Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየጄኔራል ፃድቃን ጽሑፍ ነሸጠኝ!

የጄኔራል ፃድቃን ጽሑፍ ነሸጠኝ!

ቀን:

እኔም ዴሞክራሲንና ሰላምን በመጨበጥ ላይ የምለው አለኝ!

በታደሰ ሻንቆ

‹‹ዴሞክራት ነን የምንል የትግራይ ልጆች ወዴት ነው ያለን? በሻዕቢያ የጠላትነት ዘመቻና በኢሕአዴግ ወያኔ የተሳሳተ አካሄድ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ከላይና ከታች እየተጣበቀ መሆኑ ሊያባንነን አይገባም? … አንድ ግለሰብ እከሌ እንዲህ ብሎ ተሳደበ በሚል ጠብታ ወሬ ሊያባላ የሚችልበት አደጋ እንዳለ አይታየንም? … ሕዝቦች ከዚህ ዓይነት አደጋ ጋር እንዲኖሩ ፈቅደን እንዴት ለሕዝብ ቆመናል ማለት ይቻለናል?›› ይህ ቃል በ1999 ዓ.ም. በኢንተርኔት ከተሠራጨ የሰሚ ያለህ የሚሰኝ (የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከደርግ እስከ ኢሕአዴግ የገመገመ) ጽሑፍ ላይ የተወሰደ ነው፡፡

ይህ ችግር ከመድበስበስ ተላቆ አሁን በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ፊት ለፊት ለመነሳት መብቃቱ፣ ቢዘገይም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ወሳኝ ዕርምጃ ነው፡፡ ይህ ግን አንድ ሁለት ጽሑፍ በመወርወር የሚገላገሉት ኃላፊነት አይደለም፡፡ ዛሬም የትግራይ ዴሞክራቶች ጥላቻንና ለጥላቻ መፍለቂያ የሆነ የአገዛዝ መንሻፈፍን በመቃወም ግንባር ቀደም አለመሆን የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ በጣሙን ያጎድላል፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ እንደ ሌላው ተጎጂ ከመሆኑ በላይ የመዘዘኛ ጥላቻም ዒላማ ስለተደረገ፣ ይህም ጥላቻ ሕወሓቶች በግልጽም ሆነ በስውር ከሚቆጣጠሩት አገዛዝ ወደ ሕዝቡ ያለኃጢያቱ የተሸጋገረ ስለሆነ ነው፡፡

ሕወሓት ኢሕአዴግ ገና ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ ላይ በነበረት ጊዜ ለብቻ መሮጥ በቀላሉ የማይነቀል መዘዝ እንዳለው ያስጠነቀቀም የእንግሊዝኛ ጽሑፍ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እንደተሰጋው ሌላ ነፍጠኛ፣ ሌላ ባዕድ መጣብን የሚል ቅዋሜ የተከሰተው ወዲያው ነበር፡፡ አዲስ አበባም ተገብቶ ጊዜያዊ መንግሥት ቢባል፣ የሽግግር ቢባል፣ ወይም ኢፌዴሪ ቢመሠረት፣ በመሠረቱ የአገዛዙ ቅንብር ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖችን በአጃቢነት ከመጠቀም ብዙም አለማለፉ መዘዙ እስከ ዛሬ ዕድል አግኝቶ የአገሪቱን ፖለቲካና የሕዝብን ኅሊና እንዲመዘምዝ ረድቶታል፡፡ የዴሞክራሲ ዕድል የተሰናከለው፣ አምባገነንነትም የተዋቀረው ገና ከመነሻው እንጂ እነፃድቃንና እነገብሩ አሥራት ሲፈነቀሉ አልነበረም፡፡ ለዴሞክራሲ የቆምኩ ነኝ ብሎ ከልብ የሚያምን ቡድን በፀረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ላይ ቁጢጥ ሲል፣ ወይም አገዛዙን ንዶ የፀረ ዴሞክራሲ ወገኖች እንዳያገግሙ ሆነው እስኪዳከሙ በኃይል ልግዛ ሲል መቼውንም አብሮት የሚኖር አደጋ አለ፡፡ ለዴሞክራሲ ፀር በሆኑ ወገኖች ተፈንቅሎ ወይም ተሰርስሮ የመፈንገል አደጋ፣ ወይም በሥልጣንና በድሎት ጥፍጥና ነፍዞ በዚያው የመቅለጥ አደጋ፡፡ ተፈንቅሎም ሆነ ራስ ዘቅጦ ፀረ ዴሞክራሲነት ውስጥ ከመግባት የማምለጫው ብቸኛ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ደመናና የአገዛዝ አደረጃጀት ውስጥ  በቶሎ መግባት ነው፡፡ ይህን  እውነት ማጤን ዛሬም አስፈላጊያችን ነው፡፡

