Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ በ700 ሚሊዮን ብር የፈሳሽ ማጣሪያ ግንባታ ውል ተፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ሳይት በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የፈሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ለማስገንባት ውል ተፈራረመ፡፡

ይህንን ግንባታ በባለቤትነት ለማካሄድ ውል የገባው አገር በቀሉ ኩባንያ ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ዓርብ ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራውን በይፋ ተረክቧል፡፡

ይህ ግንባታ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ኮዬ ፈጬ ሳይት ነው፡፡ በዚህ ሳይት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 50 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በመገንባት ላይ ሲሆን፣ ከሚገነቡት ቤቶች ከፊሎቹ ግንባታቸው ተጠናቆ በ11ኛው ዙር ዕጣ ወጥቶባቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሳኒቴሽን ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ በኮዬ ፈጬ ሳይት 50 ሺሕ ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ በአንድ ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉ ቢባል በአጠቃላይ በኮዬ ፈጬ ሳይት 250 ሺሕ ሰዎች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡

‹‹ነዋሪዎች ቤታቸውን በሚረከቡበት ወቅት ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቱ የሚጠናቀቅ በመሆኑ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፤›› በማለት አቶ ተስፋለም በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በተፈረመው ውል መሠረት ፕሮጀክቱ በሁለት ዙር የሚገነባ ሲሆን፣ በድምሩ 20 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ፍሳሽ በዘመናዊ መንገድ የማጣራት አቅም አለው ተብሏል፡፡ በዚሁ አካባቢ በተጓዳኝ እየተገነባ ካለው ሌላ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ጋር በድምሩ 33 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ ፍሳሽ ማጣራት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር አቶ ተስፋለም ተናግረዋል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት በባለቤትነት የሚገነባው ፀሜክስ ግሎባል የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን ያቀርባል፡፡ የፀሜክስ ግሎባል እህት ኩባንያ ራይኮን ኮንስትራክሽን ደግሞ ግንባታውን ያካሂዳል፡፡

ከፀሜክስ ጋር የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዝርጋታዎችን የሚያካሂደው ደግሞ የኔዘርላንድ ኩባንያ የሆነው ላንዱስትሪ ስኒክ ቢቪ ነው፡፡ የፀሜክስ ግሎባል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ረዘነ አያሌው በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ድርጅታቸው በ15 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥና በአምስት የኮንዶሚኒየም ሳይቶች ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያዎች ገንብቷል፡፡

ኩባንያው ባገኘው ልምድ በመጠቀም ይህንን ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ተናግረዋል፡፡ አቶ ረዘነ ጨምረው እንደተናገሩት፣ ከኩባንያቸው ጋር አብሮ የሚሠራው የኔዘርላዱ ኩባንያ በውኃ ሥራዎች ዘርፍ የ110 ዓመታት ልምድ አለው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የከተማውን ፍሳሽ የማስወገድ አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአቃቂ ፍሳሽ ማስወገድና በየኮንዶሚኒየም ሳይቶችም እየተካሄዱ ያሉት ግንባታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች