Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኛና የመዲናችን ጎዳናዎች

በተደጋጋሚ ትችት ከምናቀርብባቸው፤ ደግመን ደጋግመን በማንሳት መፍትሔ እንዲበጅላቸው ከምንወተውትባቸው ጉዳዮች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እጥረትና የትሪፊክ መጨናነቅ ይጠቀሳሉ፡፡ ለአሽከርካሪውም ሆነ ለትራንስፖርት ተገልጋዩ ራስ ምታት የሆነው ጉዳይ ያለመፍትሔ በመዝለቁ አሁንም የመፍትሔ ያለህ ቢባልበት ተገቢ ነው፡፡

ጭንቅ ጥብብ ያላቸውን የከተማዋን መንገዶች ለማፍታታት የመፍትሔ ያለህ በሚባልበት ወቅት ችግሩን ይበልጥ የሚያባብሱ ክስተቶች እየተፈጠሩ መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያመለክታል፡፡ በጋ ከክረምት ያለእንከን ማሽከርከር የማይቻልባቸው የመዲናችን ጎዳናዎች፣ የሚሸከሟቸው ተሽከርካሪዎች ከአቅማቸው በላይ እየሆኑ መምጣታቸውን ታሳቢ ያደረገ የመንገድ መሠረተ ልማት ተዘርግቷል ማለት ይከብዳል፡፡ ያሉትም በቂ ጥገና እየተደረገባቸው ባለመሆኑ ጉዳዩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጐታል፡፡ በከተማ ጎዳናዎች በቅልጥፍና መንቀሳቀስ ከባድ ሆኗል፡፡

ከ500 ሺሕ በታች እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ተሽከርካሪዎች እንደልብ ማላወስ ያልቻሉት የከተማዋ ጎዳናዎች፣ ወደፊት በላይ በላዩ እየተጨመሩባቸው ሲሄዱ የትራፊክ ጭንቅንቁ እየባሰ፣ እኛም የእንፉቅቅ ጉዞዎችን ለማድረግና በመንገድ ለመንገላታት መዳረጋችን የማይቀር፣ የማይቀረፍ ይመስላል፡፡ ይሁንና መፍትሔ ይኖረዋል ብለን ማሰባችን ግን አልቀረም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ ወደ መስመር እየገቡ ያሉ አውቶቡሶች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታ ያለውን መጨናነቅ አባብሶታል፡፡ ቦታ የሚፈልጉ ትላልቅ ተሽከርካሪዎች ወደ መስመር ሲገቡ ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ ቀድሞ በማሰብ ችግሩ እንዳይከሰት ለማድረግ ስለመታቀዱ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡

ሁለት ወዶ አይቻልምና የአውቶቡሶቹ ሥራ መጀመር የምንፈልገው ነው፡፡ ነገና ከነገ ወዲያም ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡ ካለው የትራንስፖርት እጥረት አንፃር መብዛታቸው እሰየው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው መንገድ ላይ ሲጨመሩ ሊኖር የሚችለው የትራፊክ መጨናነቅ ምን ያህል እንደሚብስ መገመት አያዳግትም፡፡ አዲስ አበባ በተሽከርካሪ ከመጓዝ ይልቅ በእግር መሄድ የሚመረጥባት ከተማ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ በእግር መጓዝ ተገቢ ቢሆንም ከአንዱ የከተማዋ ጫፍ እስከሌላኛው መጓዝ አይታሰብም፡፡ አንድ ኪሎሜትር እንኳ በእግር መጓዝ የማይቻልባት ከተማ መሆኗን ኃላፊዎቿ ይመሰክራሉ፡፡ ይኸውም ለእግረኛም የማትመች፣ የእግረኛ መንገድ በብዛትም በጥራትም የሌላት በመሆኗ ምክንያት ነው፡፡

 እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆነን በቀጣዩ ወር 500 የከተማ አውቶቡሶች የአዲስ አበባን ጎዳናዎች እንደሚቀላቀሉ ተነግሯል፡፡ በተለይ የሸገር አውቶብሶች እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ድረስ ከሁለት ሺሕ ያላነሱ ይሆናሉ፡፡ ሌሎችም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቡሶች በከተማዋ ጎዳናዎች ይታያሉ፡፡ በግል የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው ሁኔታ የከተማዋ አስተዳደር  አሁን ከሚታየው የበለጠ ወደፊት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችለውን ይህንን ጉዳይ ከግምት በማስገባት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አማራጮችን ማየት ያሻል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታዩ መጨናነቆችን በቀላሉ የእግረኛ መተላለፊያ መንገድ በመሥራት ማቃለል እየተቻለ ይህ ግን አይደረግም፡፡ በአደባባዮች አካባቢ የተቦረቦሩ መንገዶችን በቶሎ አለመጠገን ምን ያህል እንደሚያሰቃዩ የሚመለከት አካል በቶሎ ማስተካከሉ ላይ ሊበረታ ይገባዋል፡፡ ሌሎች መፍትሔዎች በፍጥነት መተግበር ካልቻሉ ችግሩ እየከፋ ይሄዳል፡፡ ቢያንስ ጊዜያዊ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ይገባል፡፡

እንዲያው የመንገድን ነገር ካነሳን ሰሞኑን የተመለከትኩትን ተያያዥ ጉዳይ ላንሳ፡፡ የአዲስ አበባ የመንገድ ችግር የትራፊክ መጨናነቅ የመንገዶች መጎርበጥ ብቻ አይደለም፡፡ እግረኞችም ብንሆን ከመንገድ አጠቃቀም ጋር ያለብን ችግር የበዛ ነው፡፡ ለትራፊክ አደጋ ምክንያትም ነው፡፡ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚወሰዱ ጥቂት ዕርምጃዎች  የተጠኑ አይመስልም፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ከቦሌ ወደ ቃሊቲ በሚወሰደው የቀለበት መንገድ አካፋይ ላይ ባማረ ዲዛይን የብረት አጥር እየተተከለ ነው፡፡ ብረቱ ከኮንክሪት ማካፈያው ላይ እየታሰረ ነው፡፡ እስካሁን ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ ተሠርቷል፡፡ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ እሙን ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ሲባል በዚያ መንገድ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ታስቦ ነው መልሱ፡፡

አደጋ ለመከላከል እንዲህ መደረጉ ባይከፋም ከአጥሩ ከፍታ አንጻር ሲታይ ግን አመል ያለባቸውን ዘላዮች አይመልሳቸውም፡፡ ስለዚህ ትርፉ ወጪ ብቻ እንደሚሆን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምናልባት አጥሩ ረዘም ብሎ ስለመሠራቱና ሰዎች በቀላሉ ሊሻገሩት የሚያስችል ቀጣይ ሥራ እንዳለው ባይታወቅም አሁን በሚታየው ግንባታ ግን የታሰበለትን ከማሳካት ይልቅ አደጋውን የከፋ ሊያደርገው ይችላል፡፡

እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር የደፈርኩትም የቀለበት መንገዱን ማካፈያ ዘለው የሚሻገሩ ሰዎች አዲሱን አጥር ከቀደመው ይልቅ በቀላሉ ለመዝለል ያመቻቸው በመሆኑ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንዳስተዋልኩትም አጥሩ እየተሠራ እንኳ ብረቶችን በቀላሉ የሚሻገሩ ነዋሪዎችን አይተናል፡፡ ስለዚህ አዲሱም አጥር መፍትሔ አልሆነም ማለት ነው፡፡ ይህ ሲታይ ለብረት አጥሩ ከወጣው ገንዘብ ይልቅ እዚያው መስመር ላይ አደባባዮች ዙሪያ የተቦዳደሱ መንገዶች ቢጠገኑበት የተሻለ ነበር፡፡ የቀለበት መንገድን ባልተፈቀደ ቦታ መሸጋገር የተዘወተረው በቂ የእግረኛ ማቋረጫዎቹ ባለመሠራታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ብረቱ የእግረኛ መሸጋገሪያ  ቢሠራበት ይመረጣል፡፡ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ከታሰበ አጥሩን ከፍ አድርጎ መስሥራቱ ምን ያግዳል?

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት