Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልቡሔ ሲነሳ

ቡሔ ሲነሳ

ቀን:

በፍቅርተ ተሾመ

‹‹ክፈት በለው በሩን የጌታዬን

መጣና ባመቱ ኧረ እንደምንሰነበቱ …››

በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረውን የቡሔ ወይንም ደብረ ታቦር በዓልን ምክንያት በማድረግ በዋዜማው ነሐሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. አባቶችና እናቶች ያቆዩትን ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ለመዘከር ብሎም ለትውልድ ለማስተላለፍ በማመን በባላገሩ አስጎብኚና መኪና ኪራይ አዘጋጅነት በጣይቱ ሆቴል በተለያዩ ባህላዊና ትውፊታዊ መርሐ ግብሮች ተከብሮ ውሏል፡፡

ባህላዊ ልብሶችን በመልበስ ደበሎውን ደርበው ዱላቸውን ይዘውና ጅራፋቸውን በአንገታቸው ላይ ያነገቡ ታዳጊ ወጣቶች በጅራፍ ጩኸት የታጀበውን የሆያ ሆዬ ጭፈራቸውን ለበዓሉ ድምቀት በሚሰጥ መንገድ አቅርበዋል፡፡

የመድረኩ መሪ አቶ ተሾመ አየለ ስለ መርሐ ግብሩ ሲገልፁ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩ የሆነ የማይሸረሸር የማይደፈር ቱባ የሆነ ባህል አለን፡፡ አሁን ጊዜ ልጆቻችን እየተከተሉ ያሉት የውጪውን ባህል ነውና ባህላችንን ለልጆቻችን ለማስተማር የራሳቸውን እንዲያከብሩ ለማድረግ ቡሔን በተለያየ ጊዜያት በተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞች አጅበን እናዘጋጃለን፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በከተሞች አካባቢ ልጆች ቡሔን መለመኛ አድርገውታል፤ የራሱ ሥርዓት አለው፤ ልመና አይደለም መሆንም የለበትም፤ የሚሰጠውም ገንዘብ ሳይሆን ሙልሙል ከነኮባው ነው፤ ግጥሙም ድንበር የዘለለ ኢትዮጵያዊ ለዛ የሌለው ነው ሲሉ ያስተዋሉትን ገልፀዋል፡፡

ይህንንም ባህል ለማሳሰብ ዕለቱን የተመለከቱ መንፈሳዊ መዝሙሮች ፣ የጅራፍ ማጮህ ውድድር፣ የአባቶች ምርቃትና ችቦ የማብራት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ታቦር በዓል የሚከበረው በመንፈሳዊ መልኩ ሲሆን፣ ትውፊታዊ ይዘቱም እንዳለ ነው የሚሉት የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ስብከተ ወንጌል ኃላፊው መምህር ስሙር አላምረው ናቸው፡፡  በመሠረታዊነት ቤተክርስቲያን በዓሉን የምታከብረው ከኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

ታዲያ ልጆች ለዝማሬያቸው ዋጋ ሙልሙሏቸውን ለመቀበል

… የዓመት ልምዳችን ሆ ከጥንት የመጣ

ከተከመረው  ተመሶብ ይውጣ

…የተጋገረው ሆ ሙልሙሉ ይውጣ

በማለት ሙልሙላቸው እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡

አሁን አሁን ባይጠፋም እንኳ እየቀነሰ ይምጣ እንጂ እናቶች የጋገሩትን ሙልሙል ለጎረቤት ልጆች ወስደው ይሰጣሉ፤ አልያም ይልካሉ፡፡ ይህም በትውፊት የመጣ መሆኑን መሆኑን መምህር ስሙር ይናገራሉ፡፡ ክርስቶስ ብርሃኑ በተገለጠበት ጊዜ ጨለማውን ገፍቶት ነበርና ከብቶቻቸውን የሚጠብቁ ሕፃናት ጨለማውንና ብርሃኑን ሳይለዩ ተገርመው በዚያው ስለቀሩ እናቶቻቸው ልጆቹ የቀሩት ምን አግኝቷቸው ነው በማለት ሙልሙል ይዘው ሄደው ጠይቀዋቸዋል፡፡

