Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ኢትዮጵያዊ በነበሩ ጊዜ አክሲዮን የገዙ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ገንዘብ መንግሥት ይወርሰዋል ብዬ አላስብም››

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የሕብረት ኢንሹራንስ ቦርድ ሊቀመንበር

በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ፣ በፋይናንስ መስክ ስማቸው ከሚጎላውና በተደጋጋሚ ከሚነሳው ባለሙያዎች እንዲሁም የቢዝነስ ሰዎች መካከል አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ አገሮች ውስጥም አሻራቸውን አኑረዋል፡፡ በናይጄሪያ የነበራቸው የ16 ዓመታት ቆይታ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በግሉ ዘርፍ በተለይም የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን በፕሬዚዳንትነት በመምራትም ይታወቃሉ፡፡ በኃላፊነት ከመሯቸውና ባለአክሲዮን ከሆኑባቸው ውስጥ በይበልጥ የሚታወቁት የሕብረት ባንክና የሕብረት ኢንሹራንስ መሥራች በመሆናቸውም ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት የሕብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በባህሪያቸውም ያመኑበትን ነገር ፊት ለፊት ይናገራሉ፤ ስህተት መስሎ የታያቸውንም እንዲታረም ይሞግታሉ፡፡ በዚህ ባህሪያቸው እንዲስተካከሉ ያደረጓቸው፤ በፍርድ ቤት የረቷቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ባለአክሲዮን ናቸው ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ መመርያ ማውጣቱ፣ አሳድሯል ያሉትን ተፅዕኖ በመንተራስ መንግሥትን መፍትሔ እንዲፈልግ እየተሟገቱት ይገኛሉ፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ ዙሪያ ስለሚነሱ ክፍተቶችና ሌሎችም ጉዳዮች ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በግሉ ዘርፍ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሐሳብ በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ በተለያዩ ርዕሶች ላይም የሚያነሷቸውን ክርክሮች ስንሰማ ቆይተናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጠፍተዋል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ቢዝነስ ነክ ስብሰባዎችን ብዙ ጊዜ የሚያካሂደው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ስብሰባዎች ላይ እንዳልገኝ ታግደሃል ብሎኝ ነበር፡፡ ይህ ትክክል አይደለም ብዬ ፍርድ ቤት ሄድኩ፡፡ ስብሰባ ያለመግባት መብቴ ተመለሰ፡፡ ለነገሩ እነሱም ሥራዬ ብለው አይጠሩኝም፡፡ ብዙዎቹ እንደሚሉት ምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ እንዳልኖርና እንዳልገኝ በተቻለ መጠን በግልጽ ግብዣ እንዳይደርሰኝ ያደርጋል፡፡ ፍርድ ቤት ሄጄ በሕግ ብረታቸውም በድርጊታቸው ግን ከድሮው የለወጡት ነገር የለም፡፡ በእኔ ዕይታ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በፈለገው መልኩ የሚመሩት ምክር ቤት ነው፡፡ እሳቸው እስካሉ ድረስ እኔን ለስብሰባ መጠራት የማይሞከር ነው፡፡ አልፎ አልፎ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ስብሰባ ሲኖር ይጠራኛል፡፡ እገኛለሁ፡፡ ለሁለቱም ቻምበሮች የቀድሞ ፕሬዚዳንት በመሆኔ አንዳንድ ጊዜ ስብሰባ ሲኖር ቢጠሩኝ፤ ቢያማክሩኝ ደስ ይለኛል፡፡ ካልጠሩኝ ግን በግድ ጥሩኝ ብዬ መክሰስ አልችልም፡፡ ስለዚህ በዚህ የተነሳ ልሳተፍባቸው በምፈልጋቸው በርካታ ስብሰባዎች ሁሉ ላይ እንደ ቀድሞው አልገኝም፡፡ አገላለጹ ትክክል ነው፡፡ ጠፍቻለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- አቶ ኢየሱስወርቅ በተለየ የሚታወቁበት አንድ ነገር አለ ይባላል፡፡ ያላመኑበትን ነገር በግልጽ በማቅረብ ከከፋም ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ጭምር ሲከራከሩ ይታያል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ልምድና ባህርይ አሁንም አብሮዎት አለ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- አንዳንድ ጊዜ ይህንን ያልኩ እንደሆነ ምናልባት በዚህ አባባሌ ወይም ይህንን ሐሳብ በመያዜ የማይደሰቱ ይኖራሉ፤ ተፅዕኖ ሊያመጡብኝ ይችላሉ በማለት የሚፈራ ሊኖር ይችላል፡፡ የመንግሥትን ድጋፍ የሚፈልጉ ጥቂቶች ደግሞ ይህቺን በመናገሬ ይቀየሙኝ ይሆናል፤ ቅር ይሰኙ ይሆናል በማለት ብዙ ጊዜ ፈርተው ዝም የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶችም ቁም ነገሩ ሳይታያቸው ቀርቶ ሊሆን ይችላል ዝም የሚሉት፡፡ ስለዚህ ፍራቻ ይታያል፡፡ ወደእኔ ከመጣህ ግን ለራሴ ብቻ በሚለው ፍልስፍና መኖር ካቆምኩ ብዙ ጊዜዬ ነው፡፡ ለራሴ ብቻ ብዬ ሕይወቴን መርቼ አላውቅም፡፡ ጥሩ ነገር ነው ወይም እውነት ነው የሚባል ነገር ሲገጥመኝ በተቻለ መጠን ያንን ጥሩ ነገር ሌሎች እንዲያውቁት ማድረግ፤ ሌሎች እንዲካፈሉኝ የማድረግ ልማድ አለኝ፡፡ አስተሳሰቤ ሙሉ ለሙሉ ትክክል ሊሆን ስለማይችል ሰዎች አዳምጠውኝ እዚህ ጋር እኮ እንደዚህ ነው እንዲሉኝ፣ እንዲያርሙኝ እፈልጋለሁ፡፡ ነገሮችን ምስጢር የማድረግ ልማድ የለኝም፡፡ በተለይ አገር ነክ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን የሚመለከቱ ጉዳዮች በሚኖሩበት ጊዜ፣ ፊት ለፊት አውጥቼ በጉዳዩ ላይ መነጋገር ወደምችልበት ቦታ መሄድ የቆየ ፀባዬ ነው፡፡ እኔ የእውነት ሞኖፖሊ አለኝ አልልም፡፡ ብዬም አላውቅም፡፡ ማለቱም ስህተት ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲገጥመኝ ሐሳቡን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት የተለመደ ፀባዬ ነው፡፡ ለምሳሌ ታስታውስ እንደሆነ የዴቪደንድ ታክስ ጉዳይ ላይ እስከመጨረሻው ድረስ ሄጄበታለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠሩት ስብሰባ ላይ ይህንኑ አንስቼ ብዙ ክርክር፣ ብዙ የጽሑፍ ልውውጥም ተደርጐበታል፡፡ የትርፍ ድርሻ ወይም ዴቪደንድ ሳይኖር የዴቪደንድ ታክስ የሚባል ነገር መኖር የለበትም፡፡ ምናልባት ገንዘቡ ከተፈለገ ሕጉን እንደገና አሻሽሎ በዚያ መሠረት መጠየቅ አይሻልም ወይ? አሁን ባለው ሁኔታ ግን ነገሩ አወዛጋቢ ነው የሚል ሐሳብ ይዤ ብዙ ተከራክሬበታለሁ፡፡ ለብዙ ሰዎችም መፍትሔ ተገኝቷል፡፡ ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ተገኝቷል ባይባልም ብዙውን የንግድ ኅብረተሰብ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ከመክፈል አድኗል፡፡ ይህን ጉዳይ ይዤ የተከራከርኩት ትክክል ስላልመሰለኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ባለአክሲዮኖች ካሉ ሕገወጥ ስለሆኑ አሳውቁ ብሏል፡፡ ይህ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ይህንን ችግር በመመልከት መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ እስቲ ስለጉዳዩ  ይንገሩኝ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ፍርድ ቤት የሚያስኬድ ባይሆንም በዓምናው የሕብረት ኢንሹራንስ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከባለአክሲዮኖች የተነሣውን ጥያቄ በመያዝ ነው ወደዚህ ነገር የገባሁት፡፡ የባአክሲዮኖቹ ጥያቄም የሕብረት ኢንሹራንስ አክሲዮንን ስንገዛ ኢትዮጵያዊ ሆነን ነው የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዘን ነው፡፡ አክሲዮን የገባነውም በኢትዮጵያዊነታችን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ግን 21 ዓመት ሆኖታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮች ተለዋውጠዋል፡፡ አንዳንዶቻችን አክሲዮን ከገዛን በኋላ ዜግነታችንን ለውጠናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እያላቸው ሞተዋል፡፡ ነገር ግን አክሲዮኖቻቸውን በህይወት ላሉ ልጆቻቸው አውርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ወራሾች ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ አሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸው