Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመንግሥት ተቋማት በወቅታዊ ጉዳዮች ተጠምደው ሰነበቱ

የመንግሥት ተቋማት በወቅታዊ ጉዳዮች ተጠምደው ሰነበቱ

ቀን:

በአዲስ አበባ በፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ በአስተዳደሩ ሥር ያሉ መንግሥታዊ ተቋማት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመጠመዳቸው፣ መደበኛ ሥራዎችንና አገልግሎቶችን ከነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እያቆራረጡ ሲያከናውኑ ነው የሰነበቱት፡፡

ወደ መንግሥታዊ ተቋማት ጉዳይ ለማስፈጸም የሄዱ ባለጉዳዮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋማቱ በስብሰባዎች ላይ በመሆናቸው መደበኛ አገልግሎቶችን ማግኘት አልቻሉም፡፡

በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀጣጥሎ የነበረው ተቃውሞ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ላይ በርከት ያሉ አዳዲስና ነባር ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የተስተጋቡባቸው ስለነበሩ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች የየመሥሪያ ቤቶቻቸውን ሠራተኞች ሰብስበው በማወያየት የማረጋጋት ሥራ ሲሠሩ መክረማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

- Advertisement -

ነገር ግን በውይይት መድረኮች ላይ የመንግሥት ተሿሚዎች በተቃዋሚ ሠልፈኞች የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ፣ እንደ ሰላም አደፍራሽ በመፈረጅና በማስተባበል ተጠምደው እንደነበሩ ስብሰባዎችን የተከታተሉ የሁለት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ መንግሥት የተለያዩ ማኅበራትንና ዘርፎችን ሰብስቦ በመጥራት ሲያወያይ መክረሙም ታውቋል፡፡ በዋነኝነት በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ የሴት ፎረሞችና ሊጐች፣ የወጣት ማኅበራትና የንግድ ማኅበራትን ሲያወያይ ሰንብቷል፡፡

በተያያዘ ዜናም በአገሪቱ የተከሰተውን የተቃውሞ ሠልፍ አስመልክቶ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የፌዴራል ፖሊስ ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ ሕወሓት በተቃውሞ ሰበብ የሚንቀሳቀሱ ‹‹የጥፋት ኃይሎችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን እታገላቸዋለሁ፤›› ብሏል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በሁከት ለማፈራረስና የብሔር ብሔረሰብ እኩልነትን የማይቀበሉ የትምክትና የጠባብነት ኃይሎች የሚፈጽሙትን ሕገወጥ ተግባር፣ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመቆም እንደሚታገል የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታውቋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አራተኛ ሙት ዓመት መታሰቢያን አስመልክቶ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ እነዚህ ኃይሎች የሚፈጽሙትን ማንኛውም ተግባር ከእህት ድርጅቶቹ፣ ከአጋር ድርጅቶቹና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ሕዝባዊ ፍርድ እንዲያገኙ አደርጋለሁ ብሏል፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በሰውና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳትም ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማው ገልጿል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአገሪቱ በተከሰቱ ተቃውሞዎች በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑ የተለያዩ አካላትን ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በሁከቱ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑ የተለያዩ አካላትም ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረጉ አስረድቷል። በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርጊት ግን ፍጹም ሕገወጥ ነው ብሏል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ ዓርብ ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹99 በመቶ የሚሆኑት በሕገወጥ ሠልፉ የተሳተፉ ዜጎች በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በቦታው የተገኙ ናቸው፤›› ብለዋል።

የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰርገው በመግባት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚፃረሩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ መስተዋሉንም አመልክተዋል፡፡

በተያያዘም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክልሎች መንግሥትን በመቃወም በሚካሄዱ ብጥብጥ የታከለባቸው ተቃውሞዎች ምክንያት፣ አደጋ ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ ለዜጎቹ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። በስልክና በኢንተርኔት አገልግሎቶች መቆራረጥ ሳቢያ በኢትዮጵያ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ በአገሪቱ ካሉት የአሜሪካ ዜጎች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት እንዳሰናከለበት መግለጫው ጠቅሷል። ይህ ማስጠንቀቂያ እስከ እ.ኤ.አ. የካቲት 2017 እንደሚዘልቅ የማስጠንቀቂያ መግለጫው ይጠቁማል።

የተቃውሞ ሠልፎቹ ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት እንዳስከተሉ መግለጫው ጠቅሶ፣ ተቃውሞዎቹ ሊቀጥሉና ሊስፋፉ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳለ አስፍሯል። በዚህም ተቃውሞው ወደ አዲስ አበባ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁና የተቃውሞ ሠልፎችንና ሰዎች በብዛት ከሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ አሳስቧል።

በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሠልፎች መደረጋቸውንና የሠልፉ ተሳታፊዎችም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸውን ቀጥለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...