ዛሬ የሚያስጨንቀን የተንሻፈፈ የአገዛዝ መዘዝ ሳይነቀል 25 ዓመታት መቀጠሉ ከመሆንም ዘልሏል፡፡ ጥላቻ ከብሶቶች ጋር ተወሳስቦ ከባድ ፍንዳታ ለመፍጠር እየተንደረደረና በሄድ—መለስ ዘይቤ ግፊትና ቁጣ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ በዚህ አደገኛ የገሞራ መሰናዶ ውስጥ የኢሕአዴግ መንግሥት ግማሽ እንቅልፍ ዓይነት ነገር ውስጥ እየናወዘ ነው፡፡ ልጆችና ሽማግሌዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ የሚታይ ነገር አለ፡፡ ተቀምጠው በእንቅልፍ እየተንገላጀጁ ሳሉ ተነስ ተኛ ሲባሉ አይ እቆያለሁ ይላሉ፡፡ እያንቀላፋህ አይደል ሲባሉ ደግሞ አይ አላንቀላፋሁም፣ ዓይኔን ከድኜ ነው በማለት ንቁ ለመምሰል ይጣጣራሉ፡፡ ኢሕአዴግም ያለበት ሁኔታ የዚያ ዓይነት መሳይ ነው፡፡ ፖለቲካው ልብ መንካት ተስኖታል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነኝ፣ ዴሞክራሲን እየገነባሁ ነው ባይነቱ የምድረ በዳ ስብከት ከሆነና መሳቂያ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ተቃዋሚንና ተቃውሞን የፀረ ሰላሞችና የውጭ ጠላት መሣሪያዎች ሥራ አድርጎ የመወንጀል ፈሊጥ ከተያዘ (የደርግ 17 ዓመት በኢሕአዴግ 25 ዓመት ላይ ተደምሮ) 42 ዓመታት ሆኖታል፡፡ በዱሮ በሬ የማረስ አሮጌነት ማለት እንደዚህ አይሆኑ መሆን ነው፡፡ የሕዝብ ድጋፍ አለን ባይነቱና በግንቦት 2007 ዓ.ም. ከአጋሮቹ ጋር መቶ በመቶ ተቃዋሚን ዘርሮ ‹‹የተመረጠበት›› ክንዋኔ፣ መርምሮ አጣሪ ሳያሻው ገና ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቅዋሜ በቅዋሜና መዘባበቻ ሆኖ አርፏል፡፡

ኢሕአዴግ አዙሮ አለየው እንደሆነ እንጂ፣ የዚህ ዓይነቱ ተጋላጭነት በአመፅ መጣል ሕገወጥ ነው ብሎ ለመከራከርና ለመርታት እንኳ ፖለቲካዊ አቅም የሚያሳጣ ነው፡፡ የሕዝብ ወገንተኛ ነኝ ባይነቱም ሲመች በምናምኑ ሕዝብን እየሸነገሉ የፖለቲካ አጫፋሪ ማድረጊያ፣ አልመች ሲል ደግሞ ሕገወጥና ፀረ ሕዝብ እያሉ መሸንቆጫ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ሕጋዊ መንገድን ሳያሟሉ የአደባባይ ሠልፍና ስብሰባ መውጣት በፀጥታ ኃይል በኩል ጥይት መጠቀምን ተገቢ የሚያደርግ ከመሰለ ቆይቷል፡፡ ለሕዝብ አሳቢ መሆን ሕዝብ ተቃውሞ ውስጥ በመግባት አለመግባቱ ወይም ሕገወጥ ሠልፍ በማድረግ አለማድረጉ የሚሰፈር አይደለም፡፡ ሕጉ ሠልፍ ሲያስቡ ማሳወቅን ብቻ የሚፈልግና የሚመለከተው አካል ዝም ካለ እንደተፈቀደ የሚቆጠር ነው፡፡ ይህን መብት የሚንከባበከብ መንግሥት ካለ ለፀጥታ ዝግጅት ጊዜ ቢያጥረው በዚህ ቀን አድርጉት ብሎ ቁርጥ ያለ ነገር ይናገራል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት በተለይ ከ97 ምርጫ በኋላ ይፈጽም የነበረው የማይፈልገውን ሠልፍ በሰበብ አስባብ እንዳይካሄድ ማዳፈን ነው፡፡ በአንድ  ወቅት እንዲያውም የሠልፍ መብትን ፈቃድ የመስጠትና የመከልከል ጉዳይ አድርጎት ነበር፡፡

ከዚህ ልምድ ተነስቶ ለቅዋሜ የሚወጣ ሕዝብ ሳያሳወቅ ሠልፍ ቢወጣ ምን ያስገርማል! ሥልጣን ሙጥኝ ያለው ኢሕአዴግም የሠልፍ መብትን ቢያወላክፍ፣ ሠልፍ የሚባለው በኃይል ሥርዓቱን ለመጣል ነው ብሎ ቢፈራም አይፈረድበትም፡፡ የሠልፍ መብትን እንደ ልብ ቢለቅ በአገሪቱ ሙሉ የቅዋሜ ሠልፍ ያጥለቀልቀዋል፡፡ ያጥለቀለቀ ሠልፍ ደግሞ ካልወረድክ ሞቴ ነው ወደ ማለት ሊዞር እንደሚችል በሌላው እያየ ነው፡፡ በአጥለቅላቂ ሠልፍ ከመጠመድ በፊት ችግሮችን ለምን አይፈታም እንዳይባልም ዋነኞቹ ችግሮች ቀጥታ የራሱን የተዛባ የሥልጣን አደረጃጀትና አሠራር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ከቡድን ፈንታ ለሕዝቦች የሚታመን፣ በሕዝቦች ፈቃድ ሥር የሚኖር (በገለልተኛ ተቋማት ላይ የተዋቀረ) ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ባለበት ሠልፍ አሳውቆ መውጣትም ሆነ አደባባይ መሰብሰብ መከራ አይሆንም፡፡ ጥያቄዎች ከአደባባይ በፊት ተሰሚነት የማግኘት ዕድል ስላላቸው ሠልፍ አያስፈራም፡፡ ሕዝብን ግን መንግሥትን መፍራቱ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ለጥያቄዎችና ለችግሮች ጆሮ የሌለው መንግሥት እስከ መውረድ የሚደርስ ቅጣት አለበትና፡፡

      ዛሬ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚፈልጉት የዚህ ዓይነት አገዛዝ ነው፡፡ ግን እንዴት? መላ ሕዝቦችን የተቃውሞ ፓርቲ ወይም ግንባር አትምሞ ወደዚያ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ያደርሰናል አይባል ነገር የሕዝቦችን ቀልብ ሰብስቦ የያዘና ማንቀሳቀስ የቻለ የለ፡፡ በአጥላቅላቂ የተቃውሞ ፍንዳታ ያለውን መንግሥት በታትኖ ወደ ዴሞክራሲ በመድረስ ዘዴ ላይ አንተማመን ነገር ወደ ባሰ አዘቅት ሊያንሸራትት የሚችል ጣጣችን ብዙ ነው፡፡ ‹‹ያለኔ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስብ የለም፣ ተቃዋሚ የጥፋት ኃይል ነው፤›› የሚለውን የሥልጣን ስስት ፕሮፓጋንዳ እንርሳው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የገዛ አገሩንና ወገኑን ይሁነኝ ብሎ ለማጥፋት እንቅልፍ ሲያጣ የሚያድር የጤነኛ እርጉም ፖለቲከኛ እንደሌለም ዕውቅ ነው፡፡ የውጭ ጠላት ሰላማችንን የሚያጠፋው ቀዳዳ እስካገኘ ድረስ ነው፡፡ ዋናው ጠላታችን የገዛ ገመናችን ነው፡፡ በተበጣጠሱ የፖለቲካ ፍላጎቶች መከፋፈላችንና በጥላቻዎች መመዝመዛችን ትልቁ ገመናችን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ሥልጣን ለማርዘም ቢሆነኝ ተብሎ ከገዥ ቡድን ሊመጣ የሚችል በግርግር አስደንብሮ ፀጥ የማድረግ ታክቲክ ወይም ከተቃዋሚ በኩል ግርግርን እንዳቋራጭ የለውጥ መንገድ የመጠቀም ሙከራ የማይጠፋ የፖለቲካ ቀውስ ማቀጣጠያ ሊሆን ይችላል፡፡ የውጭ ጠላት ሰርጎ-ገብም የጥላቻ ገመናችንን የእርስ በርስ ፍጅት መለኮሾ አድርጎ በቀላሉ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