እንዳይንቀሳቀስ፣ በአክሲዮኖቻቸው ያገኙት ትርፍ እንዳይሸጥ ተከልክሏል፡፡ ይህ ምንድን ነው የሚሆነው? መንግሥት ሊወርሰን ነው ወይ? ከዚህ ቀደም ደርግ የወረሰው ሳይበቃ  አሁንም እንደገና ልንወረስ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ አንደኛ  የሕብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ የቦርድ ሰብሳቢ እንደመሆኔ፣ ሁለተኛም እንደ ኢትዮጵያዊነት፣ ባልደረቦቼም በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አስተሳሰብና አቋም አለን፡፡ እኔ ይህንን ነገር አልደግፈውም፡፡ ነገር ግን በሕጉ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

ባንኮችና ኢንሹራንሶች መቶ በመቶ ባለቤትነታቸው በኢትዮጵያውያን መያዝ አለባቸው የሚለው በግልጽ በሕግ ተቀምጧል፡፡ ባለአክሲዮን የሚሆኑት ኩባንያዎችም ከሆኑ ኢትዮጵያውያን መሆን አለባቸው፡፡ ይህ በአዋጅ ወጥቷል፡፡ አዋጁ እስካልተሻረ ድረስ እንዲሻሻል በየጊዜው ከመጠየቅ ውጭ አዋጁን የምንሰብርበት ሌላ መንገድ የለም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በመንግሥት በኩል እንዲታሰብበትና መፍትሔ እንዲፈለግለት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ በበኩሌ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ነገር ግን ኢትዮጵያዊ በነበሩ ጊዜ አክሲዮን የገዙ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ገንዘብ ይወርሰዋል ብዬ በምንም መልኩ አላስብም፡፡ አይሆንምም፡፡ ግን ደግሞ ሕጋዊ መፍትሔ ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብዬ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት የገባሁበት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የመመርያው መውጣት ያስከትላል ባላችሁት ሥጋት ላይ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ተወያይታችኋል? የፋይናንስ ተቋማት ባለቤትነት በኢትዮጵያውያን ዜጎች ብቻ ይሁን መባሉስ እንዴት ይታያል?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- በፋይናንስ ተቋማት ማቋቋሟያ አዋጁ አልተነጋገርንበትም፡፡ ይኼ ሕግ ለባንኮችና ለኢንሹራንስ ድርጅቶች ቀርቦ አልተወያየንበትም፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ በአዲሱ መንግሥት ነፃ ገበያ ተፈቀደ፡፡ ለግሉ ዘርፍ ተዘግቶ የነበረው የፋይናንስ ዘርፍ ኢትዮጵያውያኖች ማቋቋም እንዲችሉና እንዲገቡ ተፈቅዶ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ እንደማስታውሰው በወቅቱ ናይጄሪያ ስለነበርኩ ረቂቁ ተልኮልኝ አይቼው ነበር፡፡ መጀመሪያ የወጣው ሕግ የመከርንበት አልነበረም፡፡ በዚያን ወቅት እነዚህ ተቋማት በኢትዮጵያውያን መያዝ አለባቸው የሚለውን ሐሳብ የምንቃወመውም አልነበረም፡፡ በዚያን ወቅት ማለት ቢቻል ኑሮ ምናልባት ለኢትዮጵያውያን ብቻ በሚለው ላይ ለተወሰነ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ብቻ እንዲያዝ ቀስ በቀስ በኋላ ላይ ግን የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡበት ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል ብዬ ልመክር እችል ነበር፡፡ አሁን ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ዓለም ብዙ ተጉዟል፡፡ ሁሉንም ነገር በአንድ ሌሊት ከመንግሥት ቁጥጥር ማውጣት አያስፈልግህም፡፡ የኢኮኖሚ አውታሮች ግን መከፈታቸው የማይቀር ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ እንግዲህ የዓለም ንግድ ድርጅት ከተቋቋመ ብዙ ዓመታት ሆኖታል፡፡ ኢትዮጵያም አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረበች 14 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንደ ኮሜሳ ባለው ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ መግባትና አንዱ አገር ለሌላው ገበያውን ክፍት ማድረጉ ይጠቅማል በማለት ቀስ በቀስ ወደዚህ ለመግባት መንግሥት እየሞከረ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ የዛሬ 23 ዓመት ለፋይናንስ ተቋማት ሕግ ስታወጣ፣ ኩባንያዎቹ የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ መሆን አለባቸው መባሉ እንደ ስህተት የሚታይ አይደለም፡፡ ከ23 ዓመት በፊት እንደነበረው በዚያው መቆየቱ ግን አደጋ ያስከትላል ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ለዳያስፖራዎችም ሆነ ለውጭ ኩባንያዎች ዘርፉ አለመከፈቱ አደጋ እንደሚያስከትል ሥጋት የሆነብዎ ነገር ለምንድን ነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ዳያስፖራዎች በአጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ስላላቸው የባለቤትነት ድርሻ እርግጠኛ ባልሆንም ከአጠቃላይ ባለአክሲዮኖች አምስት በመቶ አይሞላም፡፡ ኢትዮጵያዊ በነበሩ ጊዜ አክሲዮን ገዝተው ኋላ ላይ ዜግነታቸውን የቀየሩትን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እኛ በተቻለን መጠን ፓስፖርትና መታወቂያ እየጠየቅን ስንሸጥ የቆየነው አንዳንዶች ይህንን አልፈው ሊገቡ ይችላሉ በማለት ብሔራዊ ባንክ ማስጠንቂያ ደብዳቤ እ.ኤ.አ. በ2009 ጽፎ ስለነበር ነው፡፡ ትዝ የሚለኝ የብሔራዊ ባንክን ደብዳቤ ኮፒ አድርገን ለሁሉም ባለአክሲዮኖች መስጠታችን ነው፡፡ በተቻለን መጠንም ስንመክር ቆይተናል፡፡ ነገር ግን ጥቂቶች አክሲዮናቸውን በውርስ ያስተላለፉ፣ የአክሲዮን ባለቤት ከሆኑ በኋላም ዜግነታቸውን የቀየሩ ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገንዝበናል፡፡ ቁጥራቸው ግን በጣም ትንሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በኢንሹንስ ድርጅቶችና በባንኮች ውስጥ የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ካሉ አሳውቁ፣ ለፖሊስ ጠቁሙ ብሏል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ይህንን እያደረጉ ነው? እንዴትስ እያስተናገዳችሁ ነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ሰዎችን በሙሉ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ስጡን ብለናል፡፡ ይህንን ማድረግ ያልቻሉትን አስታውቀናል፡፡ በተለይ ደግሞ እነዚህ ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸው ተዘግተዋል፡፡ ዴቪደንዳቸውም ተዘግቷል፡፡ ማንኛውም ሰው ሲጠይቀን ኢትዮጵያዊነታቸውን አረጋግጠን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ የተወሰኑ የሚጠይቁ ግን አሉ፡፡ ሕጉ ስለማይፈቅድ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ የሆነ ሆኖ በዚህ ችግር ውስጥ የገቡ እንዳሉ አውቀናል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ሐሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የመፍትሔ ሐሳብ ብለው ያቀረቡት ምንድን ነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ሐሳቤን ሳንፀባርቅ የቆየሁት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ እንዲያውም የውጭ ተወላጆችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ መግባት ይኖርባቸዋል የሚለው ቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ብቻቸውን ባንክና ኢንሹራንስ እንዲያቋቁሙ ፈቃድ እንዳይሰጥ ማድረግ ነገር ግን በአገራችን ሕግ በተቋቋሙ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ እነዚህ ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለውን ድርሻ የተወሰነ አድርጐ ወይም ለተወሰነ ዘመን መፍቀዱ ይጠቅማል ብዬ በማሰብ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡    

ሪፖርተር፡- ይህንን ሐሳብዎን የበለጠ ቢያብራሩት? ሐሳብዎንና መሆን አለበት ብለው ያመኑበትን ጉዳይ ለማን አቀረቡ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ለብዙዎች አቅርቤያለሁ፡፡  በመጨረሻ ግን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ነው ያቀረብኩት፡፡ እሳቸውም ጋ ቢሆን ዘልዬ አልሄድኩም፡፡ መጀመሪያ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሄጄ ይህ ነገር ቢታሰብበት ጥሩ ነው፤ ለብዙዎች መፍትሔ ቢሰጥ ጥሩ ነው ብያለሁ፡፡ እንደ እኔ ቢሆን በተወሰነ ደረጃ የውጭ ሰዎች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚገቡበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ነው፡፡ ይግቡ ስልም ሙሉ ለሙሉ መፍቀድ ሳይሆን፣ አሁን ባሉት ባንኮችና ኢንሹራንሶች ውስጥ በተወሰነ ደረጃ አክሲዮን እንዲገዙ ማድረግ ቢችሉ የሚል ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ ለማንኛውም የአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ከ20 ዓመት በላይ ዝግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ይከፈታል ወይም አይከፈትም የሚለው ነጥብ ጥያቄ አይደለም፡፡ ይሄ ጥያቄ ጊዜ አልፎበታል፡፡ መቼ ይከፈታል? እንዴትስ ይከፈታል? የሚለው ነው አሁን ላይ የሚነሳው፡፡ መቼም ቢሆን የውጭ ኩባንያዎች መግባታቸው አይቀርም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጐን ለጐን መታየት ያለበት አንዱ ይሄ ነው፡፡ አገር ውስጥ ላሉት ኩባንያዎች የውድድር ሜዳው መስተካከል አለበት፡፡

አለበለዚያ ድንበር ዘለል ውድድር ውስጥ ከተገባ ለማሸነፍ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ውድድሩ ሜዳም መስተካከል አለበት፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደሚለው ከሆነ ብዙ ትንንሽ ተቋሞች ሳይሆኑ ቁጥራቸው አነስ ያሉ ትልልቅ ተቋሞች እንዲኖሩ ይፈለጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ባንኮችም ሆኑ ኢንሹራንሶች መቀላቀል ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ለእኔም ይሰማኛል፡፡ የተቋማቱ አፈጣጠር የተለያየ በመሆኑም ለማዋሃድ የሚቻለውም ቀድሞ ሥራ ሲሠራ ነው፡፡ አንዳንዱ በብሔር፣ አንዳንዱ በፓርቲ፣ ሌላውም በሃይማኖት የተቋቋመ ስለሆነ አሁን ባለው ሁኔታ መቀላቀል ያስቸግራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለማንኛውም እውነተኛ ውድድር እንዲኖር ለአገር በቀል ገበያ እኩል ሜዳ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ያልተስተካከለ ገበያ ውስጥ ተቀምጠን፤ ከጊዜ በኋላ ኢኮኖሚያችን መከፈቱ ስለማይቀር በሚከፈትበት ጊዜ ደካማ ተቋማት ሆነን የውጭዎቹ በቀላሉ እንደ አርጀንቲናና ፊሊፒንስ ኩባንያዎች እንዳንበላ ሥራው ቀድሞ መጀመር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖችን የተመለከተውን ጥያቄ ይዘው መጀመሪያ የሄዱት ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነውና ከዚያ ምን ምላሽ ተሰጠዎት?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ሐሳቡ ጥሩ ነው፡፡ የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ከእኛ ይልቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የሚመለከተው ነው፡፡ እኛ አስፈጻሚዎች ነን፡፡ እዚያ የዳያስፖራ ክፍል ሄደው ቢያነጋግሩ ይጠቅማል የሚል ምክር ሰጡኝ፡፡ ጊዜ ሳልፈጅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ክፍል ቀጠሮ ጠይቄ በመሄድ ጉዳዩን አወያየኋቸው፡፡ አስረዳሁ፡፡ ይህ ጉዳይ እነሱም ጋ መነሳቱንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለፍትህ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፈዋል፤ ግልባጭም ለብሔራዊ ባንክ ተልኳል አሉኝ፡፡ ምን ተጻፈ ብዬ አልጠይቅም፡፡ ብሔራዊ ባንክ አንድ ምላሽ ይሰጣል ብዬ ጠበቅኩ፡፡ ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. አንድ ደብዳቤ መጣ፡፡ ማሻሻያ የተባለው ደብዳቤ ኩባንያዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የግለሰብ ባለአክሲዮኖች ነው፡፡

