– በአውሮፕላኖች ዕድሜ ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ተጠየቀ
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የግል አየር መንገዶች የውጭ አገር ዜጎች እጅ አለበት መባሉ አነጋጋሪ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሕግ የግል አየር መንገድ በባለቤትነት ማንቀሳቀስ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ የውጭ አገር ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ አየር መንገድ ማቋቋም ወይም በተቋቋሙት ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ይከለክላል፡፡
ዓርብ ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ፣ ‹‹አንዳንድ የግል አየር መንገዶች ኢትዮጵያዊ ማሊያ ለብሰው የሚጫወቱ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፤›› የሚል አቤቱታ ለባለሥልጣኑ ቀርቧል፡፡
የአቢሲኒያ በረራ አገልግሎትና የፓይለት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው መንግሥት የአቪዬሽን መስኩን ለኢትዮጵያዊያን ብቻ የከለለው ዘርፍ ቢሆንም፣ የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያንን በመጠቀም የይስሙላ የአገር ውስጥ ኩባንያ በማቋቋም በትክክል በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ ኩባንያዎችን ገበያ እየተቀራመቱ መሆኑን በምሬት ገልጸዋል፡፡
‹‹የንግድ ፈቃዱ በኢትዮጵያዊ ዜጋ ስም የወጣ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች አገር በቀል ሳይሆኑ አገር ውስጥ የተተከሉ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሌላቸው፣ የሠሩበትን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ውጭ የሚወስዱ፣ ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል የማይፈጥሩ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ግብር የሚከፍሉና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ኩባንያዎችን ገበያ የሚቀራመቱ ካንሰር የሆኑ ኩባንያዎች ናቸው፤›› ያሉት ካፒቴን ሰለሞን፣ የእነዚህን ኩባንያዎች ጉዳይ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንደሚያውቅ በመጠቆም፣ ‹‹እስከ መቼ ነው በዝምታ የምትመለከቷቸው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች ማኅበር በበኩሉ አየር መንገዶች ወደ አገር በሚያስገቧቸው አውሮፕላኖች ላይ የጣለው የዕድሜ ጣሪያ እንዲነሳ ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አየር መንገዶች ከ22 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው የመንገደኛ አውሮፕላኖች እንዳያስገቡ ይከለክላል፡፡ የጭነት አውሮፕላኖች ዕድሜ ገደብ 25 ዓመት ነው፡፡ ይህ የሚደረገው የበረራ ደኅንነት ለማስጠበቅ እንደሆነ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የግል አየር መንገዶች ማኅበር በፕሬዚዳንቱ ካፒቴን አበራ ለሚ አማካይነት ይህ የአውሮፕላኖች ዕድሜ ገደብ እንዲነሳ ጠይቋል፡፡ የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የበረራ ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል፡፡
‹‹ከሃያ ሁለት ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው አውሮፕላን ማስገባት አይቻልም ከማለት ለአውሮፕላኖች የሚደረገውን ጥገና መቆጣጠር፣ ይህ አውሮፕላን ለበረራ ብቁ ነው አይደለም ብሎ መመርመር አይቻልም ወይ?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በአውሮፕላኖች ላይ የተጣለው የዕድሜ ገደብ አቅማቸውን ገና ባልገነቡ የግል አየር መንገዶች ላይ ትልቅ ጫና እንደፈጠረ የተናገሩት ካፒቴን አበራ፣ አዳዲስ አውሮፕላኖች ገዝቶ ለማስገባት የግል አየር መንገዶች አቅም እንደማይፈቅድ ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ልምድ የወሰደው ከእነ ናይጄሪያና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ከመሳሰሉ በአቪዬሽን ደኅንነት መልካም ስም ከሌላቸው አገሮች መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎች ብዙ አገሮች የአውሮፕላን ዕድሜ እንደማይገድቡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለምን ከሌሎች አገሮች ልምድ አይወስድም? የዕድሜ ገደቡን አንስቶ በጥገና ሥራ ላይ ግን ቁጥጥሩን ማጥበቅ ይቻላል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ካፒቴን ሰለሞን በበኩላቸው