(ክፍል አንድ)
በመሓሪ ይፍጠር
የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩትና የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሕወሓት ውስጥ በአንድ በኩል በልማታዊ ዴሞክራሲ ኃይሎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ በትምክህት፣ በጥበትና በኪራይ ሰብሳቢነት ጎራ መካከል በተካሄደው የሐሳብ ፍትጊያ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከሚያቀነቅነው ‹‹አንጃ›› ጋር ተሠልፈውና እንደ ሠራዊት አባል ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ባለመሆናቸው ምክንያት ከሥራቸው የተሰናበቱትን ግለሰብ አንድ ጽሑፍ እንደ ዋዛ አነበብኩ፡፡ በቅፅል ስማቸው ‹‹ጆቤ›› እየተባሉ የሚጠሩት ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈ ደብዳቤ ነው።
በሕወሓት ክፍፍል ወቅት ሕገ መንግሥቱን ተፃርረው በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጭልጥ ብለው ገብተው የነበሩት የእኚሁ ግለሰብ ደብዳቤ ይዘት፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱን የሚፃረረው የሠራዊት ግንባታ ሰነድ ከሥራ ይወገድ›› የሚል ነው። ምንም እንኳን የ‹‹ጆቤ›› ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈ ቢሆንም፣ በደብዳቤያቸው ላይ ‹‹ከሥራ ይወገድ›› በማለት የጠቀሱት ሰነድ ላይ የሰነዘሯቸው ሐሳቦች አሁንም ሰውዬው ከቀደምት አስተሳሰባቸው ያልተላቀቁና የጠቀሱትን መፅሐፍ አዋቂ በመምሰል በውሸት አስተሳሰብ ለማጠብ በመሞከራቸው፣ እንደ ዜጋ ይህን ምላሽ ለመስጠት ብዕሬን ከወረቀት ጋር አዋድጃለሁ።
እርሳቸው እንዳሉትና እኔም መጽሐፉን ፈልጌ እንዳነበብኩት ‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የተሰኘው ሰነድ ባለ 209 ገጽና በብራና ማተሚያ ድርጅት የታተመ ነው። እርሳቸው ከጠቀሷቸው እውነቶች ውስጥ አንዱ ይኸው ጉዳይና ግለሰቡ ባያምኑበትም ‹‹ሠራዊቱ በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥቱ ብቻ መመራት አለበት›› የሚለው አፋዊ ትረካቸው ይመስለኛል። የተቀሩት እሳቤዎች ግን በሐሳብ መንትዮቻቸው ‹‹አወቅክ…አወቅክ…›› ሲባሉ መጽሐፉን በኒዮሊበራል አስተሳሰብ የማጠብ ጥረት ብቻ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ከዚህ እልፍ ሲልም የመከላከያ ሠራዊቱን ከፍተኛ መኮንኖች በውሸት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ አድርጎ የመሳል አባዜንም ያካተተ ነው። እንዲያውም በተሃድሶው መስመር ተጉዘው ውጤታማ በመሆን ላይ ያሉትን ሥርዓቱንና ሠራዊቱን በሚያስገርም ሁኔታ በደርግነት እስከ መፈረጅ ይደርሳል። ይህም ግለሰቡ ዛሬም ቢሆን የተሃድሶው መስመር እንቅፋት ለመሆን መከጀላቸውን የሚያመላክት ይመስለኛል።
ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ‹‹የአገራችን መከላከያ ተቋም ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርጐ መንቀሳቀስ ሲገባው፣ በግላጭ ሕገ መንግሥቱን የመጣስ ክስተቶች እየታዩ ነው›› በማለት ተቋሙን ይከሳሉ። ለክሳቸው ያቀረቡት ማስረጃ ግን የለም። ምናልባት እርሳቸው በደፈናው ‘ውንጀላዬ ካለፈው ደርግ መጣ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠንቀቅ በሉ ከሚለው ጽሑፌ የቀጠለ ነው’ የሚሉን ከሆነ፣ ይህን ጽሑፋቸውን ‹‹ክፍል ሁለት›› ብለው ሊያቀርቡልን በተገባ ነበር። ይህን ግን አላደረጉትም። ያም ሆኖ ግን እርሳቸው ‹‹ደርግ መጣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠንቀቅ በሉ›› ለሚለው ጽሑፋቸው መነሻ የሆናቸው የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በመቐለ ከወጣቶች ጋር ያደረጉት ተሞክሮ የማስተላለፍ ውይይትን ተከትሎ ነው።
ታዲያ በወቅቱ እኔም የ‹‹ጆቤ››ን ሐሳብ ተንተርሼ በኢንተርኔት ላይ የተጫነ ነገር እንዳለ ፈትሼ ነበር። በትግርኛ የተካሄደውን ውይይትም አገኘሁት። ትግርኛ ሁለተኛ ቋንቋዬ በመሆኑም የውይይቱን መንፈስ በሚገባ ተረድቼዋለሁ። የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስን በአካል አላውቃቸውም። አልፎ አልፎ በቴሌቪዥን መስኮት ካልሆነ በስተቀር እርሳቸውን የማግኘት ዕድሉም አላጋጠመኝም። ጡረተኛውን ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትንም በጽሑፋቸው እንጂ በአካል አግኝቻቸው አላውቅም። ሁለቱንም ባገኛቸውና ሐሳባቸው ምን እንደሆነ ብረዳ ጥሩ ነበር። ሆኖም የሚያገናኘን ነገር ባለመኖሩ ‹‹ጆቤ››ንም በጽሑፋቸው፣ ጄኔራል ሳሞራንም በወቅቱ ካስተላለፉት የተሞክሮ ውይይት አንፃር መልዕክቶቻቸውን ለመመልከት ሞክሬያለሁ።
ሆኖም ተሞክሮን ከሚያስተላልፈው ከጄኔራል ሳሞራ ውይይት ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ‹‹ደርግ መጣ›› ሊያስብላቸው ያስቻላቸውን ነገር ማግኘት አልቻልኩም። እናም ‹‹ጆቤን›› ልታዘባቸው የግድ ብሎኛል። ምክንያቱም እርሳቸው እንዳሉት በኤታ ማዦር ሹሙ ንግግር ምክንያት የተጣሰ ሕገ መንግሥትም አላገኘሁም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ‘ወጣቶች አገራዊ ፍቅር እንዲያድርባቸው አንድ ጄኔራል መኮንን ተሞክሮውን ማካፈል አይችልም፣ ስለሚመራው መሥሪያ ቤትም የመናገር መብት የለውም’ የሚል ድንጋጌ ተፅፎ ባለማየቴ ነው። እንዲሁም ‹‹ጆቤ›› ውይይቱን ተከትለው ‘የጄኔራሉ ንግግር ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ነው’ ለማለት የፈለጉበት መንገድ ከራሳቸው የጥላቻ ምናብ ተነስተው መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። እናም በዚያ አስተያየታቸው እኔ በእርሳቸው ቦታ ሆኜ ማፈሬን ልደብቃቸው አልሻም።
ለነገሩ ስለውትድርና ምንም ዓይነት ዕውቀት ባይኖረኝም እንዲሁ ሳስበው ግን አንድ ጄኔራል መኮንን እንደ ዜጋ የሚያቀርባቸው ሐሳቦች እንደምን ሕገ መንግሥቱን ጥሷል ሊያስብል እንደሚችል ግልጽ ሊሆንልኝ አልቻለም። እንዲሁ ዝም ብዬ ስገምት ግን ጄኔራል ሳሞራ ከተራ ታጋይነት እስከ የአንድ አገር ሠራዊት ኤታ ማዦር ሹምነት ድረስ የደረሱ፣ ለዚያውም በአገራችን ታሪክ ለሕዝቦች ባበረከቱት አስተዋፅኦ የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ማግኘት የቻሉ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ይመስሉኛል። ታዲያ በዚህ የሕይወት ጉዟቸው ውስጥ በርካታ ድሎችንና ውጣ ውረዶችን ያሳለፉ፣ ራሳቸውን በየጊዜው በልምድና በትምህርት ያበቁና ዛሬ ላሉበት የኃላፊነት ደረጃ የደረሱ በመሆናቸው የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገመት የሚከብድ አይመስለኝም። እርግጥም ጄኔራል መኮንኑ በኤታ ማዦር ሹምነት እየመሩ ያሉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹አንቱታን›› የተቸረው እንዲሁም በተሰማራባቸው በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ግዳጆች በሕዝባዊነቱ ከበሬታን ያተረፈ ሠራዊትን፣ በሕገ መንግሥቱና በሕዝባዊ ወገንተኝነት እምነቱ ፅናትንና ጀግንነትን እንዲላበስ በማድረግ ብሎም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሠራዊቱን በማዘመን ረገድ እርሳቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው የላቀ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል።