ግለሰብ ዳያስፖራዎች አክሲዮን ገዝተዋል፡፡ ድርሻቸውም ትንሽ ነው፡፡ ዴቪደንዳቸውም ተይዟል፡፡ የእነሱ ጉዳይ ምን ይደረግ? የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ የግለሰቦች ኢንቨስትመንትን አልተመለከተም፡፡ የእነሱን ጉዳይ መመልከት ያስፈልጋል በማለት ጭምር ነው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሄድኩት፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ከአንድ ሰዓት ለበለጠ ጊዜ ሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸውን ይዘው በጣም ጥሩ ውይይት አድርገናል፡፡ እንዴት ልግለጸው? ደስ በሚልና በሚያጠግብ ሁኔታ አወያይተውኛል፡፡ ሐሳቤንም አቅርቤያለሁ፡፡ እንዲያው የእነዚህን ሰዎች ችግር ብቻ ማየት አልነበረም፡፡ መመርያው ፍርኃትንም ጭምር አሳድሯል፡፡ የተፈጠረው አንደምታ ጥሩ አይደለም፡፡ ልንወረስ ነው ወይ? ለትውለደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ቢጫ ካርድም ይዘናል እያሉ ነው፡፡ በደንብ ያልተገነዘቡትም ነገር ያለ ይመስለኛልና ጉዳዩ በደንብ ቢታይ ብዬ ተናግሬያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራዎች ብቻ ሳይሆን የውጭ ኩባንያዎችም በተገደበ መልኩ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ይግቡ የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ በተለይ ዳያስፖራዎች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ዘርፉን ቢቀላቀሉ ይገኛል ብለው ያስቀመጡት ስሌትም ስላለ ስለሱም ቢንገሩኝ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- እንደማስበው ከአሁኑ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዲሴምበር 31,2016 የጊዜ ገደብ በመስጠት የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ዜግነት ያላቸው በተለይም ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ እስከ 25 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ይህንንም እስከሚቀጥሉት አምስት ዓመት ድረስ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለሁሉም ቢፈቀድ ጥሩ ነው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ የፋይናንስ ተቋማቱ 25 ከመቶ ድርሻ ለውጭ ዜጐችና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን 20 በመቶ አዲስ ሽያጭ፣ አምስት በመቶ ደግሞ አሁን ላሉት ብንሸጥ፣ ሽያጩም በውጭ ገንዘቦች እንዲሆን ቢደረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ይሆናል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱም አክሲዮኖቻቸው የሚሸጡት በከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ አሁን እኮ አክሲዮን ሲሸጡ እስከ 70 በመቶ ከፍተኛ መጠን ወይም ፕሪሚየም ጨምረው ነው፡፡ ገዥ ስላላቸው አንድ አክሲዮን 30 በመቶ ፕሪሚየም ተጥሎለት በውጭ ምንዛሪ ለውጭ ሰዎች ቢሸጥ፣ በአማካይ እስከ 30 በመቶ በፕሪሚየም ይሸጣል ብንል እንኳ የ20 በመቶ የአክሲዮኑ ድርሻ፣ በ30 ከመቶ ፕሪሚየም ዋጋ ቢሸጥ፣ ለአገራችን የፋይናንስ ተቋማት ካፒታል በውጭ ምንዛሪ ወደ አገራችን እንዲገባ ማመቻቸት ማለት ነው፡፡ በዚህ ስሌት በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ ከአራት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማስገባት ይችላል፡፡ ይህ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ እንደማስበው እነዚህ ሰዎች በዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ሕጉን ለቀቅ ማድረጉ ሌሎች ፈራ ተባ እያሉ ዳር የቆሙትን ሁሉ ያበረታታል፡፡ ጉዳዩን አበክረን ብናየው ጥሩ ይመስለኛል፡፡   

ሪፖርተር፡- ይህንን ሐሳብ ካቀረቡ ምላሹ ምን ሆነ? ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በተወያዩበት ወቅት ምን ምላሽ ተሰጠዎት? መፍትሔስ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከማስበውና ከምገምተው በላይ ተቀብለው ሲያነጋገሩኝ ፍላጐትና ምኞቴን ከማስረዳት ውጭ ወዲያው መልስ ይሰጡኛል ብዬ አይደለም የሄድኩት፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ወዲያው መልስ ለመስጠት አይችሉም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን እንደተረዱልኝ በትክክል ገብቶኛል፡፡ እኔም አመስግኛለሁ፡፡ እጅግ ከምጠብቀው በላይ፣ ምናልባትም ይገባኛል ከምለው በላይ አክብሮት አሳይተውኛል፡፡ ሪፖርተር፡- ሕጉ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የውጭ ዜጐች አይገቡም ብሏል፡፡ ይህ ማለት ዜግነታቸውን ሲቀይሩ አክሲዮናቸውን መሸጥ ይችሉ አልነበረም? ይህ ለምን አልሆነም?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ትክክል ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ላይ እንደ ጥፋት አድርጌ የማየው ነገር የለም፡፡ ማናችንም ብንሆን ወደ መንግሥት ጣት መቀሰር አንችልም፡፡ አዋጅ ወጥቷል፡፡ አዋጁ እስካለ ድረስ ይህ አዋጅ ትክክል አይደለም ብለን ብናስብም እንኳ በአዋጁ መገዛታችን ግን ግድ ነው፡፡ እሱን ያለማድረጋችን ጥፋቱ የእኛ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ከእኛ ከጥቂት ሰዎች አስተሳሰብና በኢንስትሪው ውስጥ ከተሰማራነው ከጥቂቶች የበለጠ ልበ ሰፊና ታጋሽ ነው፡፡ ይህ ነገር ጥፋትም ቢሆን፣ በዚህ ጥፋት ቅጣት ተጥሎ የሚገኘው ገቢ ወይም የሚገኘው ጠቀሜታ ለመንግሥት ኢምንት ነው፡፡ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ አዎ፣ የፋይናንስ ተቋማቱም ቢሆኑ ዜግነታቸውን ለውጠው ነገር ግን በባንክና ኢንሹራንስ ውስጥ አክሲዮን የያዙ ኢትዮጵያውያን መኖር አለመኖራቸውን ለማወቅ ቁጥጥር አላደረጉ ይሆናል፡፡ አላደረጉም ነበር፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ የወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ካሉ አሳውቁን፣ ሪፖርት እንድታደርጉ በየጊዜው እንድትጣሩ ብሏል፡፡ እኛም አልጨቀጨቅንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥፋቱ የከፋ ነው ብሎ እጅ መቀሰር አይቻልም፡፡ ትርፍ የለውም፡፡ እኔን እንደሚመስለኝ ሌላም ማየት የሚገባን ነገር አለ፡፡ ዳያስፖራዎች እያወቁም ሆነ ሳያውቁ አክሲዮን የገዙት ይህንን ያህል ትርፍ ለማጋበስ ብቻ ነው ተብሎ መታሰብ የለበትም፡፡ ትክክል አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም ከፋይናንስ ተቋማት የበለጠ ኢንቨስት ያደረጉት በሪል ስቴት ዘርፍ ነው፡፡ በዚያ በኩል ደስ የማይል ሁኔታ ገጥሟቸዋል፡፡ ብዙ ዳያስፖራዎች ገንዘባቸውን አቃጥለዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ባንክና ኢንሹራንስ የሄዱበት ምክንያት የፋይናንስ ዘርፉ የቅርብና ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚደረግበት ነው፡፡ አንዳንዴም ከሚያስፈልገውም በላይ ቁጥጥር አለባቸው፡፡ አንዳንዴ በየጥቃቅኑ ሥራ ውስጥ ሳይቀር ብሔራዊ ባንክን የከተቱ የሚመስሉ መመርያዎችም ይወጣሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን የማይታበለው ጥብቅ ቁጥጥር በመደረጉ እስካሁን ድረስ በመልካም ጤና ላይ ሆነው እየሠሩ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራዎች በእነዚህ ዘርፎች የሚያደርጓቸው ኢንቨስትመንቶች በሪል ስቴት ውስጥ የገጠማቸውን ዓይነት እንደማይከሰት እርግጠኛ በመሆን ነው፡፡ ኢንቨስትመንታቸውም የተጠበቁ ይሆናሉ የሚል እምነት ይዘው ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር በበጐ ጐን ቢታዩ ይሻላል፡፡ ለምሳሌ በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውሰጥ ዳያስፖራዎችን ብናስገባ እነዚህን ተቋሞች ይቆጣጠሩና ወደ ሌላ አቅጣጫ ይወስዷቸዋል የሚል ፍራቻ ካለ ብሔራዊ ባንክ  ትልቁን ድርሻ ከየባንኩና ኢንሹራንስ ኩባንያው መውሰድ ይችላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራዎች በባንክና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ እንዳይገቡ የተደረገበት ዋና ምክንያት ምንድን ነው? ምን ስለሚታሰብ ይመስልዎታል የመንግሥት ዋናው ሥጋትስ?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- በእነሱ ስም እነዚህን ተቋሞች የሚቆጣጠሩ ባለአክሲዮኖች ይወስዷቸዋል የሚል ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ የራሱን የልማት አቅጣጫ ይይዛል፡፡ ፋይናንስ የአገር ሀብት እንደመሆኑ መጠን በየት አቅጣጫ መፍሰስ እንዳለበት መንግሥት ዕቅድ አለው፡፡ ለምሳሌ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይህን ያህል፣ ለዚያኛው ዘርፍ ደግሞ ይህንን ያህል ብሎ ይመድባል፡፡ አሁንም ቢሆን እኮ መንግሥት እያደረገው ነው፡፡ ምን ያህል ብድር ለየትኛው ሄደ የሚለውን እኮ ይከታተላል፡፡ ይህም እኮ ያው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት ዳያስፖራዎችን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ አስገብቶ በቀላሉ መቆጣጠር ይችል ነበር ከተባለ ይህንን ለማድረግ ሥጋቱ ምንድነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- ሼክስፒር እንዳለው ስለሚያስፈራ ነገር ስታስብ መጀመሪያ ሊያሳስብህ የሚገባው ራሱ ፍርኃት ነው፡፡ በአንድ መድረክም በዚሁ ጉዳይ ላይ ተናግሬያለሁ፡፡ መንግሥት ለምንድነው የሚፈራው ለሚለው እሱ ፍርኃትን ነው የሚፈራው፡፡ መሳሳትን ነው የሚፈራው፡፡ እንግዲህ ብዙ ጊዜ እንደምለው የሚሠራ ሰው የመሳሳት ዕድል አለው፡፡ ሰፊና ጠባብ ይሆናል እንጂ ዕድሉ አለ፡፡ ነገር ግን መሳሳት ሊያስኮንን አይገባም፡፡ የሚያስኮንነው ከስህተት ያለመማር ነው፡፡ ወይም ስህተት መሆኑን እያወቀ ስህተቱን የሚደግመው  መኮነን አለበት እንጂ በጐ ነገር አደርጋለሁ ብለህ በምትሠራበት ጊዜ ስህተት ቢፈጠር፣ አንገትህን የሚያስቆርጥ መሆን የለበትም የሚል የግል ዕይታ አለኝ፡፡

ቢሮክራሲውን የሚመሩት ውስጥ ፍርኃት የነገሰበት ከባቢ ሁኔታ አለ ብዬ ነው የማስበው፡፡ አንዳንዴ ከማየውና ከተጻፈውም እንዳነበብኩት የቅጣት ዱላ ይበዛል፡፡ የማይሠራና የማይሳሳት ደግሞ ጠያቂ የለውም፡፡ መንቀሳቀስ ያለባቸውን አካላት ሁሉ እንደ እግር ብረት ጠፍሮ የያዘው ፍርኃት ነው፡፡ የፍርኃት ቆፈን አለ፡፡ ቀስ በቀስ፣ ፊት ለፊት ልንገጥመውና ልናስወግደው የሚገባው ጉዳይ የመሳሳት ፍርኃትን ነው፡፡ ላለመሳሳት መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እርስዎ የመሳሳት ፍርኃት የሚሉት፣ ለቢሮክራሲውም ችግሩ ፍርኃት ከሆነ መደረግ ያለበት ምንደን ነው?

አቶ ኢየሱስወርቅ፡- የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ሰዎች በሚያውቁት ችሎታቸውና ዕውቀታቸው በሚፈቅደው ሥራ ላይ መሰማራት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል በይፋ እንደተነገረው የሰዎች ሹመት በዕውቀትና በችሎታ ሳይሆን ቅድሚያ በታማኝነት የሚለው ነገር መከለስ አለበት፡፡ ሰዎች በሚችሉትና በሚያውቁት ቦታ ላይ መመደብ አለባቸው፡፡ ነገር ግን የፌዴራሊዝም ጠባይን ለማንፀባረቅ ሲባል ብዙ ማመቻመች አለ፡፡ ለምሳሌ የቢሮክራሲው ቁልፍ ቦታዎች ላይ የፌዴራል ክፍፍል አለ፡፡ ይህ በሥጋት የተነሳ ነው፡፡ ይሁን ከተባለ፣ ለፌዴራል ሥርዓታችን ጠቃሚ ነው ከተባለና እስከ መጨረሻው እንሂድበት ካልን፣ ይህ ቦታ ለዚህ ብሔር የምንል ከሆነ፣ ከዚያ ብሔር ውስጥ ምርጥ የሆነው በማሾ ወይም በባትሪ ተፈልጐ መምጣት አለበት፡፡ ካልሆነ በፖለቲካ  ታማኝነት ብቻ ሹመት የሚሰጥ ከሆነ ወይም የቢሮክራሲውን አሠራር የሚይዙት ከሆነ የምንጯጯህበት የመልካም አስተዳደር ጩኸት አንዱ ምንጩ ይኼ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ይህንን እስካደረግን ድረስ የስህተታችን መከሰት በተቻለ መጠን ዝቅ ለማድረግ ሞክረናል ማለት ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ቅድመ ሁኔታውን እየሠራን ነው ማለት ነው፡፡ ስህተት እንዳይሠራ እስከመጨረሻው መታሰብ አለበት፡፡ ይህም ሆኖ መቶ በመቶ ስህተት አይሠራም ማለት ከሰዎች እግዚአብሔርነትን መጠበቅ ይሆናል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች