Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የሪዮ ኦሊምፒክ ከተጀመረ እስከ መጠናቀቂያው ዋዜማ ድረስ ያላሳየን የለም፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ላለፉት 60 ዓመታት በነበራት ተሳትፎ ሁሌም የምንጠብቃቸው ድሎች በአትሌቲክስ የስፖርት ዘርፍ በሩጫው ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ የኦሊምፒክ ውድድሮች ሲደረጉ በቴሌቪዥን ሥርጭት የምናያቸው በርካታ ውድድሮች ያስቆጫሉ፡፡ የድህነትና የኋላቀርነት ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ጥበት መገለጫ የሆኑት ደፋር አለመሆንና ራስን መጠራጠር ቢያንስ የተወሰኑትን እንኳ ለመሞከር እንቅፋት ሆነውብናል፡፡ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ ተወዳዳሪዎች ባልተናነሰ ሌሎች የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች ተመልካች መሆን በጣም ያናድዳል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ መገለል በተጨማሪ ሌሎች የሚያናድዱ ጉዳዮችም አሉን፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የራሳችን የነበሩ በሩጫ የመካከለኛና የረዥም ርቀቶችን በቅጡ መወዳደር አቅቶን ድሎቻችንን አሳልፈን ስንሰጥ ታይተናል፡፡ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ፋጡማ ሮባ፣ መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ሚሊዮን ወልዴና የመሳሰሉትን ጀግኖች ያፈራች አገር ያስለመዱንን ድሎች የሚያስቀጥሉ ጀግኖችን እያጣን ነው፡፡ ዕድሜ ለአዲሷ ጀግና ለአልማዝ አያና (ይህንን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር) ይሁንና የዘንድሮው አያያዛችን አላማረኝም፡፡ ጎረቤት ኬንያ እስካለፈው ሳምንት አጋማሽ ድረስ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችና ሦስት የብር ሜዳሊያዎች አግኝታ ከዓለም 13ኛ ደረጃ ላይ እያለች፣ ውዲቷ አገራችን ግን አንድ ወርቅ፣ አንድ ብርና ሦስት ነሐሶች በማግኘት 41ኛ ደረጃ ላይ ነበረች፡፡ ኬንያዊያን የወርቅ ሜዳሊያዎችን ባገኙባቸው ውድድሮች የነበራቸው አስደናቂ ብቃት፣ በእኛ ጀግና አልማዝ አያና የአሥር ሺሕ ሜትር የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረ ወሰኖች ባይካካስ ኖሮ አያያዛችን በጣም አስፈሪ ነበር፡፡

በዘንድሮው ኦሊምፒክ ከብዙዎቹ አትሌቶቻችን የታዘብኩት የብቃት ማነስ ነው፡፡ በማጣሪያዎችም ሆነ በፍፃሜ ውድድሮች ከአልማዝ አያና ጋር ለመነፃፀር የሚያስችል ብቃት የነበራቸው አትሌቶች የትኞቹ ናቸው? ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡት ያደረጉት ትግልና ያስገኙት ውጤት ቢያስመሰግናቸውም፣ በአልማዝ አያና ደረጃ ስናየው ግን የሚያስመካ አይደለም፡፡ ሞ ፋራህ በአሥር ሺሕ ሜትር እንደተለመደው ተዝናንቶ ያሸነፈው አብረውት የተወዳደሩት (ያጀቡት) የተለየ ብቃት ማሳየት ስላልቻሉ ነው፡፡ ሃያ አምስት ዙሮችን አጅበውት ከሚሮጡ ይልቅ ከመሀል ተስፈንጥሮ ወጥቶ ሞ ፋራህን የሚቆርጥ በመጥፋቱ ድሉን በቀላሉ ወሰደው፡፡ እንደፈራነው ሞ ፋራህ ትንሽ እንኳ የሚያስጨንቅ ፉክክር አልገጠመውም፡፡ ምሩፅ፣ ኃይሌና ቀነኒሳ ለዓመታት ያስከበሩት ድል በቀላሉ ከእጃችን ወጣ፡፡