የተሟላ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል በሌለበት አሮጌ አውሮፕላን እንዲገባ አይመከርም ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ አሮጌ አውሮፕላን ይግባ ብለን አንከራከርም፡፡ ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ አየር መንገዶች ከ22 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው አውሮፕላኖች እንዳያስገቡ ሲከለከሉ፣ የውጭ አየር መንገዶች ያረጁና ያፈጁ አውሮፕላኖችን ይዘው እንደ ልባቸው እንዲሠሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ይህ አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የአገር ውስጥ አውሮፕላኖች የዕድሜ ገደብ 22 ዓመት ከሆነ የውጭ አየር መንገዶች ኢትዮጵያ አምጥተው በሚሠሩባቸው አውሮፕላኖች ላይ 15 ዓመት የዕድሜ ገደብ ሊጣል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጡት ዓለም ፀሐይ መኮንን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዲስትሪ በፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ብሔራዊ አየር መንገዱ፣ የውጭ አየር መንገዶችና የግል አየር መንገዶች በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡
‹‹በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የአቅም ውስንነት አለ፡፡ መጨናነቅ ይታያል፡፡ ያለው አንድ መንደርደሪያ በመሆኑ በርካታ አውሮፕላኖች በአጭር ሰዓት ውስጥ ይነሳሉ ያርፋሉ፤›› ያሉት ዓለም ፀሐይ፣ ተጨማሪ መንደርደሪያ ወይም ተጨማሪ የአውሮፕላን መግቢያና መውጫ ይሠራ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ በሰጡት ምላሽ፣ በአውሮፕላኖች ላይ የሚጣለው የዕድሜ ገደብ የበረራ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ሲባል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ዕድሜያቸው የገፋ አውሮፕላኖች ለአደጋ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ከሚል እሳቤ ወደ አገር የሚገቡ አውሮፕላኖች ዕድሜ እንደሚገደብ የገለጹት አቶ ሽመልስ፣ ለአውሮፕላኖች የሚደረገውን ጥገና መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ‹‹አየር መንገዶች ያላቸውን የቴክኖሎጂና የሠለጠነ የሰው ኃይል ብቃት መመርመር ይቻላል፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በጉዳዩ ላይ ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገሩበት ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርትን መጨናነቅ በተመለከተ መጨናነቁ የሚፈጠረው በተወሰኑ ሰዓቶች ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመንደርደሪያ አጠቃቀምን ማሻሻል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ የፓይለት ማሠልጠኛ ተቋማት በክልል ያሉ ኤርፖርቶችን እንዲጠቀሙ ባለሥልጣኑ በማመቻቸት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ኤርፖርት አዲስ መንደርደሪያ መሥራት ይቻል እንደሆነ የሚያጠና ቡድን ተቋቁሞ ጥናቱ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በግል አየር መንገዶች ባለቤትነት ላይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት በባለሥልጣኑ የአየር ትራንስፖርት ዕቅድ ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ይገዙ የተጠቀሰው ችግር መኖሩን አምነዋል፡፡ ‹‹ለጥቅም ሲሉ በኢትዮጵያዊነታቸው የተሰጣቸውን መብት አሳልፈው የሚሸጡ እንዳሉ እናውቃለን፤›› ያሉት አቶ እንዳሻው፣ በጉዳዩ ዙሪያ የባለሥልጣኑ አመራሮች ቁጭ ብለው መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ችግሩ እነሱን ለመከላከል ብለን የምናወጣው መመርያ ሌላውን የሚጎዳ፣ የግል ኢንቨስትመንትን የማያበረታታ ይሆናል ብለን ስለሠጋን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአብዛኛው ይህ ችግር የሚፈጠረው አውሮፕላን ተከራይተው በሚሠሩ ኩባንያዎች እንደሆነ ገልጸው፣ አሁን ያለው ደንብ አንድ የግል አየር መንገድ ቢያንስ ለስድስት ወራት በኪራይ በሚያመጣው አውሮፕላን እንዲሠራ እንደሚፈቀድለት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን አንድ አየር መንገድ ፈቃድ አግኝቶ ለመሥራት ቢያንስ አንድ አውሮፕላን በግዢ ማምጣት አለበት ብንል ብዙዎችን እንጎዳለን፡፡ ስለዚህ የተሻለ የመፍትሔ ዕርምጃ ለመውሰድ ጉዳዩን በጥናት ማየት ይኖርብናል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