Sunday, April 21, 2024

መሪ የሌለው አመፅ ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳታል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ራስ ተፈሪ መኮንን በ1923 ዓ.ም. ኃይለ ሥላሴ ሆነው ዘውድ በጫኑበት ወቅት በኢትዮጵያ ለማምጣት ካቀዷቸው ነገሮች መካከል ዘመናዊ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያን ነፃነት መጠበቅና ያለማንም ጣልቃ ገብነት አገር መምራት መሠረታዊ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡

በመሆኑም ብዝኃነት በሰፈነባት ግዙፍ አገር የክልል ግዛቶችን በማፍረስ አንድ ማዕከላዊ መንግሥትን መሥርተዋል፡፡ የጣሊያን ወረራ በ1933 ዓ.ም. ከተቀለበሰ በኋላም ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅ አድርገዋል፡፡ ብሔራዊ የጦር ኃይል እንዲመሠረት፣ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት እንዲቀረፅ፣ ዘመናዊ የፋይናንስ ተቋማት፣ የትራንስፖርትና የኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማቶች እንዲዘረጉና እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ፓርላማም በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በኢትዮጵያ ተመሥርቷል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አሠርት ዓመታት አስተዳደር በርካቶች ለኢትዮጵያ የተመኙት መሪ እንደተገኙ ይቆጠር እንደነበር ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የኢትዮጵያን አብዮት አስመልክቶ ‹‹The Ethiopian Revolution፡ War in the Horn of Africa›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፓርላማው የፌዝ እንደነበር፣ በንጉሡ የተሰጡ ውሳኔዎችን ከማፅደቅ ውጭ ሥራ እንዳልነበረው፣ ንጉሡ የፍርድ ቤቶች ውሳኔን እስከ መሻርና በራሳቸውም ሕግ እስከማውጣት የተለጠጠ ሥልጣን እንደነበራቸው የታሪክ መዛግብት ይገልጻሉ፡፡

በንጉሡ አስተዳደር ዘመናዊ አስተዳደር መፈጠሩን፣ በመንግሥት የሚመራ ኢንዱስትሪ፣ የከተማ መስፋፋት፣ የቢሮክራሲ መደራጀት፣ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት መጠናከሩን መካድ እንደማይቻል የታሪክ ባለሙያዎች ያረጋግጣሉ፡፡

ይሁንና በወቅቱ በነበረው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ ዘውዳዊውን ሥርዓት ከመጠየቅ አላገደውም፡፡

የተዛባ የሀብት ክፍፍል በአገሪቱ በስፋት መስተዋሉ፣ የንጉሣዊው ሥርዓት ፍፁም የበላይነት፣ ድርቅ፣ በከተማ የሀብታምና የደሃው የኑሮ ልዩነት በእጅጉ መስፋቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የካምፓስ ሕይወትን ወደ ፖለቲካ መድረክነት እንደቀየረው ይነገራል፡፡

በአንድ በኩል የተማሪዎች የፖለቲካ ክርክር ሲስፋፋ፣ በሌላ በኩል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የገበሬዎች ንቅናቄዎች መስፋፋት ጀመሩ፡፡

በመሬት ግብርና ሽንሸና የተሰቃዩ የባሌ ኦሮሞዎች በጄነራል ዋቆ ጉቱ መሪነት የትጥቅ ትግል መጀመራቸው፣ በተመሳሳይ የጐጃም ገበሬዎች ንቅናቄ፣ እንዲሁም ኤርትራ በፌዴሬሽን ኢትዮጵያን መቀላቀሏ ተጥሶ ከኢትዮጵያ ጋር በኃይል መዋሀዷ ያስቆጣቸው የኤርትራ ወጣቶች በትጥቅ ትግል ዘውዳዊውን ሥርዓት እንደገዘገዙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በስተመጨረሻም በአገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ በረሃብ ያለቁትን ዜጐችና በአጠቃላይ የነበረው ሁኔታን ንጉሡ መደበቃቸው ነገሮች የበለጠ እንዲፋፋሙ አድርጓል፡፡ ይህም የተማሪዎችን ቁጣ እንዲገነፍልና ወደ አዲስ አበባ አደባባዮች እንዲወጡ ይህንንም ተቃውሞ መምህራን፣ የታክሲ ሾፌሮችና የሠራተኛ ማኅበራት መቀላቀላቸው የንጉሡ ዘውዳዊ አገዛዝ ማብቂያ ነጋሪትን ጐስሟል፡፡

ይሁን እንጂ ንጉሡ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ስለሚመጣው አመራር በተማሪዎቹ ንቅናቄ ጭራሽኑ ግምት ተሰጥቶት እንዳልነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ተማሪዎቹ ከፍተኛ የፖለቲካ ንቅናቄ ውስጥ ገቡ እንጂ ግልጽ የሆነ ርዕዮተ ዓለም ያልነደፉ፣ እንዲሁም የተደራጀ መዋቅርም እንዳልነበራቸው ፕሮፌሰር ገብሩ በመጽሐፋቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህ ክፍተት በወቅቱ የተሻለ መዋቅር ለነበረው የጦር ኃይሉ አደረጃጀት የሥልጣን ዕድልን ፈጥሯል፡፡

በመሆኑም የደርጉ ኮሚቴ በተማሪዎች ንቅናቄ የተፋፋመውን ንጉሡን የማውረድ ዘመቻ ጠልፎ ሥልጣን ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡

የግሪኩ ፈላስፋ አርስቶትል የሕዝባዊ አመፅ የመጨረሻ ግብ ዘውዳዊ ሥርዓትን ማስወገድ ወይም በዴሞክራሲያዊ መንግሥታት ግዙፍ ወይም መጠነኛ ለውጥ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ መፍጠር ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል፡፡

የሕዝብ አብዮቶች መነሻ የፖለቲካ ሥርዓቱ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ማየት ሲሳነውና በዜጐች መካከል የሀብት መበላለጥ ሲሰፋ፣ የሀብት ክፍፍሉ ሲዛባ፣ እንዲሁም የጥቂቶች የበላይነት ሲሰፍን ሕዝብ እንደሚነሳና አብዮታዊ አመፅ እንደሚቀጣጠል ይጠቀሳል፡፡

በንጉሡ ዘመን የሆነውም ይኸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአብዮቱ መጨረሻ ሥልጣን ወዳልተፈለገ እጅ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህንን ስህተት ለመቀየር የነበረው ብቸኛ አማራጭም ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡

ወቅታዊው የሕዝብ የተቃውሞ ቅርፅ

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም ከዓመት በፊት በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከዓመት በኋላ በድጋሚ በ2008 ዓ.ም. ኅዳር ወር ላይ አገርሽቷል፡፡ ተመሳሳይ ጥያቄን ያነገበው አመፅ ከቀድሞው ይልቅ ጠንከር ያለ በመሆኑ መንግሥት ያቀደውን ማስተር ፕላን እንዲያጥፍ አስገድዶታል፡፡ መንግሥት ይህንን ማስተር ፕላን በይፋ ማጠፉን ቢገልጽም፣ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ግን እስካሁን ሊበርድ አልቻለም፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ከወልቃይት ማንነትና የመሬት ባለቤትነት ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ ከጐንደር ወደ ባህር ዳር፣ ደባርቅ፣ ደብረ ማርቆስ እንዲሁም የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በመስፋፋት የአማራ ሕዝብ ንቅናቄን እየፈጠረ ይመስላል፡፡ እየተስፋፋ የሚገኘው ተቃውሞ በአዲስ አበባም በመጠኑ እንደታየ ቢገለጽም በሰላማዊ ሠልፉ ለመሳተፍ የሞከሩት ወጣቶች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳልሆኑና ከኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች እንደመጡ መንግሥት ገልጿል፡፡

እየተስፋፋ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወደ ሕዝባዊ አብዮት ሊቀየር የሚችል ቢሆንም፣ የሕዝብ አብዮት ነው ብሎ ለመደምደም እንደሚከብድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የታሪክ ተመራማሪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በገዥው ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ፊት ለፊት የፓርቲው አመራሮችን መታገል ያልፈለጉ ግለሰቦች ወደ ሕዝብ የወረወሩት የተቃውሞ አጀንዳ ነው? ወይስ በትክክል የሕዝብ ተቃውሞ ነው? የሚለውን መርምሮ መለየት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በጊንጪ የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት ይዞታ ተነካ በሚል ሰበብ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተቃውሞ በአንድ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዴት ሊመጣ ቻለ? በተመሳሳይም ከወልቃይት ጥያቄ ወደ መንግሥት ይውረድልን ጥያቄ በአንድ ጊዜ እንዴት ተደረሰ? የሚለው ጥያቄ በመጀመሪያ መመለስ አለበት፤››  ብለዋል፡፡

የበለጠ መረጃ የሚጠይቅ መሆኑን የሚገልጹት የታሪክ ተመራማሪው፣ የሕዝብ አብዮት ምልክቶችን ያሟላል ለማለት እንደሚከብድ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ሶሺዮሎጂስቱ ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ በበኩላቸው፣ መንግሥት በቅርቡ በተደጋጋሚ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ማጠፉ  እንደ ድክመት የቆጠሩ ቡድኖች ዕድሉን ለመጠቀም እየሞከሩ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን በሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት በመንግሥት ሲታጠፍ፣ በአዲስ አበባ የትራፊክ አስተዳደር መመርያ በታክሲ ሾፌሮች አድማ ሲቀለበስ፣ የቅማንት የማንነት ጥያቄ በቅማንት ሕዝብ ተቃውሞ በድጋሚ ሊከለስና የመሳሰሉት ክስተቶችን በተሳሳተ መንገድ መንግሥት ልፍስፍስ እንደሆነ አድርገው የተረዱ ቡድኖች ዕድሉን ለመጠቀም እየሞከሩት ያለ እንቅስቃሴ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ውሳኔዎቹን የወሰነው ሕዝባዊነቱን ለማሳየት ሊሆን ይችላል፡፡ አልያም የተቃውሞ አንቀሳቃሾቹ እንደተረዱት ተልፈስፍሶም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁኔታው ግን በየትኛውም ዓለም ሊከሰት የሚችል ተከስቶ የሚያውቅ ነው፤›› ብለዋል ዶ/ር የራስወርቅ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ልዑልሰገድ ግርማ በበኩላቸው፣ ወቅታዊው የተቃውሞ ሠልፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች የሚጠራ፣ ተዋናዮቹ እነማን እንደሆኑና ዓላማቸው ምን እንደሆነ እንደማይታወቅ ይገልጻሉ፡፡

የተቃውሞው መሪዎች

በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ የተቃውሞ ሠልፎች ሕዝቡ እንዲወጣ ጥሪ እየተደረገ ያለው በማኅበራዊ ድረ ገጾች ነው፡፡ በተመሳሳይ ሰዓትና ቦታ ውስጥ የሌሉ ሰዎች ስሜትን በመጋራት ብቻ የሚቀሰቅሱት እንጂ የሚመሩት አለመሆኑን፣ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ (የዛሚ ሬዲዮ መሥራችና ባለቤት) ይገልጻሉ፡፡

ተቃውሞውን ለማካሄድ በአካል መገኘትን፤ ተቃውሞን ለመምራት አካላዊ ክልከላዎችን ማለፍ፣ አልያም በአካል መገኘትን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዘመን የሻረው በመሆኑ የተፈጠረ መልካም አጋጣሚ የመሆኑን ያህል በተቃራኒውም ክፉ አጋጣሚ ሊባል እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

ክፉ አጋጣሚ ለማለት የሚያስችለውም በአመዛኙ ስሜታዊ በሆኑ ንግግሮች የሚቀሰቀስ እንጂ፣ ክርክር ተደርጐ በነጠረ ሀቅ ላይ የተመሠረተ ተቃውሞ ሊሆን አለመቻሉ ዋነኛው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የማኅበረሰቦችና የመንግሥት ህልውና በክልል የተወሰነ ቢሆንም፣ ክስተቶችን ድንበር ዘለል ሆኖ ከመጋራት ባለፈ ለውጥንም ለማምጣት በዚሁ መስመር መንቀሳቀስ መቻሉ አደጋ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ይገልጻሉ፡፡

