Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአለ በፊልም ሁለተኛ ዲግሪ የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች ያስመርቃል

አለ በፊልም ሁለተኛ ዲግሪ የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች ያስመርቃል

ቀን:

አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የመጀመሪያዎቹን የፊልም ፕሮዳክሽንና ፋይን አርትስ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ዘንድሮ ያስመርቃል፡፡ ተማሪዎቹ የትምህርት ክፍሎቹ ከሁለት ዓመታት በፊት በይፋ ትምህርት መስጠት ሲጀምሩ የተመዘገቡ ሲሆኑ፣ በፊልም ፕሮዳክሽን 17 በፋይን አርትስ ስምንት ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ ምርቃቱን በማስመልከትም የእነዚህ ተመራቂዎች እንዲሁም በትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ዲግሪ የኪነ ቅርጽ፣ የኪነ ቅብና የኪነ ህትመት ተመራቂዎች ሥራዎችን ያካተተ ዐውደ ርዕይ ይካሄዳል፡፡

ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ 30 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ የሚያስመርቅ ሲሆን፣ ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚካሄደው የዘንድሮ ተመራቂዎችም የመመረቂያ ሥራዎቻቸውን በዐውደ ርዕዩ ያቀርባሉ፡፡ በዘንድሮው ዐውደ ርዕይ የትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ባች የፊልም ፕሮዳክሽን ምሩቃን ሥራዎችም ይካተታሉ፡፡

የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አገኘሁ አዳነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተመራቂዎቹ የተዘጋጁ አጫጭር ፊልሞች ለእይታ ይበቃሉ፡፡ የተመራቂዎቹ ፊልሞች አጫጭር ሲሆኑ፣ አንድ ላይ ይታያሉ፡፡ ታዳሚዎችም የፈለጉትን ያህል ፊልም መመልከት ይችላሉ፡፡

‹‹ከሥነ ጥበብ መግባቢያ ሥልቶች አንዱ የሆነው የሲኒማ ጥበብ ተማሪዎች ፊልሞችን ጨምሮ ትምህርት ቤቱ ከብዙ ትግል በኋላ በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ያስመረቃቸው ተማሪዎች ሥራዎች በዐውደ ርዕዩ ይካተታሉ፡፡ ይህ ለትምህርት ቤቱ ትልቅ ስኬት ነው፤›› በማለት ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

ትምህርት ቤቱ በተለይም በፊልም ፕሮዳክሽን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት መስጠት ሲጀምር ለዘርፉ ግንባር ቀደም እንደመሆኑ ብዙ ተጠብቆበታል፡፡ ለሲኒማው የላቀ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሙያተኞች በማፍራት ረገድ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም በባለሙያዎች ተመልክቷል፡፡ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር እንደሚናገሩት፣ የትምህርት ክፍሎቹ ተመራቂዎች ለሲኒማው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሲኒማ ዘርፍ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ማነቆዎች አንዱ የፊልም ተቋማትና በቂ የተማረ ሰው ኃይል ውስንነት ነው፡፡ የፊልም ታሪኮች ወጥ አለመሆን፣ የድምፅና የምሥል ጥራት ችግሮች፣ የኮፒራይት መብት አለመጠበቅና ሌሎችም በርካታ የሲኒማው ተግዳሮቶች ይነሳሉ፡፡ በዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት የወሰዱ ባለሙያዎች መበራከት ደግሞ በተማረ ሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ይታመናል፡፡  

‹‹በአንድ ጀንበር ለውጥ ባይመጣም ተማሪዎቹ ከአዳዲስ የክውን ጥበባት (ፐርፎማንስ አርት) ንድፈ ሐሳቦች ጋር የሚያስተዋውቃቸው ሥልጠና ወስደዋል፡፡ የዓለም ሲኒማ ከሚገኝበት ቦታ አንፃር የአገሪቱን ሲኒማ አካሄድ የመጠየቅ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ናቸው፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ ሲኒማውን ለማሳደግ ትምህርት ክፍሉ አጋዥ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በእርግጥ የተቋሙ መኖር ብቻውን ሲኒማውን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል ብሎ መደምደም ባይቻልም ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እንደ አንድ ዕርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡  

ተማሪዎቹ በተለያዩ ተጋባዥ ዓለም አቀፍ መምህራንና የፊልም ባለሙያዎች ከመሠልጠናቸው አንፃር ንግድ ተኮር (ኮሜርሻል) ከሆነ ሲኒማ ወጣ ባለ መልኩ ምርምር የታከለባቸው (ኤክስፐርመንታል) ሥራዎች በማቅረብ እንደሚሳተፉም ተስፋ ያደርጋሉ፡፡     

በትምህርት ክፍሎቹ ያስተምሩ ከነበሩ መምህራን አብዛኞቹ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ይህ መምህራኑን ለማግኘት ከነበረው ውጣ ውረድ በተጨማሪ በወጪ ረገድም ትምህርት ቤቱን እንደተፈታተነው ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ተማሪዎቹ የዩኒቨርሲቲውን ክንድ የሚፈታተን ወጪ ወጥቶባቸዋል፡፡ በዘርፉ የዓመታት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ተጋብዘው ተማሪዎቹ ከልምዳቸው እንዲማሩ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ ተመራቂዎቹ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በሥራዎቻቸው ሌሎችንም ያስተምራሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ጥሩ ጥሩ ፊልሞች እንደምናይ አምናለሁ፤›› ይላሉ፡፡

በቀጣይ ትምህርት ቤቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ሥር ካሉ የትምህርት ተቋሞች መምህራንን በመውሰድ በድህረ ምረቃ የትምህርት ክፍሎቹ ሥልጠና እንዲሰጡ የማድረግ ዕቅድ እንዳለውም ያክላሉ፡፡ በክዋኔ (ፐርፎርማንስ) ረገድ ከቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል፣ በድምፅ (ሳውንድ ሥልጠና) የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትና ከኮምፖዚሽንና ኢሜጅ ሜኪንግ ጋር በተያያዘ የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህራንን የማሳተፍ ሐሳብ አለ፡፡ ‹‹የኛው መምህራን የማያስተምሩ ከሆነ በውጭ ባለሙያዎች ብቻ የትምህርት ክፍሎቹን ቀጣይነት ማረጋገጥ አይቻልም፤›› በማለት ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

የትምህርት ቤቱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች ዐውደ ርዕይ ከነሐሴ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን፣ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ዐውደ ርዕዩ ተማሪዎች ከሥነ ጥበቡ ማኅበረሰብ ጋር የሚገናኙበት መድረክ ይሆናል፡፡ ‹‹ሥዕል፣ ሠዓሊና ተመልካቹ ከመገናኘቱ በተጨማሪ የሦስትዮሽ ንግግር ይደረጋል፡፡ ለተማሪዎቻችንም ጥሩ ልምድ ይሆናል፡፡ ዐውደ ርዕዩ የመጨረሻ ትምህርታቸው ማለት ነው፡፡ ተመራቂዎቹ በሥራዎቻቸው ማኅበረሰቡን ይጠይቃሉ፡፡ ማኅበረሰቡም ስለሥራዎቻቸው ይጠይቃቸዋል፤›› ይላሉ፡፡

በዐውደ ርዕዩ የተመራቂዎችን ሥራዎች ከማሳየት ባሻገር በትምህርት ቤቱ ለረጅም ዓመታት ያስተማሩ እውቅ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችና መምህራንም ይሸለማሉ፡፡ መምህራኑ ከሦስት አሠርታት በላይ ያስተማሩና በትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራንም በሙያ ብቃታቸው የተከበሩ መሆናቸውን ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹ለዓመታት በላቀ ሁኔታ ያስተማሩ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች በመሆናቸው እውቅና እንሰጣቸዋለን፡፡ መምህራኑ በህትመት ጥበብ ለረጅም ዓመት ያስተማሩት አብዱልራህማን ሸሪፍ፣ በኪነ ቅርጽና በትምህርት ቤቱ የአስተዳደር ሥራም ብዙ የሠሩት ታደሰ በላይና ለረጅም ዓመታት በትጋት ያስተማሩት ዘሪሁን የትምጌታ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ያላቸውን ትልቅ ቦታ ከግምት በማስገባትም ማመስገን ተገቢ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ለቀደምቶቹ ባለሙያዎች በወጣቶቹ ፊት እውቅና መስጠት ወጣቶችን ለበለጠ ሥራ ለማነሳሳት እንደሚረዳም ይገልጻሉ፡፡ ከመምህራኑ በተጨማሪ ከዘንድሮ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ያመጣው ተማሪ መስፍን ተስፋም ይሸለማል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...