እናም በእኔ እምነት ወጣቶች ከእኚህ እጅግ የካበተ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው ጄኔራል መኮንን ተሞክሮ ያገኙ ዘንድ መጋበዛቸውና እርሳቸውም በውይይቱ ላይ መገኘታቸው ኃጢያቱ ምን እንደሆነ ለማንም የሚገባ አይመስልም። በእኔ እምነት በዚህ ዓይነት ውይይት ላይ እንኳንስ ኤታ ማዦር ሹሙ ቀርቶ፣ ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል አበበም ቢሆኑ ከክፍፍሉ በፊት የነበራቸውን ጤነኛ አመለካከት ለወጣቶች ቢያስረዱ ክፋት ያለው አይመስለኝም። እርግጥ የ‹‹ጆቤ›› ፍላጎት ቀደም ሲል የጠቀስኩትንና አመቺ ነው ተብሎ በታሰበ ወቅት የተሃድሶውን መስመር ማደናቀፍ በመሆኑ፣ በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ውሸትን እየቀመሩ መጻፋቸው ብዙም የሚደንቅ አይመስለኝም።
ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለውን መፅሐፍ ሲያነቡ እርሳቸው በምናባቸው ውስጥ የፈጠሩት የሠራዊቱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊነት በከፊልም ቢሆን መሠረታዊ ችግሩ የት ላይ እንደሆነ እንደተገለጠላቸው ሊነግሩን ሞክረዋል። በእርሳቸው እምነት የችግሩ ምንጭ በሰነዱ ላይ ሠራዊቱ የገዥው ፓርቲ ‹‹የመጨረሻው ምሽግ›› እንዲሆን ወይም ‹‹ቀባሪው እንዳይሆን›› ሆኖ መገንባቱ ነው። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ የሠራዊት አገነባብ መንገድ ለእርሳቸው እንዴት አዲስ እንደሆነባቸው ግልጽ አይደለም፡፡ በየትኛውም አገር ውስጥ ቢሆን የሚሠራበት አካሄድ ነውና።
አንድ አገር የሚከተለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ፊውዳላዊም ይሁን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አሊያም ሊበራል ዴሞክራሲ ወይም ሃይማኖታዊ ወይም ሌላ፣ ሠራዊቱን የሚቀርፀው የሥርዓቱ ነፀብራቅ እንዲሆን አድርጎ ነው። ሊበራል ዴሞክራሲን በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ሠራዊቱ የሚገነባው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም እንደማይሆነው ሁሉ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በሚከተል ሥርዓት ውስጥም ሊበራል ዴሞክራሲን የሚያቀነቅን ሠራዊት ሊገነባ አይችልም። ሃይማኖታዊ በሆኑ ሥርዓቶች ውስጥም ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› የሚል ሴኩላሪዝምን የሚያቀነቅን ሠራዊት ሊገነባ አይችልም። ከዚህ አኳያ አገራችን ውስጥም ሠራዊቱን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም መገንባት የቆመለትን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በፅናት እንዲጠብቅ የሚያደርገው እንጂ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚያጋጨው አይደለም። እናም ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል አበበ በሑፋቸው ላይ ከሰነዱ ጠቅሰው፣ ‹‹እኛ የምንገነባው የመከላከያ ኃይል የአብዮታዊ ዴሞክሪሲያዊ ሥርዓታችን ዘብ ነው ብለን በግልጽና በጥሬው ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው›› የሚለውን አባባል፣ ‹‹ምን ዓይነት እብሪት ነው?›› በማለት የገለጹበትን ጨዋነት የጎደለውን አባባላቸውን ያስተካክሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሌሎች ከመጽሐፉ የጠቀሷቸውንና ‹‹ለምን ሠራዊቱ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለም ይመራል?›› ብለው ለመሞገት ሲሉ ያነሷቸውን ጉዳዩችንም ከዚሁ አኳያ እንደሚያዩዋቸው በመተማመን።
ያም ሆነ ይህ ግን ዕውነታውን ለመረዳት በቅድሚያ ‘ሕገ መንግሥቱ ስለ ሠራዊቱ ምን ይላል?’ ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87 ላይ ‹‹የመከላከያ መርሆዎች›› በሚል ርዕስ ሥር አምስት ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል። እነርሱም የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል፣ የመከላከያ ሠራዊት የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናልና የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል የሚሉ ናቸው። ሕገ መንግሥት ጥቅል ሐሳቦችን የያዘ እንደመሆኑ መጠን በዝርዝር አዋጆችና ደንቦች መደገፉ የግድ ነው። እናም መንግሥት የሠራዊቱን ሕገ መንግሥታዊ ሚና ይበልጥ ለማጠናከር በአዋጅ ቁጥር 27/1988 የመከላከያ ሠራዊቱን አቋቁሟል።
ታዲያ እዚህ ላይ ሳልጠቀስ የማላልፈው ነገር ቢኖር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በአገር ውስጥ ፀጥታ የማስጠበቅ ተግባር የሚሰማራው የችግሩ ሁኔታ ከፖሊስ አቅም በላይ ከሆነ አሊያም ሊሆን ይችላል ተብሎ በመንግሥት በኩል ሲታመንበት ነው። በተለይም ከክልሎች አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ችግር ሲያጋጥምና ክልሉ የፌዴራል መንግሥቱን ድጋፍ ሲጠይቅ ሠራዊቱ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው ይህን ባለመፈጸማቸው ሳቢያ ከሠራዊቱ በጡረታ በመገለላቸው አላውቀውም ካላሉ በስተቀር፣ የሠራዊቱን ሕገ መንግሥታዊ ሚና አስመልክቶ በአዋጅ ቁጥር 395/1995 ድንጋጌ ወጥቷል።
ይህ ድንጋጌ ሠራዊቱ ምን ያህል ሕገ መንግሥቱን ብቻ ተመሥርቶ ተግባሩን እንደሚያከናውን የሚያሳይ ነው። ይኸውም አዋጁ ሠራዊቱ ለሕገ መንግሥቱና ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መከበር ዘብ እንደሚቆም፣ የአገር ሉዓላዊነትን እንደሚያስከብር፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማክበር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች መከታተልና በመንግሥት ሲታዘዝ አደጋውን ለማምከን መሥራት፣ እንዲሁም የተጣለበትን ኃላፊነት በሕግና በሕግ ብቻ የመወጣት ግዴታ ጥሎበታል።
ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ሠራዊቱን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ አድርገው ለመሳል ቢሞክሩም መሬት ላይ ያለው ዕውነታ ግን ይህ አይደለም። ሠራዊቱ ለሕገ መንግሥቱና ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያለው ታማኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰላማዊ ሠልፍ እንደማያደርግና ሌሎች በሚጠሩት ሠልፎችም ላይ እንደማይገኝ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችል፣ በስውርም ይሁን በግልጽ የፖለቲካ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይችል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመቃወምም ይሁን በመደገፍ ቅስቀሳ እንደማያደርግ፣ የመምረጥ መብት ቢኖረውም በግሉም ይሁን የፖለቲካ ፓርቲን ወክሎ ሥልጣን እንደማይዝ፣ እንዲሁም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳማያደርግ በሠራዊቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ገደብ ተጥሎበታል። እንግዲህ እነዚህ ኃላፊነቶች፣ ግዴታዎችና ገደቦች በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱን ተመርኩዘው የሠራዊቱን ተልዕኮዎች በተዘረዘረ መልኩ ለመግለጽ የወጡት አዋጆች፣ ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ አደራና ግዴታ ያሉበት እንጂ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በደፈናው ሠራዊቱን ለመክሰስ ሲሉ ለማለት እንደከጀሉት ሠራዊቱ የሚመራባቸው ሰነዶች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መሆናቸውን የሚያሳዩ አይደሉም።
እናም እነዚህን ሕገ መንግሥታዊና ከሕገ መንግሥቱ መንጭተው የወጡ አዋጆችንና ደንቦችን በሠራዊቱ ውስጥ የማስረፅ (Indoctrinate) ሥራን ለማከናወን በመንግሥት ደረጃ አንድ ሰነድ ተዘጋጅቶ መመርያ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ለዚህም ይመስለኛል ‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለው ሰነድ የሠራዊቱ የግንባታ መመርያ ሆኖ የተዘጋጀው። ታዲያ የሰነዱን አስፈላጊነት በዚህ ደረጃ ከተማመን ዘንዳ፣ አሁን ደግሞ ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል አበበ ይህን ሰነድ ‹‹ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው›› በማለት ወዳነሷቸው ጉዳዩች ላምራ።
ማንኛውም የጡረተኛውን ጄኔራል መኮንን ጽሑፍ ያነበበ ሰው፣ ‹‹የሠራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተሰኘው ሰነድ ሕገ መንግሥቱንና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለውን ርዕዮተ ዓለም በማደባለቅና በማምታት ስለሠራዊት ግንባታ ይዘባርቃል፤›› ከሚለው ኢ-ተዓማኒና አስገራሚ ሐሳብ ጋር መፋጠጡ አይቀርም። እኔም የተሰማኝ እንዲህ ዓይነት ስሜት ነው። ይሁንና በእኔ እምነት የተሃድሶውን መስመር ለማደናቀፍ ሁለት የማይነጣጠሉ ሰነዶችን (ሕገ መንግሥቱንና የሠራዊት ግንባታ ሰነዱን ማለቴ ነው) በግድ ለማለያየትና ሆድና ጀርባ አድርገው ለማቅረብ እያምታቱና እያዘባረቁ ያሉት ‹‹ጆቤ›› ይመስሉኛል። ምክንያቱም የሠራዊት ግንባታው ሰነድ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅና ለመከላከል ሲባል የወጣ የአንድ ተቋም የግንባታ መመርያ እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ሆኖ ስላላገኘሁት ነው።
እርሳቸው ሠራዊቱ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያለውን ውግንና በተመለከተ በመጽሐፉ ገፅ 23 ላይ ‹‹ለአንድ ፓርቲ ዘብ በመሆን መልክ ሊገልጽ ይችላል። ከፓርቲው ውጪ ሆኖም ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመጠበቅ አንፃር ሊገለጽ ይችላል›› የሚለውን አባባል በመውሰድ፣ ሰነዱ ከሕገ መንግሥቱ የሚለይ ለማስመሰል ሞክረዋል። ይሁንና ሆን ብለው ከዚህ ዓረፍተ ነገር በላይ ያለውን ሊጠቅሱት አልፈለጉም። እርሳቸው