ዶ/ር ልዑልሰገድ በበኩላቸው በሙስናና በመንግሥት የአገልግሎት ዘርፎች የተጓተተ አሠራር የተቆጣ ማኅበረሰብ ተቃውሞውን ከማኅበራዊ ሚዲያ ባለፈ አደባባይ ወጥቶ ሊገልጽ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ይህንን የገነፈለ ቁጣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች እየጠለፉት እንጂ፣ መሪና ሌላ ዓላማ ያልነበረው የሕዝብ ቁጣ ነው ብለዋል፡፡

የተቃውሞው መጨረሻ

ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት የታሪክ ተመራማሪ የተደራጀ መሪ የሌለው ተቃውሞ መሪ እስኪያገኝ ሊቀጥል እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ በማከልም የገዥው ፓርቲ ልሂቃን ተቃውሞው ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ መፍትሔ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን በበኩላቸው፣ ተቃውሞው የታቀደ መጨረሻ እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፋይዳ አይኖረውም ማለት እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡

‹‹የመንግሥት መስተካከልን ሊያመጣ ይችላል፤›› የሚሉት አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹ይህ ግን በተቃውሞው ግለት ሳይሆን መሠረታዊ ጥያቄዎቹ ምንድን ናቸው የሚል ጥያቄን በገዥው ፓርቲ ልሂቃን፣ በተቃዋሚዎችና በተራው ሕዝብ ላይም የሚጭር በመሆኑ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ተቃውሞው ቁጣን ለመግለጽ እንጂ ሌላ ነገር አለመሆኑን ነው፡፡

አስከፊ ሁኔታ ተፈጠረ ከተባለ ተቃውሞው አዲስ አበባን ሲይዝ መሆኑን የሚገልጹት የታሪክ ተመራማሪው፣ የሚስተዋሉት ተቃውሞዎች በአመዛኙ ማንነት ተኮር ይዘት ያላቸው በመሆኑ አዲስ አበባን ይቆጣጠራል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ያስረዳሉ፡፡ ይህ ከሆነ ግን ከባድ የሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለተቃውሞው መሪ ለማበጀት በውጭ የሚገኙ ሁለት ቡድኖች መተባበራቸው ይነገራል፡፡ እነዚህም ግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የተባለው የቀድሞው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች የመሠረቱት የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ትብብሩን የመሠረቱት ሁለቱ ቡድኖች በባህሪያቸው የሚስማሙ እንዳልሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

ለዘመናት በሰሜኑ (በአማራውና በትግሬው) የፖለቲካና የባህል የበላይነት የኦሮሞ ሕዝብ ተጨቁኗል በሚል መነሻ ኦነግ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት መታገሉንና ዓላማውም የኦሮሞ ሕዝብን መገንጠል እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በመሆኑም ዋነኛ መሠረቱ የአማራው ሕዝብ በሆነው ግንቦት ሰባት እና በኦዴግ መካከል የተመሠረተው ትብብር ተቃውሞውን ለመምራት ተቀባይነት እንደማይኖረው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ይስማማሉ፡፡

‹‹አህያ በሬ ሆኖ ጅብ ገበሬ ሆኖ የታረሰ መሬት የለም፤›› በማለት አቶ ዘሪሁን ጥምረቱ ወይም ትብብሩ ተቃውሞውን ወደሚፈለግ አቅጣጫ ለመምራት እንደማይሳካለት ገልጸዋል፡፡ ይህ ሊሆን ከቻለ ግን በሶሪያ እየሆነ ካለው የባሰ መበታተን ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡  

በተመሳሳይ የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው፣ ‹‹ጨቋኙ ሥርዓት ያለው እዚህ ነው፡፡ ተጨቋኙም ሕዝብ ያለው እዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ከአትላንቲክ ማዶ ሆኖ የኢትዮጵያን ትግል መምራት ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡ በተለይ በትጥቅ ትግል የሚያምኑና ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተባብረው ለኢትዮጵያ መፍትሔ እናመጣለን የሚሉ ኃይሎች አዳዲስ ችግር ይወልዱ እንደሆነ እንጂ፣ ምንም ዓይነት የተሻለ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፤›› ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

(ለዚህ ዘገባ አሥራት ሥዩም አስተዋጽኦ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -