Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገሪቷን ለገጠሟት ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው በብሔራዊ ውይይት ብቻ ነው!

ለዓመታት ለተጠራቀሙ ብሶቶችና ቁርሾዎች መነሻ የሆኑ ተቃውሞዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተቀስቅሰው ለግጭቶች መንስዔ ሆነዋል፡፡ ግጭቶቹ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም ምክንያት ከመሆናቸው በተጨማሪ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ላይ ሥጋት ጋርጠዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ባለመደመጡና ተገቢውን ምላሽ ባለማግኝቱ በምሬት የታጀቡ ወጣቶች አደባባይ ሲወጡ ምላሹ የከበደ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህንን አጋጣሚ እንደ ማንቂያ ደወል መጠቀም የነበረበት መንግሥት ያጋጠሙት ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ጣቱን ወደ ሌሎች ኃይሎች ሲቀስር፣ ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት ችግሮቹን የበለጠ የሚያባብሱና የሚያወሳስቡ ወገኖችም ተከስተዋል፡፡ ሁለት እልህ የተጋቡ ኃይሎችን ወደ ክብ ጠረጴዛ አምጥቶ ያጋጠሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሲባል ማንኛውም መስዕዋትነት መከፈል አለበት፡፡ ከአገርና ከሕዝብ ህልውና የሚቀድም የለምና፡፡

አገሪቱ ፅኑ ሕመም ይዟታል፡፡ ልጆቿ ሕመሟን ተረድተው በጋራ መፍትሔ ፍለጋ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ለሕመሙ መነሻ የሆነውን ችግር ከሥር ከመሠረቱ መረዳት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግትርነትና አጉል ድርቅና መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ወገን የራሱን አጀንዳ ብቻ ለማስፈጸም ከመሯሯጥ ይልቅ፣ ያጋጠሙ ችግሮች ምን ዓይነት መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል መባል አለበት፡፡ ከሥልጣን የበለጠ ማሳሰብ ያለበት የአገር ህልውና ነው፡፡ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ነው፡፡ በሊቢያ፣ በሶሪያና በየመን ለሕዝብ ዕልቂትና ለአገር ውድመት የዳረጉ አመፆች ዛሬ ቁጭት እየፈጠሩ ያሉት ገና ከመነሻው እልህ በተጋቡ ኃይሎች መካከል ሰላማዊ ውይይትና ድርድር ለማድረግ ፍላጎት ባለመኖሩ ነበር፡፡ ‹‹ብልህ ከሌሎች ውድቀት ሲማር ሞኝ ከራሱም ጥፋት አይማርም›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ዕልቂትና ውድመት ውስጥ የገቡ አገሮችን ድርጊት ከመድገም የማይመለሱ ወገኖች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ባወጣው ይውጣ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖች በተቻለ መጠን ወደ ብሔራዊ ውይይት ማምጣት ከፍተኛ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ወደ ደም መፋሰስ የሚያመሩ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ የእስካሁኑ አሳዛኝ ድርጊት ይበቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡ ዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ለሚያነሱዋቸው ሰላማዊ ጥያቄዎች መንግሥት ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲኖርበት፣ በሕገወጥ መንገድ የሚከሰቱ  የኃይል ተግባራት ደግሞ ሊገቱ ይገባል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲባል የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ዋስትና የሰጣቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ መሠረታዊ መብቶች ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ መከበር አለባቸው፡፡ የተለየ አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸው ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ አለባቸው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር ተከፋፍቶ ዜጎች የፈለጉትን የመደገፍም ሆነ በአባልነት አስተዋጽኦ የማድረግ መብታቸው መከበር አለበት፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ አመለካከቶች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት የሐሳብ ገበያ በመሆኑና ሕገ መንግሥቱም በሚገባ የተቀበለው በመሆኑ በምልዓት ተግባራዊ ይደረግ፡፡ የኃይል ተግባራት ሕገወጥ በመሆናቸው ለሕጋዊና ለሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ከለላ ይሰጥ፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትና አምባገነንነት ለአገር አይበጁምና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ይጣል፡፡ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮችም ላይ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ የፖሊሲ ውሳኔዎች ተግባራዊ ይሁኑ፡፡ ለዚህም ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ለውይይት መድረኮች ይመቻቹ፡፡

መንግሥትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ድርጅታቸው ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት የሚበጁ ውሳኔዎችን ያስተላልፍ ዘንድ ከፍተኛ ጥረት ያድርጉ፡፡ የአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ ብቻ በአገሪቱ ላይ እንዲነግሥ መፈለግ ለበለጠ ምሬት፣ ብሶት፣ ተቃውሞ፣ ግጭትና ውድመት የሚዳርግ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከ80 በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባሉባት ኢትዮጵያ አንድ ገዥ ርዕዮተ ዓለም ብቻ ለአገር ብቸኛ አማራጭ ነው ብሎ መደምደም ጤነኛ አስተሳሰብ ካለመሆኑም በላይ፣ አገር እንደሚያጠፋ መተማመን ላይ መደረስ አለበት፡፡ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ተጨባጩን የአገር ሁኔታ በሚገባ ገምግሞ የሚያስማማ ውሳኔ ላይ መድረስ እንጂ፣ መሬት ላይ የሚታየውን ሀቅ ንቆ ሌሎች ምክንያቶችን መደርደር ለበለጠ ጥፋት ይጋብዛል፡፡ እስካሁን ለተፈጠሩ ችግሮች ኢሕአዴግ ያበረከተውን አሉታዊ አስተዋጽኦ በጠንካራ ግምገማ አይቶ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ሲገባው፣ ችግሮቹን ሁሉ ለሌሎች በማሸከም ለማድበስበስ መሞከር አገሪቱን የበለጠ አደጋ ውስጥ ይከታታል፡፡ ይልቁንም ውስጡን ፈትሾ፣ ችግሮቹን ሁሉ አምኖና ራሱን ለለውጥ አዘጋጅቶ በመቅረብ ከተቀናቃኞች ጋር ውይይት መቀመጥ ያስከብራል እንጂ አያሳፍርም፡፡ ከዚህ በኋላ ግጭቶች ወደ ደም መፋሰስ እንዳያመሩ የሚፈልግ ከሆነ ተጨባጩን እውነታ እየመረረውም ቢሆን ይቀበል፡፡ አደረጃጀት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መጓዝ ፋይዳ የለውም፡፡

በሌላ በኩል በአገርም ሆነ በውጭ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችም ቢሆኑ፣ አገርን ትርምስ ውስጥ ከሚከቱ አደገኛ ድርጊቶች ታቅበው ለብሔራዊ ውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጫ መስጠት አለባቸው፡፡ በቀጥታ የማይቆጣጠሩትን የሕዝብ ጥያቄና ተቃውሞ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት አቅጣጫ እያሳቱ ለዕልቂትና ለውድመት የሚጋብዙ አጓጉል ድርጊቶችን ከመፈጸም ሊገቱ ይገባል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ እናስባለን የሚሉ ከሆነ ለብሔራዊ ውይይት መጀመር ተነሳሽነቱን ያሳዩ፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል ብቻ የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ለመጣል መሞከር አሳፋሪ ነው፡፡ የአገርን ህልውና ከጠባብ የሥልጣን ፍላጎት አሳንሶ ለማየት ማሰብም ሆነ መሞከር ተቀባይነት የለውም፡፡ ይልቁንም አገርን ለውድመት የሚዳርጉ አጉል ድርጊቶች ለመፈጸም ከመሯሯጥ ወጥተው፣ ለዴሞክራሲያዊትና ለሰላማዊት አገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረውን ብሔራዊ ውይይት አጀንዳቸው ያድርጉ፡፡ አመፅና የኃይል ተግባርን ሙጥኝ ካሉ ግን የሚመኙትን ሳይሆን የሚያገኙት፣ ለጠላት ዓላማ ማስፈጸሚያ ይሆናሉ፣ ለአገርና ለሕዝብ ውድመት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ኃላፊነት የጎደለው ግትርነት፣ ጥላቻና እልህ ውስጥ ከመዳከር ወጥተው ለብሔራዊ ውይይት መጀመር ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡

በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሰላማዊ ውይይት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበራትና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ በነፃነት በመንቀሳቀስ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እንዲያረክቱ ዕድሉን ሊያገኙ ይገባል፡፡ እነሱም ያለምንም አድልኦና ወገናዊነት አጥፊውን እየገሰፁና እያረሙ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ክብ ጠረጴዛ እንዲመጡ ተነሳሽነቱን ሊወስዱ ይገባል፡፡ ይህም ብሔራዊ ግዴታቸው ነው፡፡ በጠላትነት የሚተያዩ ወገኖች ውስጣቸው ያለውን ቁርሾ አውጥተው ለአገሪቱ ዘለቄታ ያለው የጋራ መፍትሔ እንዲያመጡ እነዚህ ወገኖች ጠንክረው መሥራት አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ በፖለቲካ ኃይሎች እየተጠለፉ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ይሆኑና ለግጭትና ለውድመት ጥሬ ዕቃ በመሆን አደጋውን ያባብሱታል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን ከዚህ በፊት የታዩ አላስፈላጊ ተሞክሮዎችን በፍፁም በማስወገድ፣ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ለሕዝቡ ህልውና ሲሉ ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ለመቀራረብና ለመነጋገር ቢያስቸግሯቸው እንኳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያግዛቸው ተነሳሽነቱን ይውሰዱ፡፡  የግድ ነው፡፡

በሕዝብ ውስጥ ጥላቻን የሚዘሩ፣ ማንነትና ሰብዕናን የሚጋፉ፣ በሰላምና በእኩልነት አብሮ የመኖር እሴትን የሚንዱ፣ ዴሞክራሲ እንዳይሰፍን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚታገሉ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር የሚተጉ፣ የሕግ የበላይነትን የሚገዳደሩ፣ በአጠቃላይ ለሰላምና ለዕድገት ጠንቅ የሆኑ አጓጉል ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎቿ የጋራ አገር መሆን የምትችለው መሠረታዊ መብቶች ሲከበሩ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሲረጋገጥ ነው፡፡ እኩል ተጠቃሚነት ሲኖር ነው፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ ድርጊቶች ሲቆሙ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ እነዚህን የተቀደሱ ጉዳዮች  በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈን ሁሉም ወገኖች ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ ይስጡ፡፡ የጥላቻ ድልድዮች ይሰበሩ፡፡ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጎልቶ ይታይ፡፡ የፍቅር እንጂ የጥላቻና የጥፋት መንገዶች ይዘጉ፡፡ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሔዎች እንዲፈለጉ መድረኮች ይመቻቹ፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚያስማሙ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አማራጮች በሙሉ ይፈተሹ፡፡ እነዚህ ምኞቶች ዕውን ይሆኑ ዘንድ ሁሉም ወገን በቅንነትና በኃላፊነት መንፈስ ራሱን ያዘጋጅ፡፡ አገሪቱን ለገጠሙዋት ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ብሔራዊ ውይይት ብቻ እንደሆነ መተማመን ይኑር!       

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...

የአስፕሪን ታሪክ

በቤት ውስጥ የሚገኝ የመድኃኒት መደርደሪያ፣ ምንም ቢሆን፣ እስፕሪንን ሳይጨመር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...