ሁለተኛው የሥነ ጥበብ ቅርሶች ካታሎግ
‹‹የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ቅርሶች Ethiopian Fine Arts Heritage›› የተሰኘ ባለሁለት ቋንቋ ካታሎግ ለኅትመት በቃ፡፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተዘጋጀው ቅጽ ሁለት ካታሎግ፣ በሕይወት ያሉና የሌሉ አንጋፋ ሠዓልያንን የሕይወት ታሪክና ሥራ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሥራዎቻቸውን በዐውደ ርዕይ ያቀረቡ ሠዓልያን ገጸ ታሪክና ሥራዎቻቸው ተካትቷል፡፡
ታሪካቸውና ሥራዎቻቸው ከቀረበላቸው ሠዓልያን አገኘሁ እንግዳ፣ አለ ፈለገሰላም፣ ይገዙ ብስራት፣ ለማ ጉያ፣ ገብረክርስቶስ ደስታና አፈወርቅ ተክሌ፣ ታዬ ወልደመድኅንና ደስታ ሐጎስ ይገኙበታል፡፡
በቅጽ ሁለት ካታሎጉ መግቢያ እንደተመለከተው፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የአገሪቱን የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ከማሰባሰብና ከማደራጀት በተጨማሪ ሥራዎቹን በካታሎግ እንዲታተሙና ለተጠቃሚዎች የማዳረስ ተግባሩን ይቀጥላል፡፡