፡ ለምሳሌ በተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹ ላይ ገኖ የወጣው አንዱ የፖለቲካ ጥያቄ  የሕወሓት የበላይነት ጥያቄ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በራሱ በድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ጭምር ጠርቶ አለመውጣቱ፣ እንኳን በሕዝቡ ውስጥ በድርጅቱ ውስጥ እንኳን መተማመኛ እንዳልተደረሰበት በተቃውሞዎቹ ግልጽ ሆኗል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ ያለውን የአንድ ብሔር የበላይነት አለ የሚለው አመለካከት ያለቅጥ ተራግቦ ሳለ፣ በኢሕአዴግ ዘንድ ከተለመደው ፍረጃና ማጥላላት ውጪ ሐሳቡን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲከላከል አይታይም፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ጉዳዩ እንዳለ እንኳን ለመቀበል የሚፈልግ አይመስልም፡፡

ምክንያታዊ ውይይትና ክርክር ሲጠፋ አሉባልታና የፈጠራ ወሬዎች ያለምንም ማረጋገጫ እንደ እውነት ይወሰዳሉ፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ጽንፈኛና በስሜት የተሞሉ አስተሳሰቦች ምንም ሳይፈተኑና ሳይጣሩ በብዙ ሰዎች ዘንድ ይደርሳሉ፡፡ ይኼንን መዋጋት የሚቻለው ግልጽነትን በማስፈን፣ በብሔር ላይ የተመሠረቱ የጥቅምና የሙስና ትስስሮችን በመዋጋት፣ እንዲሁም ሚዲያው ሁኔታውን በግልጽ በማንሳት በማስረጃ በማስደገፍ ለማወያየት በመሞከር ነው፡፡ ኢሕአዴግ/መንግሥት የፖለቲካና ምክንያታዊነት ምኅዳሩን ያለቅጥ በማጥበብና የመንግሥት ሚዲያንም ለፕሮፓጋንዳ ሥራ በማዋል ኅብረተሰቡን ወይም በሶሻል ሚዲያ ያለምንም ተቆጣጣሪና ኃላፊነት ለሚተላለፉ መረጃዎች፣ አልያም በውጭ ላሉ ጽንፈኛ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች ዳርገውታል፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያው – ኢሕአዴግና መንግሥት የተሸነፉበት አውድማ  

በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በተለይም እንደኛ የሚስጥራዊነትና የቁጥጥር አስተዳደር መመሥረት ለሚፈልጉ መንግሥታት የዘመኑ ትልቁ ፈተና ቴክኖሎጂው የፈጠረው ማኅበራዊ ሚዲያ ይመስለኛል፡፡ በእኛ አገር እንደተደረገው አሳሪ ሕጎችን በማውጣት፣ ለነፃ ሚዲያ ምቹ ሁኔታን በመንፈግና ሚዲያው እውነተኛ ሕገ መንግሥታዊ ሚናውን እንዳይጫወት በማድረግ ሕዝብን ስብከት መሰል የልማት ወሬ የሚያወሩ የመንግሥት ሚዲያዎችን እንዲሰማ በማድረግ በአገሪቱ የሚናፈሰውን መረጃና የተለያየ አስተሳሰብ መቆጣጠር ይቻላል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት የማኅበራዊ ሚዲያ መፈጠር ይኼንን አስተሳሰብ ምናልባትም ከመሠረቱ ለውጦታል፡፡ ማንም ሰው በእጁ በያዘው ሞባይል በመጠቀም መረጃ ይለዋወጣል፣ ሐሳብ ያንሸራሽራል፣ ይከራከራል፡፡ በተቃውሞዎቹ ወቅትም የታየው ይኼው ነው፡፡ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማቋረጥ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም በአገሪቱ ወረዳዎችና የገጠር አካባቢዎች ጭምር የተከናወኑ ነገሮች፣ የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች በፎቶና በቪዲዮ ጭምር ታጅበው በደቂቃዎች ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያው ይለቀቃሉ፡፡

አመለካከትን በበጎም ሆነ በመጥፎ፣ በተለይም በዋኝነት ተጠቃሚ በሆኑ ወጣቶች ዘንድ ለማድረስ ከፍተኛ አቅም ባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ኢሕአዴግና አባላቱ በመንግሥት ሚዲያ ነጋ ጠባ ከሚነገሩ ነገሮች ውጪ፣ እነዚህን አመለካከቶች ለመከላከልና መልስ ለመስጠት ሲጠቀሙበት አይታይም፡፡ ምሁራንና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ምክንያታዊና ለአገሪቱ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳትና በማወያየት አስተሳሰቦችን ለመቅረፅ ሲሞክሩ አይታይም፡፡

መሪ የሌለው ተቃውሞ እስከ መቼ?

በኦሮሚያም ሆነ በአማራ እየተጠሩ ያሉት ተቃውሞዎችና ሠልፎች በማኅበራዊ ሚዲያውና አክቲቪስቶች የሚስተባበሩ ይመስላሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በባህር ዳር ለመውሰድ ከሞከረው የማስተባበር ሚና ባሻገር በአገሪቱ ተመዝግበው እየተንሳቀሱ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞውን የማስተባበርና የመምራት ሚና ሲጫወቱ አይታይም፡፡ በአንዳንድ አገሮች እንደታየውም ሲቪል ማኅበራትና ሌሎች ማኅበረሰባዊ ቡድኖችም ይህንን ሚና ሲጫወቱ አይታዩም፡፡ መንግሥት ለመደራደርና በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ዕርምጃዎች ጥያቄዎቹን ለመመለስ የእውነት ፈቃደኛ ቢሆን እንኳን በተቃውሞ የተነሱ ጥያቄዎችን በደረጃ ዘርዝሮ፣ ለመደራደር የሚችለው የትኛው ቡድንና አካል እንደሆነ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ ተመዝግበን እንንቀሳቀሳለን የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳን የመሪነት ሚናን ሊወስዱ በተቃውሞ እንቅስቃሴው ላይ በቂ ትንታኔ ሳይኖራቸው የተደበቁ ነው የሚመስሉት፡፡ በአንድም በሌላም መንገድ ጥያቄዎቹን ለማስተባበርና ሥርዓት ለማስያዝ ካልተሞከረ መቋጫ ለሌለው አላስፈላጊ መስዕዋትነት ከመዳረጉም ባሻገር፣ ከተቃውሞዎቹ የሚገኘውን የፖለቲካ ትርፍ በማሳጣት ኢሕአዴግ በራሱ ለመሻሻል ቃል ከመግባት ውጪ ተጨባጭ አንድምታ እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡

የመንግሥት ምላሽ – ኃይል ኃይል አሁንም ኃይል

የፌደራል ሥርዓቱ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ጥያቄዎች የሚመልስበት አግባብ በሕገ መንግሥት ተቀምጠው ሳለ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ላለፉት ዓመታት ችግሮችን በፓርቲና በፖለቲካ መስመሮች ለመፍታት በመሞክሩ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሊያገኝ ይገባ የነበረው ልምድና ችሎታን አሳጥቶታል፡፡ በመሠረቱ በዴሞክራሲ መብቶች መረገጥና ዜጎች መብታቸውን በመጠየቃቸው ምክንያት በመታሰራቸውና በመገደላቸው ምክንያት ጫካ ገብቶ በትጥቅ ትግል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ መንግሥት፣ በፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃና ጥንካሬ ዘላቂ ሰላምን ፈጥሬ አገሪቷን አስተዳድራለሁ ብሎ ማሰቡ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ የፖለቲካ ዋጋውም ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

ሕገ መንግሥት ባለበት አገር የፀጥታ ኃይሎች የሚገዙበት የኃይል አጠቃቀም ሕግ ባለበት አገር፣ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ባልታወጀበትና የለየለት ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ማንም በሕገ መንግሥት እገዛለሁ የሚል አገር ዜጎቹን አንዱንም ቢሆን፣ በየመንገዱ መግደል፣ መደብደብ፣ ማሰርና ማሰቃየት የለበትም፡፡ በዚህ ዘመንም እንደዚህ እያደረጉ አይታወቅብኝም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ እነዚህ ሃይ ባይ የሌላቸው ዕርምጃዎች ብሶትን ከመጨመርና በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ቂም ከመፍጠር በዘለለ በማስፈራራት ተቃውሞዎቹን የማስቀረት አቅማቸው አናሳ መሆኑ፣ በኦሮሚያ ማስተር ፕላኑ ከተሰረዘ በኋላ ሠልፎቹ መቀጠላቸውና የፀጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ ዕርምጃ እንደ አንድ ዋና ጥያቄ መነሳቱ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ዜጋ ሕይወት አልፎ አንድም የፀጥታ አባል ተጠያቂ አለመደረጉ ሰብዓዊ መብቶችና ሕገ መንግሥቱ የፖለቲካ ሰነድ ከመሆን ባሻገር ለዜጎች ጥበቃ እንደማያደርጉ በማመላከት ዜጎች በሰላማዊ ትግል ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግ ነው፡፡ 

የጦርነት ነጋሪትና በጦርነት የማይፈታ ጥያቄ

መንግሥት በጉልበቱ በጣም በመተማመን ራሱን ብቻ እያዳመጠ ተቃውሞዎቹን፣ ሕዝቡንና ጥያቄውን ያነሱትን ዜጎች በማይመጥን ሁኔታና በጉልበት ለመመለስ የሚሞክር ከሆነ የትጥቅ ትግልን እንደ መፍትሔ የሚቆጥሩ ዜጎች ቁጥር ይጨምራል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓትና ግንባታና በተቃውሞዎቹ የተነሱት ጥያቄዎች ጦርነትን በማሸነፍ ሊመለሱ እንደማይችሉ የእኛኑ አገርን ጨምሮ በብዙ አገሮች የታየ ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን አገራችን ባለችበት አቋም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደ አማራጭ ከታየ ከዚያ የሚተርፍ አገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥትን ባህሪ እየተረዱና እያወቁ፣ ፈረንጅ አገር የሚገኝ ኮምፒዩተራቸው ላይ ተቀምጠው አሁንም አሁንም ሠልፍ በመጥራትና በለው በለው በማለት የዜጎችን ክቡር ሕይወት አላስፈላጊ በሆነ መንገድ እንዲጠፋ ማድረግ፣ ከመንግሥት ባልተናነሰ ኃላፊነት ማጣት ነው፡፡ ያለምንም ማረጋገጫ ሕዝብን የሚያውክ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ የጥላቻ አመለካካትን መንዛት አገሪቱ ለሁላችንም እንዳትሆን ከማድረግ የዘለለ እርባና እንደሌለው አለመረዳት ግዴለሽነት ነው፡፡

የፖለቲካው መንታ መንገድ

ኢሕአዴግ የሕዝብ ጥያቄና ብሶት መኖሩን እንደሚያምንና በቅርቡ ተሃድሶ መሰል እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ራሱን እንደሚያስተካክል ለሕዝብ ገልጿል፡፡ ይሁንና አሁንም በዝግ ስብሰባና በድርጅታዊ መንገድ፣ እርስ በርስ በመገማገምና ጥቂት ሰዎችን ከሥልጣን በማንሳት ከሕዝብ የተነሳበትን ጥያቄ ለመፍታት የሚሞክር ከሆነ ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጉዳይ ለኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የፌደራል ሥርዓቱ መጎልመስና ከሥርዓቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አግባብ መመለስ ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ነፃና ሕገ መንግሥታዊ ሚናቸውን የሚወጡ የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት መኖር፣ የተለያዩ አመለካከቶችን በግልጽነትና በምክንያታዊነት የሚያንሻራሽሩ ሚዲያዎች መፈጠር፣ ሙስናና በተለያየ መረብ የተሳሰሩ የጥቅም ትስስሮችን መዋጋት ለአገሪቱ ህልውና ወሳኝ ነው፡፡

ስለዚህም ኢሕአዴግ ጉዳዮቹን መመርመር ያለበት ሥርዓቱንና የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብን እየተገበረበት ያለበትን መንገድ በጥልቀት ከማየት ነው እንጂ፣ መልካም አስተዳደር ማስፈንና ሙስናን መዋጋት በሚሉ፣ ቢሳኩ እንኳን መሠረታዊ ችግሮቹን በማይፈቱ ዕርምጃዎች ከሆነ አገሪቱ ምናልባትም አሸናፊ ወደማይኖረው ብጥብጥ የማምራት ዕድሏ የሰፋ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ድርጅቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ‘ራሳችንን መፈተሽና ማስተካከል አለብን’ የሚል ምክር የሚመስል ሐሳብ በመሰንዘር ችግሩን እንደማይፈቱት ይታወቃል፡፡ አገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን የሕዝብ ተቃውሞ ከስሜታዊነትና ከማናለብኝነት ወጥተው አገርና ዜጎችን  ለዘለቄታው በሚጠቅም መልኩ ካልመሩት መንታው መንገድ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስደን እንደሚቻል ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...