Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉውይይቶች ዘላቂ የመፍትሔ በሮችን ይክፈቱ!

ውይይቶች ዘላቂ የመፍትሔ በሮችን ይክፈቱ!

ቀን:

በሒሩት ደበበ

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ፈታኝ ሁኔታ እንደገጠመው በተለያዩ ክስተቶች እየተገለጠ ነው፡፡ ከድርቅና ከመልካም አስተዳደር ዕጦት በላይ የተለያዩ የሕዝብ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች እየበረቱበት መጥተዋል፡፡ ባሳለፍናቸው ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ‹‹የተረጋጉ›› የሚመስሉ ገጽታዎች ቢታዩም፣ በአገሪቱ የማኅበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ያረበበው ሥጋት ቀላል አይመስልም፡፡ ጠንከር ያለ መፍትሔንም ይሻል፡፡

ይህንን እውነታ የሚያሳየው ባለፈው ሳምንት ልዑል ዘሩ የተባሉ ጸሐፊ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ‘አገርን ከምስቅልቅል እናድን’ በማለት ያቀረቡት ጽሑፍ ነው፡፡ ‹‹የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ብትሆንም በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፤›› ሲሉም የመንግሥትን ክፍተት፣ የሕዝቡን ጠንከር ያለና የተደራጀ ቅሬታ፣ የተቃዋሚውን ጎራ አሠላለፍና የተቀናጀ ዘመቻ፣ እንዲሁም የአካባቢያችንን ለአደጋ መጋለጥ በተጨባጭ ማሳያዎች ተንትነዋል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም የአቶ ልዑልን ሐሳብ የምጋራባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ በተለይ የሰሞኑን የሕዝብ ቅሬታና አገራዊ የፖለቲካ ተቃውሞ ተከትሎ ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በብዙዎቹ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተካሄዱ ውይይቶች፣ ከራሱ ከሲቪል ሰርቫንቱ እየተደመጠ ያለው የለውጥ መሻትና ቅሬታ ምናልባትም በኢሕአዴግ ሁለት አሥርትና ተኩል ዕድሜ ውስጥ የከረረና ከፍ ያለ መሆኑ በተለያዩ መድረኮች የታዘቡና የተሳተፉ ወገኖችም እያረጋገጡ መምጣታቸው ነው፡፡

ውይይት መጀመሩ መልካም ቢሆንም ሕዝብ ይደመጥበት!

ዘንድሮ የተነሳው የሕዝብ ቅሬታ በማንነት ጥያቄም፣ ይሁን በመልካም አስተዳደር ወይም በሙስናም ይበል በጋራ ማስተር ፕላን ጉዳይ ‹‹አስደንጋጭ›› ነው የተባለው ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ምርጫ ‹‹ባሸነፈበት›› ወቅት መሆኑ ነው፡፡ አምስተኛው አገራዊና ብሔራዊ ምርጫ በግንቦት 2007 ዓ.ም. ሲካሄድ አንድም የግልም ሆነ የተቃዋሚ ዕጩ ተወዳዳሪ የፌዴራልም ሆነ የክልል ምክር ቤት ውስጥ ሊገባ አልቻለም፡፡

ይህ ክስተት ኢሕአዴግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕዝቡ ‹‹ተስፋ ጥሎብኛል›› የሚል መታበይ ውስጥ ሲከተው፣ የተቃዋሚ ኃይሎች ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙን አወጁ፡፡ በተለይ በውጭ አገር የሚኖሩና አማራጩ ‹‹የትጥቅ ትግል ነው›› የሚሉቱ በኢትዮጵያ የሰላማዊና የዲሞክራሲያዊ ትግል በር ላይከፈት እንደተከረቸመ አድርገው አስተጋቡ፡፡ በእርግጥ በዚህ ውጤት ላይ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ ተሟጋቾችና ምዕራባውያንም ‹‹ለምን? እንዴት?›› የሚል ጥያቄ እንዳነሱበት ይታወቃል፡፡