‹‹… ፊቱ እንደ ፀሃይ  በርቶ የታየው

ልብሱ እንደ ብርሃን   ያንፀባረቀው

ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና

የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣልን…›› እያሉ በመዘከር ይዘምራሉ፡፡ ይህ ብርሃን ሲገለፅ በደመና ሆኖ የተሰማው ድምፅ በአከባቢው ለነበሩት ሁሉ ከዚህ ቀደም ሰምተውት የማያውቁት ለጆሮአቸው የከበደ ነበርና ደንግጠው ወድቀዋል፡፡ ዛሬም ይህን ነጎድጓድ ድምፅ ለማሰብ ጅራፍ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እነደሚሰማ መምህር ስሙር አያይዘው አመጣጡን ያስረዳሉ፡፡

ጅራፍ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል በአዘቦት ቀናት እረኞች ከብቶችን ለማገድ የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ልጥ ተልጦ ቃጫ ተፍቆና ተገምዶ የሚዘጋጅ ነው፡፡

ቡሔ ከተራራው ስያሜ ጋር በተያያዘ ደብረታቦር ይባላል፡፡ ቡሔ ለሚለው ስያሜ ደግሞ የተለያዩ የስሙ መነሻ ሐሳቦች ይነሳሉ፡፡ አንደኛው ወቅቱ ለክረምቱ ማለቅ ዋዜማ እንደሆነና ከደመናማው ጨለምለም ከሚለው የክረምት ወቅት ወጥቶ ብርሃን የሚመጣበት በመሆኑ ብርሃኑን ወቅት ሲያመለክት ነው፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንደሚባለው ሁሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ቡሔ ማለት መላጣ ሲሆን፣ ገላጣ የሚል መልክ ሲኖረው  ወቅቱን አመልካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተጨማሪም ቡሔ (ቤሔእየ) ሲባል ይኽም የቡሔ ዕለት የሚጋገረው ሙልሙል ያለ እርሾ መጋገሩን ይጠቁማል፡፡ እንዲሁ ሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ይነሳሉ፡፡

ቡሔ ሲመጣ የሚታወሰው ሌላኛው ነገር ችቦ ነው፡፡ በመዲናዋ እንደሚስተዋለው ችቦ በሚበራባቸው በዓላት ከመኖሪያ ቤቶችና አብያተ ክርስቲያናት ባለፈ ሰዎች በመዝናኛ አካባቢዎች፣ በመሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተሰብስበው ያበራሉ፡፡ በዚህ በዓል ችቦ ትውፊቱና ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ እናቶች ልጆቻቸው ጠፍተውባቸው ፍለጋ በወጡ ጊዜ ችቦ ይዘው እንደሄዱ ሁሉ ችቦው መብራቱ ለዚህ ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ከዘመን ዘመን ተሻግሮ እዚህ የደረሰው የቡሔ በዓል በሕፃናት ወንዶች ሆያ ሆዬ ጭፈራ ፡-

‹‹… አባቴ ቤት አለኝ ለከት  እናቴ ብት አለኝ ለከት

አጎቴም ቤት አለኝ ለከት  ተከምሯል እንደ ኩበት››

እያሉ ከእናቶች ሙልሙል በመቀበል፣ በአባቶች ምርቃትና በጋራ ችቦን በማብራት በየዓመቱ የሚከበረው በዓል ከዚህ ውጭ መልኩን መቀየሩ ዘወትር ሕመም እንደሚፈጥርባቸው አቶ ተሾመ  ይናገራሉ፡፡

በዕለቱ ከተገኙት እንግዶች መካከል የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ ታገል አድማሱና አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ይገኙበታል፡፡ የባህል ሙዚቃ ተጫዋቹ መምህር ዓለማየሁ ፋንታ በዓሉንና እንዲሁም የነሐሴ 12 ቀን የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ልደት አሰስመልክቶ መዲና ዘለሰኛ ተጫውተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...