ይህንን እንተወውና ራሳችን በምናካሂደው ተቃውሞ ውስጥ፣ በውስጣች ተሸፋፍነው የቆዩ የገዛ የጥላቻ ዝንባሌዎቻችንን ደም ፍላት አስክሮ ሊታረም ወደማይችል መባላት ውስጥ ሊወስደን ይችላል፡፡ የዚህን አደጋ ምልክቶችም በዚህ ዓመት በታዩት የጎንደርና የኦሮሚያ ተቃውሞዎች ውስጥ ዓይተናቸዋል፡፡ በቀላል ብልጭታ ሊለኮስና እንደ ቋያ እሳት ሊዛመት የሚችል ገመና ይዘን በደርግ ዓይነት አወዳደቅ አገዛዝን ከነሠራዊትና ከነፀጥታው ንዶና በታትኖ እንደገና በመገንባት ዓይነት ዴሞክራሲን ማቋቋም ከከፋ አደጋ ጋር ቁማር ጨዋታ መግጠም ነው፡፡ ከራሳችን ውስጥ ከሚነሳ ትርምስና እሳት ሌላ፣ ከላይ የሻዕቢያ መንግሥት ቂምና የዓባይ ግድብን የህልውናዬ ጠንቅ ያለ ስውርና ግልጽ የተንኮል፣ ምናልባት ከግርጌ የአልሸባብ ቂም፣ ከጎን ወደኛ ሊፈስ የሚችል የደቡብ ሱዳን ትርምስ፣ ዙሪያውን ደግሞ ግርግርና ቀውስ እያነፈነፈ በብርሃን ፍጥነት ሰተት ብቅ የሚለው እስላማዊ አሸባሪነት፣ ይህ ሁሉ ከመዘማመዱ በፊት ገና መታመስ ሲመጣ ኢኮኖሚያችን ላይ የሚደርሰው ስብራት በመከራ የተጀማመረ የውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት መበርገግ፣ የቱሪዝም ገቢ መድረቅ፣ የልማት አውታራት ለውድመት መጋለጥ፣ ወዘተ ወዘተ… ሻል ካለ ግብፅ የገባችበት ዓይነት ማጥ ውስጥ መግባት፣ ባስ ካለ የእነ የመን ዓይነት በውስጥ ክፍፍልና በውጭ ኃይሎች አማሽነት በሚዘወር ፍዳና እልቂት መቆላት …

      ይህን ዓይነቱን አደጋ ከመጋበዝ የኢሕአዴግን አገዛዝ ባልተለወጠ ዘይቤውም ቢሆን እንዳመጣብን እንቻለው አይባል ነገር፣ እንዲህ ያለ ውሳኔ ለሚጠራቀም ብሶትና ምሬት መገነዣ አይሆንም፡፡ መፍትሔ ያጣ ምሬት ምናባቱ ይለይለት የሚል ጭፍን ቁጣንና ፍንዳታን ይወልዳል፡፡ ለፍንዳታ የሚሰጥ የቆመጥና የጥይት ምላሽ ለጊዜው ቅዋሜን ቢበታትንም እንደገና ኃይል አጠራቅሞ ወይም የባሰ ይባስን አጋግሞ የገዘፈ ሌላ ፍንዳታን ይወልዳል፡፡ ከኃይል ዕርምጃ በመለስ የምናየው መንግሥታዊ አያያዝ ተስፋ የሚሞላ አይደለም፡፡ የቅዋሜ መበራከትና መቆራቆራስ የመጣው ከሃይማኖት ትምህርት ማነስ ይመስል የሃይማኖት አባቶችን ስለሰላም ስበኩ ማለት ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ የለኝም እንደማለት ያለ ነው፡፡ የቢቸግር መላ እርጉዝ የማግባት ዓይነት፡፡ ከፀጥታ ቁጥጥር፣ ማሳደድና እስራት በመለስ የሕዝብ ኮንፈረንስ እያሉ መነዝነዝም ተቃውሞ የማኮላሸት ተልዕኮ ያለው የአዕምሮ አጠባ ተግባር ነው፡፡ እስካሁን ከምናየውም እንደታሰበው የተዋጣለት እጥበትን ከማስገኘት ይልቅ፣ ከማሾፊያነት አለፈ ቢባል መልሶ ቆሽት የሚያሳርር ውጤቱ የበለጠ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ
ዓይነቱ ፕሮፓጋንዳዊ ድቆሳ ጋር ከተዋዋወቀም 42 ዓመታት ሞልቶታልና በዚህ ቢመረር አያስገርምም፡፡ በአጭሩ ኢሕአዴግን መሸከምም የጠራ አቅጣጫ ከጎደለው (ግብታዊ) ፍንዳታ አያድንም፡፡ የአዲስ አባባ ከተማን ከዙሪያው የኦሮሚያ ከተሞች ጋር የማልማት መርሐ ግብርን  በመጠራጠር ሰበብ ከተከፈተው ቅዋሜ አንስቶ እስካ ዛሬ የተከሰቱት የቅዋሜ ቁጣዎች ከጊዜ ጊዜ ክረትና ስፋት እየጨመሩ መምጣታቸውን ልብ ላላም ወደ አጥለቅላቂነት ያደገ ቁጣ ሩቅ አንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡

      አጥለቅላቂ ፍንዳታ ቢመጣም ኢሕአዴግ ደቁሶ፣ ልማት የድጋፍ ሲሳይ እስኪያበዛለት ድረስ ለጥ ሰጥ አድርጎ ለመግዛት የሚያስችል የፀጥታ ኃይል ጥንካሬ አለው ብለን ማሰብም ሌላ የሎተሪ ጨዋታ ነው፡፡ አሁን አሁን የምንሰማቸው አንዳንድ ነገሮች መያዣ መጨበጫም የቸገረ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ የባህር ዳሩ የነሐሴ 1 ሠልፍ ከመካሄዱ አስቀድሞ ሰማያዊ ፓርቲ ሠልፉ ቀርቷል ለማለት ምክንያቴ ያለው አስተዳደሩ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የፀጥታ ጥበቃ ማድረግ አልችልም ብሎኛል የሚል ሆኖ ሳለ፣ ምክንያቱን ሐሰት ሳይሉ ከአማራው መስተዳድር በኩል ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ የጠራውን ሠልፍ በኃላፊነት መምራት ነበረበት፣ ለጠፋው ሕይወትና ንብረት ተጠያቂ ነው፤›› መባሉ፣ ‹‹ሕገወጡን›› ሠልፍ ማካሄድ ነበረበት  ከማለት ያልራቀ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ሠልፉ ‹‹ሕገወጥ ነው›› ብሎ ዕርምጃ መውሰድ በሌላ በኩል ለወንጀላ ቢመቸኝ ብሎ አይቻልም ያልኩህን ሠልፍ ለምን በኃላፊነት አልመራህም፡፡ በዚህ ላይ ያስተኮሰና የተኮሰን ትቶ ሠልፍ ጠሪን ለጉዳት ተጠያቂ ማድረግ፡፡ ሠልፍ ሕገወጥ ሆነ አልሆነ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከአደጋ መጠበቅ ከማንም በላይ የፀጥታ ኃይል ኃላፊነት መሆኑ መቼ ይሆን የማዕዘን ድንጋይ የሚደረገው? ሌላ ልጨምር፡፡ የወልቃይት ወደ ትግራይ መካተት የሕዝብ ይሁንታን መሠረት አድርጎ የተከናወነ ይመስል፣ ገጠርና ከተማን ላገናኘው የጎንደር ቅዋሜ መነሻ የሆነው የወልቃይት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ከአንዳንድ የኢሕአዴግ መንግሥት ሰዎችና ደጋፊዎች አካባቢ ‹‹የወልቃይት ጥያቄ የሚባል የሕዝብ ጥያቄ የለም፣ የግለሰቦች/የኮሚቴ ነን ባዮች ጥያቄ ነው፤›› የሚል ነገር እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ ይህንን የሚሉ ሰዎች የወልቃይት ነገር ቱግታ ሲፈጥር፣ ውስጥ ለውስጥ ሲያብከነክንና ጥላቻ ሲያመርት መኖሩ ተሰውሯቸው ነው? ከዚህ ይልቅ ችግራቸው የሚይዙ የሚጨብጡትን የማጣት ይመስላል፡፡

      ችግሩ በትክክል ካልተጤነ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዳያስፖራ የባህር ዳር በዓል ላይ ተጠይቀው የወልቃይት ጉዳይ በቅርቡ መልስ ያገኛል ስለማለታቸው በመገናኛ ብዙኃን የተነገረው እንኳ የትግራይንም፣ የወልቃይትንም፣ የጎንደርም ሕዝብ መልካም ግንኙነት በሚጠግንና የሁሉንም አመኔታ ባገኘ መልክ መልስ የማግኘቱ ነገር ያሳስባል፡፡ ለአንድ ገዥ ፓርቲና መንግሥት በሕዝብ ለመታመን መቻልና የፖለቲካ ተቀባይነት ማግኘት ለአስተዳደራዊ ህልውናው መቅኒንና ደም ማለት ነው፡፡ ፖለቲካው ከደረቀና ሕዝብ አመኔታ ከነሳው የፀጥታ ኃይል ጥንካሬ የወፍራም ፀጉር ብጤ ይሆናል፡፡ ውስጥ ለውስጥ የመነመነ ፀጉራም እንስሳ አለ ሲሉ ሽው ይላል፡፡ በዚህ ረገድ በድንገተኛ የቁጣ ፍንዳታ የመጥለቅለቅ መቃረብን ስናሰብ ኢሕአዴግም ድንገት መዝረክረክ አፋፍ ላይ መድረሱ፣ የኢትዮጵያም ሕዝቦች በዴሞክራሲ ወይ በመጠፋፋት አፋፍ ላይ መድረሳቸው ይሰማናል፡፡