በምርጫ 2007 የተቃዋሚው ኃይል መዳከም፣ የምርጫ መጭበርበርም ይባል የኢሕአዴግ ጥንካሬ በሰፊ ብዝኃነት ውስጥ ‹‹የልማታዊ መንግሥት›› እሳቤ ብቻ አየሩን መሙላቱ ላያስገርም ይችላል፡፡ ግን ‹‹ኢሕአዴግ ብቸኛ ምርጫዬ ነው›› ያለው ሕዝብ በወራት ዕድሜ ውስጥ ለምንና እንዴት ተገልብጦ ቁጣ ቀሰቀሰ ነው አስገራሚው ጥያቄ፡፡ የሕዝቡ ቅሬታስ ምን ቢፈጠር ነው ከቀደሙት ጊዜያት ከፍ ያለና ያለፈ ሆኖ የታየው የሚለው ጥያቄ መንግሥትን ሊያነቃው ይገባል፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ የተጠራቀመ ችግር ነው የሚሉ ትንተናዎች እየወጡ መሆናቸው ሳይዘነጋ፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በሃይማኖት ተቋማትና በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች (በተለይ ወጣቶችና ሴቶች) ላይ ያተኮሩ ውይይቶች በመንግሥት በኩል ተጀምረዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የተጀመረው ውይይት መበረታታት ያለበትና ለአገር የሚጠቅመው ብቸኛው መንገድ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን እየታየ ያለው አሁንም መድረኮቹ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና በአንድ ወገን አስተሳሰብ እየተቃኙ፣ ‹‹በድርጅታዊ አሠራር›› መመራታቸው ብዙዎችን እያሳዘነ ነው፡፡ መቼ ነው ኢሕአዴግ አስተማማኝ ማሻሻያ ሊያሳይ የሚችለው የሚለው አጀንዳና ጥያቄም እግሩን እየዘረጋ ነው፡፡

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ሲቪል ሰርቫንቱ በስፋት በሚያነሳው ሐሳብ፣ ‹‹የሕዝብን ቅሬታ፣ ቁጣና ተቃውሞ ባለቤት የሌለው ቅዋሜ እያሉ በመግፋት በውጭ ያሉ ኃይሎችና የሻዕቢያ ቅስቀሳ እንደሆነ የተጀመረው ግፊት አክሰሪ የፖለቲካ መንገድ ነው፤›› እያለ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ሕዝብ ምን ጎደለበት መባል አለመቻሉም ያሳዘናቸው ቀላል አይደሉም፡፡

ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ስነሳ በአሥር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የወቅታዊ ጉዳዮች ምክክሮች ላይ የተሳተፉ ሲቪል ሰርቫንቶችን አነጋግሬያለሁ፡፡ በብዙዎቹ ፎረሞች የተነሳው ሐሳብ ግን በሚገርም ሁኔታ ተመሳሳይነት ያለው ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የውጭ ሚዲያዎችና ብሎገሮች ከሚያነሱት ብዙም የራቀ የሚባል አይደለም፡፡

ቀዳሚው በአገሪቱ ‹‹የታመመ›› ከሚመስለው ፖለቲካዊ ሁኔታና የዴሞክራሲ ምኅዳር ጋር የሚገናኘው ነው፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ለመመለስ የታገለ ቢሆንም አሁን ግን የሐሳብ ብዝኃነት ተደፍቋል፣ የፕሬስ ነፃነት ተገድቧል፡፡ መደራጀት፣ መቃወምም ሆነ ነፃ ማኅበር መመሥረት አልተቻለም የሚለው ሙግት እንደ ተራራ ገዝፏል፡፡

እንዲያውም አንዳንዶች፣ ‹‹ሕዝቡ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱ መታፈኑም ሆነ ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ጥያቄውን ማሰማት አለመቻሉ ለሕገወጥ ሠልፍና ነውጥ እንዲነሳሳ ስላደረገው አይፈረድበትም፤›› እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ኢሕአዴግ የሚፈልጋቸው ሠልፎች፣ ፎረሞችና ሲምፖዚየሞች በመንግሥት ሀብትና ጥበቃ ታጅበው ሲከናወኑ፣ በየደረጃው የሕዝብ ነፃ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ግን አድማጭ አላገኙም የሚለው ሐሳብ ጎልቶ ተሰምቷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት እንኳን ትልልቅ የአገሪቱ ፖለቲከኞች የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ተዋናዮች ነበሩ፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት ግን ብዙዎቹ (በተለይ ትምክህተኛና ጠባብ የተባሉቱ) የስደት ፖለቲከኞች ሆነዋል፡፡ በአገር ውስጥ ያለው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪ፣ የማኅበራት ግንባር ቀደም ኃይልና ተዋናይ አንድም ለዘብተኛ አለፍ ሲልም የኢሕአዴግ ተለጣፊ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት አገሪቱ ለጥቂቶች የነበረችበትን ያለፈ የታሪክ ካባ መልሳ የምትደርብ መስላለች ነው ያሉት፡፡ ይኼ አስደንጋጭ ዝንባሌ ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የታመመ የሚመስለው በምርጫ ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ በምሁራንና ሊያመዛዝኑ ይችላሉ በሚባሉ ዜጐች አድርባይነትም እየተገለጸ ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ነፃና ሒሳዊ አስተያየትን መሰንዘር የማይችሉ ልጉሞች እየበረከቱ የመጡበት ጊዜ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ስህተት አለማረም ብቻ ሳይሆን ‹‹በዝምታ ውስጥ የምንቸገረኝ ባህል›› አዳብረው በነፃነት (Comfort Zone) መቀመጣቸው ነው›› በዚህም ምክንያት ጥቂት የሥርዓቱ ‹‹ወገኖች›› ሐሳብ ብቻ እንዲደመጥ የተገደድንበት አገር ተፈጥራለች ይላሉ የመንግሥት ሠራተኞቹ፡፡ ወጣ ያሉ ሐሳቦችን መድፈቅና መግፋት ጭምር በማሳየት፡፡

ሁለተኛው የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆነው የመልካም አስተዳደር፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎን የተመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ በውጭ ያለው ተቃዋሚ በተለይ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሕወሓት ያላግባብ እየተጠቀመና ጠቅላይ እየሆነ ነው የሚለውን ቅስቀሳ በመድረኮቹ ማስተባበል አልተቻለም፡፡

በተለያዩ መድረኮች ተደጋግሞ እንደተነሳው በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ በመከላከያና ደኅንነት መዋቅሮች፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር መዋቅሮችና በአንዳንድ ድርጅቶች ላይ ለምን ማመጣጠን አልተቻለም? የሚለው ጥያቄ በርትቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለይ በመከላከያ ኃይልና በደኅንነቱ ውስጥ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ‹‹ከነባሩ ታጋይ ልምድ እስኪቀስሙ›› ቢባልም ከ25 ዓመታት በኋላ እንዴት ለውጥ ማምጣት ከበደ? ብሔርና ማንነት ዋነኛ የልዩነት መገለጫ በሆኑበት አገር ውስጥስ ፍትሐዊ ተሳትፎ እንዴት ወደ ጐን ሊባል ይችላል የሚሉ በርክተዋል፡፡

ይህ መሆኑ ብቻውን ባልከፋ፡፡ በዚያው ልክ በሥልጣን መባለግ፣ በሙስና ሕገወጥ ጥቅም መተሳሰር ሲመጣም በቋንቋና በማንነት መሳሳብ እንደሚበረታ የሚሰጉ ተደምጠዋል፡፡ ከመሬት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከትራንስፖርት፣ ከኢንዱስትሪና ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አንፃር ‹‹ጥቂቶች እየበለፀጉ ነው›› ለሚለው አሉባልታ ሰፊ በር የከፈተ ጉዳይም ሆኗል፡፡ ስለዚህ ይህን ብዥታ የማጥራትና ፍትሐዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ወሳኝ ሥፍራ ይዞ መጥቷል፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥም እንደ ቀዳሚ ነጥብ እየተነሳ ነው፡፡

ሦስተኛው አነጋጋሪ ጉዳይ የፍትሐዊ ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራው ጥረት ‹‹ያልደረሳቸው›› በሚባሉ ወገኖች ነው፡፡ በእርግጥ እንኳንስ ገና ደሃ በሆነች አገር ውስጥ ይቅርና የትም ቢሆን ያለመርካትና የልማት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ መንገድ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ውኃ… ሲሟሉ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት የሚፈልግ ይመጣል፡፡ ይህም ሲሟላ ኢንተርኔት፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የቅንጦት ዕቃዎችና አገልግሎት… ፍላጐቶች ማብቂያ የላቸውም፡፡

አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ግን በተለይ ከሥራ አጥነትና ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዘው የድህነት ጥያቄ ከብዶ እየታየ መሆኑ በመድረኮቹ ተወስቷል፡፡ አዲስ አበባን የሞሏት የደቡብ፣ የአማራና የትግራይ ክልል አርሶ አደሮችና ወጣቶች እንዴትና በምን ምክንያት ፈለሱ? ‹‹ብዙ ሥራ›› ተሠርቷል በሚባልበት ጊዜ እንኳን በሺዎች የሚቆጠሩ የደቡብ፣ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ወጣት ስደተኞች ድንበር ተሻግረው ለችግር እየተጋለጡ ያሉት ለምንድነው? በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምሩቃን ሥራ አጥተው ምን መፍትሔ ተቀምጦላቸዋል? የሚሉ ጥያቄዎች እንደ መርግ የከበዱ ናቸው፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ የሥራ አጡ ቁጥር አገር እየፈታ መሆኑ ነው እየተነገረ ያለው፡፡ ለምን?!

መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በክልሎች የኑሮ ውድነትን ለመመከት የሚያደርጋቸው ጥረቶች አሉ፡፡ የደመወዝ ጭማሪ፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የአንዳንድ ሸቀጦች ድጎማ… ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም የዋጋ ግሽበት በተለይ የከተማ ነዋሪዎችን ክፉኛ መፈተኑ ተነስቷል፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ አለመመጣጠን፣ የጤፍ ዋጋ እጅግ በጣም የማይቀመስ መሆን፣ የማጣፈጫ ሸቀጦች ዋጋ መናር… ሕዝቡን ሰቆቃ ውስጥ እየከተቱ መሆናቸው ተወስቷል፡፡

በዚህ ላይ ፍትሐዊነት ሳይረጋገጥና ሕጋዊነት ሲጓደል ችግሩ እንዴት ሊባባስ እንደቻለም ተወስቷል፡፡ ከጐዳና ንግድ፣ ከሰው ሠራሽ ዋጋ ንረትና እጥረት እንዲሁም ከቅሸባና ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ሽያጭ አንፃር ዜጐች ከመማረር አልፈው ለከፋ የጤና ቀውስ እየተጋለጡ መሆኑ ተቆጣጣሪ አልባ ድርጊት አስመስሎታል፡፡

በዚህ ላይ ሙስናውንና የመልካም አስተዳደር ዕጦቱን በማባባስ ወደ መንግሥት ባለሥልጣናት ተጠግተው በአጭር ጊዜ የሚበለፅጉ ሰዎችን ሕዝብ ይመለከታል፡፡ አዋዋል አኗኗራቸውን ይታዘባል፡፡ ይህ ሁኔታም ኑሮ ውድነቱም ሆነ የዋጋ ግሽበቱ በእርሱ ላይ ብቻ ተፈርዶበት እንደመጣ መቅሰፍት እንዲቆጥር ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ነው የሙስና አደጋ ሕዝብንና አገርን የመበተን መዘዝ አለው እስከመባል የሚደርሰው፡፡

አራተኛው የሕዝቡን ቅሬታ ሌላው ያባባሰው በመንግሥት አካላትም ሆነ በየትኛውም የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ ተወሽቀው በዘረኝነትና በጠባብነት ሕዝቡን እየነጣጠሉ ያሉ አጥፊዎች ድርጊት ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥት መሠረት ማንኛውም ዜጋ በሕጋዊ መንገድ የትም ክልል ሄዶ ሠርቶና ከሌሎች ጋር ተስማምቶ የመኖር መብት ሰጥቶታል፡፡ በእርግጥ ይኼ መብት ከጥንት ጀምሮ ለዘመናት የኖረ ነው፡፡

አሁን አሁን ግን ይህንን መብት በግላጭ የሚጋፉ ብቻ ሳይሆን በጠባብነት መዶሻ ያደቀቁ ኃይሎች ሚዛን ከብዶ ታይቷል፡፡ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች በማንነታቸው ብቻ ሀብታቸው ተዘርፎ ባደ እጃቸውን የተባረሩ ዜጐችን አይተናል፡፡ እንዲያውም ግድያና ስቃይ የደረሰባቸውም ነበሩ፡፡ ይህን ድርጊት በእንጭጩ ያላረመው ብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝምና መንግሥት ዛሬ ‹‹አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል›› ሲባል ችግሩ ተባብሶ ታይቷል፡፡ እንዲያውም ወደ ሰፋፊዎቹ ክልሎችም ተዛምቷል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን በታየው ግጭትና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች በተነሳው ተቃውሞ በማንነታቸው ብቻ የተጠቁ ወገኖች አሉ፡፡ ይኼ ለምን ሆነ ብሎ መፈተሽ ካልተቻለ በዚህች በጋራ አገራችን በአንድነት ለመኖር የማንችልበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም ሲሉ ነው በርካታ ተወያዮች በጥልቅ ሥጋት ያነሱት፡፡

ክስተቱ የፌዴራል ሥርዓቱ ብዝኃነትን ለማስተናገድ የሚያግዝ ቢሆንም ብሔር ተኮር መሆኑ የፈጠረው ችግር ነው እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ዛሬ አማራን ከትግራይ ሕዝብ የሚያጋጨው የወልቃይት ጉዳይ፣ ነገ በሌሎች ክልሎችና ብሔሮችም ላለመታየቱ ዋስትና የለም፡፡ ይኼ ደግሞ በአገራዊው ድንበር እንኳን ቁርጥ ያለ ጠንካራ አቋም ይዞ መሟገት ለማይሻው የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳበት የውስጥ የመነጣጠል ችግር ነው ተብሏል፡፡