በስፖርታዊ መስኮችም ሆነ በሌሎች ሥራዎቻችን ተወዳዳሪ መሆንና አመርቂ ውጤት ማግኘት የምንችለው የላቀ ብቃት ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ የወርቅ ሜዳሊያ በክብር የሚጠለቀውም ሆነ እኔ ነኝ ያለ ስኬት የሚገኘው ብቃት ሲኖር ብቻ እንጂ፣ ከዚህ በመለስ እየተባለ በኮታ ወይም በልዩ ዝምድና ወይም በሙስና በሚገኝ ችሮታ አይደለም፡፡ በእርግጥ አገራችንን ወክለው በሪዮ ኦሊምፒክ የተወዳደሩ አትሌቶች በሙሉ አሸናፊ ይሁኑ ማለት ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ውድድር በመሆኑም ማሸነፍና መሸነፍ ያለ ነው፡፡ ስናሸንፍ እንደ ጀግናዋ አልማዝ አያና በብቃት አሳምኖና ሪከርድ ሰባብሮ ሜዳሊያ ማግኘትም ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን እዚህ ግባ የማይባል አቅምና ብቃት ሳይኖር አጉል መውተርተር ግን ያሳዝናል፡፡ ያውም ድል በለመድንባቸው ርቀቶች፡፡ ስንሸነፍም አሳዛኝ ሆነን ሳይሆን ታግለን ቢሆን ደግሞ ለነገ ተስፋ ያሳየናል፡፡ እያየነው ያለው ግን ይህንን አይገልጽም፡፡ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡

በሪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች የማራቶን ውድድር ሲደረግ ያስደነቀኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ አገር ለሚመሩ ሰዎች ትምህርት የሚሰጥ፡፡ በተለይ ደግሞ ለከተማ ከንቲባዎች፡፡ አንድ ወንድማችን በፌስቡክ ገጹ ላይ የጻፈው እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹የማራቶን ውድድርን ከመነሻው እስከ መድረሻው የአገራችን የከተማ ከንቲባዎች ቢያዩት መልካም ነው፡፡ የሰው አገር ባዶ ቦታ ሲገኝ ሕንፃ ብቻ አይታየውም፡፡ ፓርኮች፣ የልጆች መጫወቻ፣ ሙዚየሞች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ እምነቶች፣ የወጣቶች የስፖርት መጫወቻ ቦታዎች፣ እነዚሁ ሁሉ ይታያሉ፡፡ ልማት ከተደረደረ ብሎኬትና ከተነጠፈ አስፋልት በላይ ነው፡፡ የልማት ግቡ ሰው ነው፤›› የሚለው አባባል ብዙ ቁምነገር አለው፡፡ አንድ ከተማ ሊያሟላቸው ከሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ዋናው ለሰው ልጅ ምቹ መሆኑ ነው፡፡ አረንጓዴ መስኮች የሌሉት ከተማ ሰው ሰው አይሸትም፡፡ ዜጎች ከቁሳዊው እርካታ በተጨማሪ መንፈሳዊ እርካታም ያሻቸዋል፡፡ ከተማ ፕላን፣ ውበትና ምቾት ከሌለው ምኑን ከተማ ሆነው? በቂ ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ ንፁህና ለኑሮ ተስማሚ የሆኑ በቂ መኖሪያ ቤቶች፣ ስታዲየሞች፣ የሠፈር የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ መጻሕፍት ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ መፀዳጃ ቤቶችና የመሳሰሉትን በአግባቡ ገንብቶ ለሕዝብ የማቅረብ ትጋትና ብቃት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ የሕንፃ ጫካ ለማን ይረባል?

በሌላ በኩል እንደ አገር ቁጭ ብለን ሳይሆን እንቅልፍ አጥተን ማሰብ ያለብን፣ ኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫ ቢቀር የአፍሪካ ዋንጫ በአጭር ጊዜ እንዴት ማዘጋጀት እንዳለብን ነው፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት በዓመት 11 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳየን ነው የሚባለው ዲስኩራችን፣ ከወሬ በዘለለ አቅማችንን ማሳየት ካልቻለ ችግር አለ፡፡ የምንወደው እግር ኳስ ወንዝ አላሻግር ሲለን ቁጭ ብለን እያየን እንቆዝማለን፡፡ አትሌቲክሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያሽቆለቁል ሰበብ እየደረደርን ተኝተናል፡፡ በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮቻችን መስማማት አቅቶን ‹ይለይልን› እየተባባልን ዛቻ ውስጥ ከገባን ውለን አደርን፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ ግስጋሴ ድህነትን ታሪክ አድርጎ ወደፊት ሲራመድ እኛ ወደኋላ እየተጓዝን በነገር እንባላለን፡፡ ከብቃት ይልቅ ለወሬ ቅርብ በመሆናችን በብዙ ነገሮች ከተሳታፊነት ይልቅ ተመልካችነታችን ጎልቶ ይታያል፡፡ ወገኖቼ እባካችሁ ከቻልን በተሰማራንባቸው ቦታዎች እንደ ጀግናዋ አትሌት አልማዝ አያና ሪከርድ ለመስበር የሚያስችል ብቃት ይኑረን፡፡ ካልቻልን ለሚችሉት ቦታውን እንልቀቅ፡፡ ይኼ ሁላችንንም የሚመለከት መሆኑን ከላይ እስከ ታች እንገንዘብ፡፡ ተግባባን?

(ሐና ማርዬ፣ ከላፍቶ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...