      የመጠፋፋት ዕድልን አምክኖ ዴሞክራሲን የመቀዳጀት ዕድልን የምንይዘው በምን መንገድ ነው? እስካሁን እንደተነጋገርነው ዝምታ፣ የሃይማኖት መሪዎች ስብከት፣ የኢሕአዴግ ኮንፈረንስ፣ ኢሕአዴግን በጭፍኑ መሸከምም ሆነ የይለይለት አመፅ አያዋጣንም፡፡ እናስ? አስተማማኙ ጎዳና፡- የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ከመናጋት/ከመፍረስ አደጋ ጋር ሳይገናኝ፣ የአገሪቱ የመረጃና የደኅንነት አውታርም የአገሪቱን የልማት ሀብቶች፣ የሕዝቦችን ደኅንነትና ሰላም ነቅቶ ከመጠበቅ ላንድ ጊዜም ሳያቋርጥ ከገዥ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ደባል አገልጋይነት እንዲላቀቅ፣ በአጠቃላይም የተክለ መንግሥቱ (የስቴቱ) አውታራት ገለልተኛ ባህርይን እንዲጎናፀፉ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ተግባር መፈጸም የሚቻለው ደግሞ ኢሕአዴግና የተቃውሞ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ተገናኝተው አብሮ ለመሥራትና የተክለ መንግሥቱን መንሻፈፍ ለማቃናት (ዴሞክራሲን ለመደልደል) ከተስማሙ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ መሰንዘር የተጀመረው በእኔ ወይ በጄኔራል ፃድቃን አይደለም፡፡ ገና ገና ቀደም ብሎ በተለያየ መልክ እንደራደር፣ ተባብረን እንሥራ፣ አገሪቱ እርቅ ያስፈልጋታል፣ ወዘተ. ሲባል ነበር ያውም ልመና ቀረሽ፡፡ ዛሬም ከድርድር እስከ እርቅ ኮሚሸን ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ የትጥቅ ትግል ጀምረናል ላሉት ምክንያት የሆናቸውና ሰሚ ለማግኘት የተመቻቸው የድርድር በርን የሚከፍተው መታጣቱ ነው፡፡ አሁንም በሩ ከተከፈተ ጠመንጃ ያነሱትም ቢሆኑ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መሰብሰባቸው አይቀርም፡፡

      የድርድርን በር ከፍቶ አገሪቷንና ሕዝቦችን ከአሳሳቢ አደጋ በማትረፍ ረገድ የዘገየው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ለሕዝቦች ሰላምና ልማት አሳቢ ከእኔ በላይ የለም ባይነቱ እውነተኛ መሆንና አለመሆን የሚታይበት ምዕራፍ ይህ ጊዜ ነው፡፡ ተደራድሮ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ከተቃዋሚ ጋር መሥራትን ይደር ይቆይ የሚያስብል አንዳችም ማመካኛ የለም፡፡ ልማቱ ራሱ በትርምስ ያለመረበሽና ያለመውደም ዋስትና የሚያገኘው ፖለቲካው ሲስተካከል ነው፡፡ የልማት ተቋማትን መተናኮል ይቅርና የእርስ በርስ ብጥብጥ ውስጥ እስከመዘፈቅ የሚያስፈራ አዝማሚያ ከላያችን እያንዣበበ ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ኢሕአዴግ የጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሔን ያላነሳ መቼ ሊያነሳ ነው? እንደ ደርግ በሬሳው ሲቀር? ወይስ ከቁጥጥር የወጣ የመተላለቅ ምዕራፍ ውስጥ ከተገባ በኋላ? ከስድስት ሚሊዮን አባላት ውስጥ ጎበዝ አንድ መላ እንበል የሚል ታጣ?

      ኢሕአዴግ ‹‹ፀረ ሰላሞች ሕዝብን ሊያበጣብጡና ሕገ መንግሥቱን በኃይል ሊያፈርሱ ነው፤›› እያለ በተደጋጋሚ ይጮኸል፡፡ እኔ ደግሞ ፍርጥ አድርጌ ልናገርና፣ ከማንም በላይ ሕገ መንግሥቱን በኃይል እንዲፈርስም ሕዝቦች እንዲበጣበጡም እያጋለጠና እየጋበዘ ያለው ራሱ ኢሕአዴግ ነው፡፡ እንዴት? ለድርድርና አብሮ ለመሥራት መፍትሔ ጀርባ ሰጥቶ፣ ከሽንገላ እስከ ጥይት በሰፉ የአፈና ዘዴዎች ቅዋሜንና መተናነቅን በማጥበቅ፣ ራሱንም አገሪቱንም ሊበላ የሚችል መከፋፈልና ግብታዊ ነውጥ ኃይል እንዲያከማች ሳያውቀው እያገዘ ስለሆነ፡፡ የዚህ ዓይነቱ የትርምስ ምናልባት የሚያሳስበው ሁሉ ይህንን የመጨረሻ ነጥብ የትግል ሁሉ ውል አድርጎ ሊወስደው ይገባል፡፡ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የመምጣትና ተባብሮ የመሥራት ጉዳይ ከመበጣበጥና ከመተላለቅ የመትረፍና ያለመትረፍ ጉዳይ ሆኗልና፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝቦችና  ለዴሞክራሲ የተጨነቀ አሳቢነት ለጋዜጣ ጽሑፍ ከመወርወር ወይም መግለጫ ከማውጣት ማለፍ አለበት፡፡ ከዳር እስከ ዳር የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለሰላማዊው መፍትሔ እንዲቆሙና ኢሕአዴግን የሚረታ ግፊት እንዲያደርጉ ወደሚያስችል እንቅስቃሴ መለወጥ አለበት፡፡ የጋዜጣ ውይይቱ፣ የስብሰባውና የሠልፉ ሁሉ ማዕከላዊ ነጥብ ጥያቄዎችና ቅዋሜዎች ሁሉ ሰላማዊ መድረክ ያግኙ፣ ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ወደ መታረቅና አብሮ ወደ መሥራት ይምጣ የሚል መሆን ያሻዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ፣

  • ‹‹ፀረ ሰላም››/‹‹የጥፋት ኃይሎች››፣ ወዘተ. የሚሉ ዓይነት ጠምዶ የማስጠመድ ፖለቲካን መቃወምና ይህንን የሚያራምዱ ፖለቲከኞችን ማሳጣት፣
  • ወጣቶች የብሔረሰብ ሰፈርንና የፖለቲካ ዝንባሌን ተሻግረው አንድ ላይ ተዋናይ መሆናቸው፣
  •  በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ በተለይ የትግራይና የኦሮሞ ዴሞክራቶችና ልጆች ጉልህ ተሳትፎ ውጤትን የሚወስን እንቁ ነው፡፡ የትግራይ ልጆች ተሳትፎ ከሕወሓት መራሽ ገዥነት የተጎተተ ጥላቻን በመፈረካከስ፣ የኦሮሞ ልጆች ተሳትፎም ከኦነግ ጋር የተያያዘ ጥርጣሬንና ጥላቻን በማጠብ ረገድ መተኪያ የላቸውም፡፡ ይህንን የመሰለ ቅንብር ያለው እቅስቃሴ መፍጠር ከተቻለ ያለጥርጥር የጥፋት አደጋ መክኖ ብሩህ ተስፋና ዴሞክራሲ ያሸንፋሉ፡፡

የለየላቸው ወግ አጥባቂዎችና የግራ ፖለቲከኞች አንድ ላይ መንግሥትን ሲመሩ በምናይበት በዛሬው ጊዜ ውስጥ፣ የኛዎቹ ሥልጣን እስከ ማቃመስ ድረስ በረዘመ ሆደ ሰፊነት አብረው ቢሠሩ ኡኡ የሚያሰኝ ነገር የለውም፡፡ አዕምሮ ላለው ድርጊቱ ከቡድን ይልቅ አገርን መጥቀም ነው፡፡ የሆነ ይሁንና እኛ የምንጨነቅለት የፖለቲከኞቹ አብሮ የመሥራት ነገር ሥልጣን የማቋደስና የፓርቲ ፕሮግራሞችን የማገናኘት አይደለምና በየትኛውም ወገን ያሉ ሥልጣን ወዳዶችና የጠብ ፖለቲከኞች ለማደናገር እንዳያመቻቸው ቁልፍ ነጥቦችን ቁልጭ አድርገን እናስቀምጥ፡፡

  1. የመጀመሪያው ደረጃ አብሮ የመሥራት ተልዕኮ አስቀድሞ የታወቀ ዴሞክራሲ የሚፈልጋቸውን ሁኔታዎች የማመቻት ነው፡፡
  • ይህም ገና በጠላትነት የመወጋገዝ ፖለቲካን አቋርጠው ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ አብሮ ወደ መሥራት ሲያመሩና ሁለቱም ወገኖች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ አስፈላጊነታቸው በግልጽ ሲወጣ፣ ኅብረተሰቡ ውስጥ ተሸጋግሮ የነበረውም የጠላትና የወዳጅ ፍረጃ መበተን ይጀምራል፡፡ 
  • የዴሞክራሲ መብቶች ይበልጥ ተግባራዊ ተጨባጭነት ያገኛሉ፡፡
  • ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የወልቃይት ዓይነት ጥያቄዎች ሌላ ጠንቅ በማይተክሉበት (የሚመለከታቸውን ሕዝቦች ሳያሸካክሩ ተቀባይነት በሚያገኙበት መልክ) ለመፍታት ይስማማል፡፡
  •  የብዙኃን ማኅበራት ነፃና ንቁ ሕይወት ያገኛሉ፡፡
  • የእነዚህ ሁኔታዎች መፍካት፣ ከፖለቲካ ወገናዊነት ገለልተኛ መሆን በሚገባቸው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለ ወገንተኝነትን ትዝብት ውስጥ ይከታል፤ ለማረም ያበረታታል፡፡
  • የፍትሕ አካላት ያለአድልኦ ለመሥራት የሚመች ነፃ ደመና ያገኛሉ፡፡
  • በፖለቲካ ታማኝነት የመንግሥት ሠራተኛን የማንሳትና የመጣል ዘልማድ ይጋለጣል፡፡
  • የፀጥታ ኃይሎች ሊይዙት የሚገባቸውን ባህርይና በሚዲያም ሆነ በሌላ መድረክ ሊያራምዱ የሚችሉትን አቋም አንድ ሁለት ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
  • እነዚህን በመሳሰሉት አደፋፋሪ ሁኔታዎች በመታገዝ ባለው የተወካዮች ምክር ቤት በኩል፣ የማያፈናፍኑ ሕጎችን እንዲቃኑ ማድረግ ይከተላል፡፡
  • ለተከታዩ ምርጫም ከእስካሁኑ በእጅጉ በኢወገንተኝነት የተሻለ የምርጫ አስፈጻሚ መዋቅር ማደራጀት ይቻላል፡፡ 
  1. የዴሞክራሲን ድልዳል የማሟላቱ ሥራ ገና እንደመጀመሩ፣ ተከታዩ የ2012 የምርጫ ወቅት አብሮ መሥራትን የሚያቋርጥ አይሆንም፡፡ ምናልባትም የመደላድል ሥራውና ዴሞክራሲን የማፅናቱ ሥራ ቢያንስ የሁለት ምርጫ ዘመን ትግግዝን ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎቹ አሁን ያላቸው እውነተኛ የሕዝብ ተቀባይነት አንዱን ወገን ሙልጭ የሚያስቀር የምርጫ ውጤት የሚያሰገኝ አለመሆኑ ለዚህ ተግባር ይመቻል፡፡ እናም የሁለተኛው ዘመን አብሮ የመሥራት መርሐ ግብር ከላይ እስከ ታች ምክር ቤቶች ድረስ የጠለቀ የሁለት በኩል ተሳትፎ ይኖረዋልና፣ ገለልተኛ የዴሞክራሲ አውታራትን የማደራጀቱና ዴሞክራሲን የማጥበቁ ተግባር ይበልጥ መጥለቁና መስፋቱ ከሕዝብ ንቁ ተሳትፎ ጋር ይዘልቃል፡፡  

 እዚህ ሒደት ውስጥ ከገባን የዴሞክራሲ ጅምራችን በጥያቄና በጫጫታ ጋጋታ እንዲቀጭ ዕድል የማንሰጥ፣ የእኔ ፖለቲካ የቅዱስ የእሱ ግን የሰይጣን፣ ለእኔ ውዳሴ፣ ለእሱ ኩነኔ የሚል ፖለቲካን ኩም የምናደርግ እንደምንበረክት እርግጠኛ ሆኜ ለመናገር እደፍራለሁ፡፡ ምክንያቱም የኢሕአዴግን ጫንቃ እየደባበስን ወደ ዴሞክራሲ መግቢያ ሳናደርግ ያባከንነው የ1997 ዓ.ም. ዕድል ዛሬም ይቆጨናልና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...