የክልሎች የድንበር፣ የይዞታም ሆነ የወሰን ጭቅጭቅ መበርታት፣ ሕዝቦች ‹‹በማንነት ጥያቄ›› ስም ወደ ዘር ሐረግ መማዘዝ፣ ወረዳና ዞን መሆን መሻት የሚያሳየው አገራዊ ኅብረት አለመፈጠሩን ነው፡፡ ይልቁንም አሁንም ዘራቸውን ወይም ብሔራቸውን መሠረት አድርገው እንዲሚጠቀሙ እንጂ፣ ከአገራዊው ትልቁ ኬክ የድርሻቸውን እያገኙ እንዳልሆኑ የተሰማቸው ዜጐች መበርከታቸውን ያመለክታል የሚሉ ሒሶችም ተነስተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት እየወቀሱ ያሉት መንግሥትን ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በአብዛኛው ማንነትና ብሔር ላይ ያተኮረ፣ ዴሞክራሲያዊም ቢሆን አንድነትን ያላመጣ ነው ይሉታል፡፡ ለአንድ አገርና ሰንደቅ በጋራ ከመሠለፍ ይልቅ ሕዝቦችን በሸረሪት ድር ወደ መተሳሰር የሚያወርድ የላላ ግንኙነት ይከተል እንደሆነም የተለያዩ ተናጋሪዎች አብነቶችን በመጥቀስ ሲያስረዱ፣ በተሻለ አስተሳሰብ ከውድቀት ማዳንና አገርንም መታደግ የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት ነው የተወሳው፡፡

አምስተኛው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አገሪቱን በመራባቸው 25 ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ውጣ ውረዶች አልፏል፡፡ የተሻለ ውጤት ያስመዘገበችው መስኮች እንዳሉም ሊካድ አይችልም፡፡ በዚያው ልክ ከፍተኛ ቅሬታ ያላቸውን ዜጎች አበራክቷል፡፡ ያልተሳኩለት አገራዊ አጀንዳዎችም እየታዩ ነው፡፡

እነዚህን ድብልቅልቅ ሁኔታዎች ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ተነጋግሮ ካልፈታቸው አገሪቱን እንዳለፈው ጊዜ ብቻውን ለማስተዳደር መሻት አያወጣም የሚሉ ሐሳብ ሰጪዎችም ተደምጠዋል፡፡ በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተካሄዱ ባሉ ውይይቶች ‹‹የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጐት ያላቸውን ኃይሎች አሸባሪ፣ ጽንፈኛ፣ አክራሪ፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ… በሚል ማግለልና መግፋት ብቻ ለመሮጥ ከመሻት ጉደለታቸውንም እየሞሉ መሳብ የመንግሥት ድርሻ ሊሆን ይገባል፤›› ያሉም ነበሩ፡፡

ይህን ሐሳብ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ደፍረው አይበሉት እንጂ፣ ‹‹መነጋገርና መወያየት የዘላቂው መፍትሔ ብቸኛ አማራጭ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ እንግዲህ መንግሥትና ፖለቲከኞች ከዚህ አስተሳሰብ ውጪ ሊቆሙ አይችሉም፡፡ ሕዝቡም ቢሆን (በተለይ የብዙኃኑ) ሁሉም ነገር በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈጸም ነው የሚሻው፡፡ ለዚህም የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትና ሰፋ ያለ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ ይኖርበታልም፡፡

ለማጠቃለል

አገር አቀፍ ውይይት በሁሉም ደረጃ መጀመሩ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ ሌሎችን የማያዳምጥበት ሊሆን አይገባም፡፡ በየመስኩ በተለይ ሕዝቡ ሊደመጥ ይገባዋል፡፡ የተነገረውን ነገር ወስዶና አንጠባጥቦ መጣል ሳይሆን ደግሞ ፈጣን የማሻሻያ ዕርምጃን አቅም በፈቀደ መጠን መውሰድ ተገቢ ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት ግን መንግሥት ገባ ወጣ የሚለውን የሕዝብ ቅሬታ እንደ መዘናጊያ ቆጥሮ (በተለይ ነገሮች ተረጋግተዋል ብሎ) ተመልሶ ወደ ጭቃው ውስጥ ከገባ የሚያፈጥነው ውድቀቱን ብቻ ነው፡፡ የአገር መዳከምና መበታተንም ሊደርስ እንደሚችል መተንበይ ሟርተኝነት አይደለም፡፡ ስለሆነም ትኩረቱ ለሕዝብ ድምፅ፣ ሐሳብና አገራዊ ውይይት ይሁን እላለሁ፡፡               

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...