ከጠቀሷቸው ዓረፍተ ነገሮች ከፍ ብሎ የተመለከተው ጉዳይ የሚያስረዳው፣ የአንድ አገር መከላከያ ኃይል አቅምና ጥንካሬ ሥርዓቱን እንዴት እንደሚከላከል የሚያትት ሲሆን፣ ሥርዓቱ አብዮታዊም ይሁን አድኃሪ እንዴት አድርጎ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ እንደሚችልም የሚያመላክት ነው። ይህ የሠራዊቱ አቅምና ጥንካሬ የሕገ መንግሥቱን ደኅንነት መጠበቅና መከላከል በሚል ሊገለጽ እንደሚችልም ያብራራል። ታዲያ ጡረተኛው ጄኔራል ምን እያሉን ይሆን? እንዲህ ዓይነቱ ቅጥፈትስ ምን ይፈይዳል? ያም ሆነ ይህ እኔ በበኩሌ ሰውዬው የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ መሆናቸውን በተለያዩ ወቅቶች ደጋግመው ስለነገሩን፣ የሚማሩት ነገር ‹‹የሴራ ንድፈ ሐሳብ››ንም (Conspiracy Theory) ያካትታል እንዴ? ብዬ እንዳስብ አድርገውኛል።
‹‹ጆቤ›› በመጽሐፉ ገፅ 25 ላይ፣ ‹‹በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ደኅንነት መከላከል ማለትና የአገር ደኅንነትን መከላከል ማለት በመሠረቱ አንድ ነው ማለት ይቻላል፤›› መባሉንም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን አስመስለው አቅርበዋል። በእኔ እምነት ይህ አስተሳሰባቸው ትክክል አይደለም። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት እችላለሁ። አንደኛው ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በየትኛውም አገር እንደሚደረገው የሠራዊት ግንባታንና አንድን ሥርዓት ለያይቶ ማየት አለመቻሉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ከመጽሐፉ ላይ ቀንጭበው ከመውሰድ ውጪ እርሳቸው ስላነሱት ጽንሰ ሐሳብ በመጽሐፉ ላይ ምን እንደተባለ ሆን ብለው ስለዘለሉት ነው። ሁለቱንም ምክንያቶቼን ዘርዘር አድርገን እንያቸውና ሰውዬው ምን እያሉ እንደሆነ እንመልከት።
በቅድሚያ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አገርን የሚመራው በሕዝብ የተመረጠ ገዥ ፓርቲና እርሱ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። እናም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አገሪቱን እየመራ ያለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም እንጂ፣ የኒዮ ሊበራል ሥርዓት ቀኖና አይደለም። ሥርዓቱ የሚመራበት ርዕዮተ ዓለምና የሠራዊት ግንባታ አንድ በመሆናቸውም፣ የአገር ደኅንነት የሚጠበቀው ይህንኑ ርዕዮተ ዓለም በሚያራምደው አካል መሆኑ ግልጽ ይመስለኛል። ይህም አገርን መጠበቅ ማለትና ሥርዓቱን መጠበቅ ማለት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ግን ‹‹ጆቤ›› እንደሚሉት ሠራዊቱ በሥርዓቱ ርዕዮተ ዓለም ስለተገነባ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጣረሳል ማለት አይደለም። ሌላ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተወዳድሮና አሸንፎ የሚመጣ አካል ካለም፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተፃርሮ እስካልቆመ ድረስ እርሱኑ መጠበቁ የሚቀር አይመስለኝም። እናም ጉዳዩን አጣሞ ለማቅረብ ካልተፈለገ በስተቀር ሀቁ ይኸው ነው። ውድ አንባቢያን ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ሰነዱን አስመልክተው ያነሷቸውን ሌሎች ጉዳዩችን በቀጣዩ ክፍል ጽሑፌ እመለስበታለሁ።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