Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመወሰን ፈተና

የመወሰን ፈተና

ቀን:

ከእንቅልፍ ከመነሳት ጀምሮ ለመኝታ ወደ አልጋ እስኪኬድ ሰዎች ቀኑን ሙሉ የተለያዩ ነገሮች ላይ ይወስናሉ፡፡ ምን ልልበስ? መጀመሪያ ወዴት ልሒድ ወይም የትኛውን ነገር ልከውን? ማንን ላግኝ የሚሉትና መሰል ነገሮች ላይ በመወሰን የቀን ውሎ ሊጀመር ይችላል፡፡ ውሳኔ እንዲህ ነግቶ እስኪመሽ የተለያዩ የሕይወት መስመሮቻችንን የሚነካ የመሆኑን ያህል ሰዎች ትኩረት እንደማይሰጡት በተለያዩ ጥናቶች ተመልክቷል፡፡

አንዳንዶች ቀላል የሚመስሉም ይሁን ትልቅ ነገሮች ላይ ለመወሰን ፈጣኖች ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ውለው አድረውበት ጊዜ ወስደው ይወስናሉ፡፡ ቀላል በሚባሉ ለምሳሌ ምን ልብላ? ነገሮች ላይ እንኳን ለመወሰን የሚቸገሩ፣ ባለመወሰን ጊዜና ሁኔታዎች እንዲወስኑላቸው ነገሮችን የሚተዉና ዘወትር ስሜታዊ ሆነው በወሰኑት ውሳኔ መፀፀትን ልማዳቸው ያደረጉም አይታጡም፡፡

በሰላሳዎቹ አጋማሽ ትገኛለች፡፡ በአንድ በጐ አድራጐት ድርጅት የአስተዳደር ሠራተኛ ነች ማክዳ ንጉሤ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በተለይም ወሳኝ የምትላቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜ ወስዳ የምትወስን ዓይነት ሰው ብትሆንም፣ በዚህ መልኩ ወስና ዛሬ የምትፀፀትባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ትናገራለች፡፡

ማክዳ እንደምትለው፣ አብዛኛውን ጊዜ በጉዳዮች ላይ ለመወሰን ጊዜ የምትወስድ ቢሆንም፣ ስሜታዊ ሆና ውሳኔ ላይ የደረሰችባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ በቶሎ የምትወስንባቸው አንዳንዴ ረዥም ጊዜ የምትወስድባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ይህንን የሚወስነው ደግሞ የጉዳዮቹ ክብደትና የምትወስንበት ሁኔታ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ለፒኤችዲ ጥናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ፍቅረኛዋ የጋብቻ ጥያቄ አቅርቦላት ነበር፡፡ ትንሽ እንቆይ በማለት ጥያቄውን ሳትቀበለው ቀረች፡፡ ዛሬ ላይ ያን ውሳኔዋን ትፀፀትበታለች፡፡ ‹‹አሁን በሥራ ምክንያት መምጣት የሚችልበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡ በቀጣዩ ዓመትም ሊያደርገው የሚችል አይመስለኝም›› ትላለች ማክዳ፡፡

በቢሮ ውስጥ ከሥራ ጋር በተያያዘ የምትወስዳቸው ውሳኔዎች አሠራርን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው በዚህ ረገድ ነገሮች ግልጽ ናቸው፡፡ በቤተሰብ ላይ ተፅዕኖ በሚኖራቸው ነገሮች ላይም መላ ቤተሰብ ተነጋግሮ የመወሰን ልማድ ስላላቸው በዚህ በኩልም ችግር የለባትም፡፡ ቢሆንም ግን አንዳንዴ ጊዜ ተወስዶ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ውጤትም መጥፎ እንደሚሆን፤ በዙሪያዋ ባሉና ስሜታዊ ሆነው በሚወስኑ ሰዎች ምክንያት በተለያየ መልኩ ተፅዕኖ ደርሶባት እንደሚያውቅም ማክዳ ታስረዳለች፡፡

ከባድ ቢሆንም ከጥቂት ዓመታት በፊት የአምስት ዓመት የፍቅር ግንኙነቱን ለማቋረጥ ወስኗል፡፡ በወቅቱ እንዲሁ ነገሮችን ሲያወጣና ሲያወርድ ቢቆይም በትክክል ቁጭ ብሎ በማሰብ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ያስታውሳል፡፡ አንድም ቀን በውሳኔው ፀፀት ገብቶትና ወደኋላ ለመመለስ አስቦ እንደማያውቅ ይናገራል፡፡

በነገሮች ላይ ሲወስን ምን ዓይነት ነገሮችን እንደሚመለከት ጠይቀነው ነበር፡፡ ‹‹ብዙም ምክንያታዊ እንድሆን የማልጠበቅባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ለመወሰን የሚከብዱኝ አይደሉም፡፡ ውስጤን ስሜቴን ተከትዬ የምወስንባቸው ነገሮችም አሉ›› በማለት እንደሁኔታዎቹ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከስሌት ሊያስገባ እንደሚችል ያስረዳል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ለምሳሌ ዕቃ ለመግዛት ቢፈልግ የትኛውን ልግዛ? ምን ትምህርት ላጥና? ባለኝ ጊዜ ውስጥ ማንን ላግኝ? የሚሉ ነገሮች በራሳቸው ውሳኔ የሚጠይቁ ቢሆኑም ያን ያህል ምክንያታዊ መሆን ወይም ከራስ ጋር መስማማት የሚጠይቁ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ውሳኔ ከሚባሉ ምርጫ መባላቸው ይቀላል ይላል፡፡

ስሜታዊ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም፣ ሁሌም ነገሮችን ምክንያታዊ ሆኖ ለመመዘን እንደሚጥር ይናገራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለነገሮች ጊዜ ለመስጠት መፍቀድ ዓይነተኛ መንገድ ነው ብሎም ያምናል፡፡ ቢሆንም ግን የሚታሰበውን ያህል ስሜትን ወደ ጐን በማለት ምክንያታዊ ሆኖ መወሰን ቀላል እንዳልሆነ ያውቃል፡፡ በዚህ መልኩ ትልልቅ በማይላቸው የሕይወቱ ጉዳዮች ላይም ቢሆን ባደረገው ውሳኔ የሚፀፀትበት አጋጣሚ አለ፡፡ ‹‹ቢሆንም በወቅቱ በነበረኝ መረጃና በነበረኝ መረዳት ያደረግኩት ትክክል ነው የምል ዓይነት ሰው በመሆኔ፣ ለመፀፀቱ ብዙም ቦታ የለኝም›› ይላል፡፡

በአርባዎቹ መጀመሪያ ትገኛለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ልጅ አላት፡፡ ከባለቤቷ ጋር ከተለያዩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ትዳሯን ማፍረስን ጨምሮ በሕይወቷ የተለያዩ ነገሮች ላይ የምትወስነው እንዴት እንደሆነ ጠየቅናት፡፡ የብዙዎችን አስተያየት ትጋራለች፡፡ ውሳኔዋ ባጋጠሟት ጉዳዮችና በምትወስንበት ሁኔታ ላይ እንደሚወሰን ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ጉዳዩ እሷና እሷን ብቻ የሚመለከት ከሆነ፣ ለመወሰን ፈጠን ትላለች፡፡ ነገሩ ልጇን አልያም ቤተሰቧን ሊነካ የሚችል ከሆነ፣ ነገሮችን ግራና ቀኝ መዝና ውሳኔዋ ሊያስከትል የሚችለውን ነገርም ለመገመት ትሞክራለች፡፡

በሌላ በኩል ነገሩ እሷን ብቻ ወይም ቤተሰቧን ይመልከት፣ የውሳኔዋ ተፅዕኖ ብዙ የማይሄድ ወይስ የረዥም ጊዜ ነው? የሚለውንም በደንብ ታጤናለች፡፡ የት ልኑርና ምን ላይ ኢንቨስት ላድርግ በሚሉ ነገሮች ላይ ከውሳኔ ላይ መድረስ ብዙ ጊዜ ማሰብ የሚጠይቅ መሆኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዳች መምጣቷን ትገልጻለች፡፡ ለተወሰኑ ጊዜአት ከኢትዮጵያ ውጭ ኖራለች፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሠርታለች፡፡ ለብቻዋ ከቤተሰብ ጋርም የተለያዩ ቢዝነሶችን ለመጀመር ሞክራ ነበር፡፡ አሁን የምትሠራው የራሷን ቢዝነስ ነው፡፡

‹‹ነገሮች ላይ ጊዜ ወስዶ መወሰን በሕይወቴ የተማርኩት ትምህርት ነው ልል እችላለሁ፡፡ መሳሳት እንዳለመፈለግ ወይም እሳሳት ይሆናል ብሎ እንደመፍራት ሊወሰድ ይችላል፡፡ በእርግጥ ለመወሰን ረዥም ጊዜ መውሰዴ የጐዳኝ ጊዜም አለ፡፡ አንዳንዴ ብዙ ማሰብ ምንም ዕርምጃ አለመውሰድ ይሆንብኛል›› ትላለች፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቷን የሰጠችን ወ/ሮ ሕይወት ይርጋ ደግሞ ብዙ ጊዜ በነገሮች ላይ ለመወሰን የምትቸገር ዓይነት ሰው ነች፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡ ሦስተኛውን ልጅ ደግሞ በመጠባበቅ ላይ ነች፡፡ ሦስተኛ ልጅ ያስፈልገኛል የሚል ሐሳብ ቀድሞም የነበራት ቢሆንም፣ መቼ የሚለው ላይ መወሰን ብዙ ጊዜ እንደወሰደባት ትናገራለች፡፡ በመጨረሻ ጊዜው ላይ ስትወስን እንኳን ወደ ጤና ተቋም ሔዳ ለረዥም ጊዜ ትጠቀመው የነበረውን የወሊድ መቆጣጠሪያ ለማስወጣት ብዙ ዘግይታለች፡፡   

ቀደም ባሉት ጊዜአትም ባለመወሰን የተጐዳችባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ታስታውሳለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች የፍቅር ጓደኛዋ የነበረው ሰው እሷ በግልጽ በማታውቀው ምክንያት ግንኙነታቸው እንዲቋረጥ ሲወስን ውሳኔውን መቀበል አቅቷት ረዥም ጊዜ መቸገሯን ትገልጻለች፡፡ ከዚያ በኋላም የነበረችበት ግንኙነት የትም እንደማያደርሳት እያወቀች ለመወሰን በመቸገር ቆይታለች፡፡ ‹‹አራት ዓመት አብረን ቆይተናል፡፡ ሁለቱን ዓመት ያሳለፍኩት እንዲህ ቢሆንስ እንደዚያ እያልኩኝ ላለመወሰን ስታሽ ነው›› ትላለች፡፡

ለመወሰን የምትቸገር ቢሆንም ከወሰነች ግን ብዙም ወደኋላ እንደማትመለስ ትገልጻለች፡፡ ብዙ ጊዜ ውሳኔ ላይ ስሜታዊ የመሆን ነገር ቢኖርም፣ እሷ ግን በንዴት ወይም በሀዘን ውስጥ ሆና ለመወሰን ሞክራ አታውቅም፡፡ ይልቁንም በእንደዚህ ዓይነት ጊዜአት ብቻዋን መሆንና በዝምታ ነገሮችን ማሳለፍ ምርጫዋ ነው፡፡

ሰዎች ውሳኔ ላይ ሲደርሱ ከስሜታዊነት ውጭ ሆነው መሆን አለበት ይባላል፡፡ ቀደም ያሉ ጥናቶች እንደሚያስቀምጡትም፣ ውሳኔ የአስተሳሰብ እንጂ የስሜት ውጤት አይደለም፡፡ በቅርብ ጊዜ የወጡ የኒውሮ ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ውሳኔዎች የምክንያታዊነት ሳይሆን የስሜት ውጤት ናቸው፡፡ ማይንድሴት የተባለ የምክር አገልግሎት ድርጅት አቋቁመው በመሥራት ላይ የሚገኙት ወይዘሮ ናርዶስ ማሞ፣ ውሳኔ ላይ ስሜታዊ መኮን የለበትም ቢባልም ውሳኔዎችን ከስሜት ነፃ ማድረግ እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ውሳኔ በማመዛዘን ብቻ የሚደረስበት፤ ስሜትም እንዲሁ ዞር በል የሚባል አይደለም፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም፣ የልጅነት ጊዜ ተሞክሮዎች እንዲሁም ሲወርድ የመጣ የዘር ነገር ሁሉ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ምንም እንኳ ትምህርት ወይም ማገናዘብ ሰዎችን ምክንያታዊ የሆነ ውሳኔ ላይ እንዲደረሱ የሚያስችል ቢሆንም፣ እንደ ስሜት፣ የልጅነት ተሞክሮና ዘር ያሉ ነገሮችም ጣልቃ ይገባሉ፡፡

ከውሳኔ ጋር በተያያዘ ስሜት ወደ ጐን መባል አለበት ቢባልም፣ በአግባቡ ከተጠቀሙበት ስሜት በውሳኔ ላይ ሊረዳ እንደሚችል ወ/ሮ ናርዶስ ይናገራሉ፡፡ ንዴትን በምሳሌነት በማንሳት ውሳኔ ላይ ለመድረስና በውሳኔው መሠረት ለመራመድ እንደሚረዳ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም ስሜትን ሰዎች በሚጠቅማቸው መንገድ መጠቀም እንዲችሉ ይመክራሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ምክንያታዊ በሚባሉት ውሳኔዎች እንኳን ስሜቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ውሳኔዎች ይህ ወይም ያ ተብለው የሚደረጉ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ምርጫ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ስሜት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ባይመስልም አንዳንድ ጊዜ ደመነፍስ ስሜትን ማመን አስፈላጊ እንደሆነ ሳይንስ እንደሚያስቀምጥ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች እንደሁኔታው ስሜታቸውን በመከተል ከውሳኔ ላይ ቢደርሱ ትክክል ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ስለፈሩ ብቻ ከዚህ የሚያስጥላቸውን ውሳኔ ይወስናሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን የሚያስፈራኝ ነገር ምንድን ነው? ብሎ በመጠየቅ ገፍቶ መሔድ እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ ናርዶስ ይናገራሉ፡፡

ሰዎች ነገሮች ላይ ሲወስኑ መጀመሪያ የተለያዩ ሐሳቦችን እንዲያንሸራሽሩና አማራጮችን እንዲደረድሩ ይጠበቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጭንቅላት መጻፍ ብቻ ስለማይበቃ ወረቀት ላይ ጭምር ሐሳቦችን ማስፈር ግድ ይላል፡፡ ከዚያም የተሻለ የሚባለውን መምረጥ ቀላል እንደሚሆን ሳይኮቴራፒስቷ ያስረዳሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...