Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቶታል ኢትዮጵያና ኤም ብር አዲስ የቴክኖሎጂ አሠራር ይፋ አደረጉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሞባይል ስልኮችን በመጠቀም በቀላሉ በየትኛውም ግብይት ለመፈጸም ቴክኖሎጂ አማራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ ነሐሴ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ቶታል ኢትዮጵያ በተመረጡ ነዳጅ ማደያዎቹ የኤም ብር አገልግሎት መስጠት መጀመሩንና ደንበኞችም በቀላሉ በሞባይል ስልካቸው አማካይነት በአቅራቢያቸው የሚገኝን የቶታል ኢትዮጵያ ነዳጅ ማደያ በአቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ (ጂፕኤስ) ታግዘው እንዲያገኙ የሚያግዝ፣  ማንኛውንም ክፍያ በኤም ብር እንዲፈጽሙ የሚረዳ ቴክኖሎጂ ይፋ አድርገዋል፡፡

የቶታል ኢትዮጵያ አፕልኬሽንን በስልካቸው በመጫን በአቅራቢያ ያሉትን የቶታል ማደያዎች ለማግኘት፣ ማደያ ውስጥ የሚገኙትን የቶታል ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለማየት እንዲሁም የፈለጉትን ማደያ ስልክ ቁጥር ከአፕሌኬሽኑ በማግኘት መጠቀም እንደሚያስችላቸው ተብራርቷል፡፡

በመላ አገሪቷ የሚገኙ የቶታል ኢትዮጵያ ደንበኞች ክፍያቸውን ለመፈጸም ኤም የብር ተጠቃሚ በመሆን፣ በሞባይል ስልካቸው ለተገለገሉበትና ለተስተናገዱበት ሁሉ ክፍያ መፈጸም ይችላሉ፡፡ በዚህም መሠረት ነዳጅ ከሚቀዳላቸው ሠራተኛ ጋር በመነጋገር ክፍያውን ወዲያውኑ በስልካቸው በኩል ያለ ጥሬ ገንዘብ መፈጸም ይችላሉ፡፡ የኤም ብር አገልግሎቶችን ለማግኘት የቶታል ኢትዮጵያ ማደያዎችን ጨምሮ በቀላሉ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ኤምብር አገልግሎት ሰጪ ተቋም ጋር በመሄድ በመመዝገብ፣ ማንኛውም የኤምብር አገልግሎት ምልክት የለጠፈ ንግድ ቤቶች በማምራት የሒሳብ ቁጥር በመክፈት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ተጠቅሷል፡፡

ኤም ብር በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት በሚሰጡ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የተጀመረ የሞባይል አገልግሎት ሲሆን፣ ማንኛውም ግለሰብ በሞባይል ስልክ አማካይነት በሚከፍተው የሞባይል ሒሳብ ቁጥር አማካይነት አገልግሎት ያገኛል፡፡ ለኤም ብር የተመዘገቡ ደንብኞች በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በአማራ ብድርና ቁጠባ፣ በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ፣ በደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲሁም በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በኩል የሞባይል ሒሳብ ወይም ዋሌት አካውንት ይከፈትላቸዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ ሽፈራው በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የኤምብር ሥራ ሂደት ኃላፊ እንዳብራሩት፣ በአገሪቱ ካሉ አምስት የብድርና ቁጠባ ተቋማት በተጨማሪ መደበኛ ባንኮችና ሌሎች ማይክሮ ይፋናንሶች ወደ አገልግሎቱ እየገቡ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከ3,000 በላይ የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎችና ወኪሎች በኩል የኤም ብር አገልግሎቱ እንደሚሰጥ አቶ ሀብታሙ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ኤም ብር አገልግሎት ከጀመረ ጀምሮ በአዲስ አበባ 600 በላይ ወኪሎች በዘርፉ የሰተማሩ ሲሆን፣ በተግባር ሥራው ላይ የሚገኙ ከ180 በላይ እንደሆኑ አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ ከሆነ፣ ኤም ብር ለወኪሎቹ ከሚሰጣቸው ጥቅማ ጥቅሞች በተጨማሪ የብድርና ቁጠባ ጉርሻ በማዘጋጀት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመጨመር አቅዷል፡፡ የኤም ብር ተጠቃሚ ለጓደኛ ወይም ለዘመድ ገንዘብ ማስቀመጥና ማውጣት፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ለዕቃ ወይም አገልግሎት ገዢዎች ክፍያ መፈጸም፣ ወደ ቁጠባ ሒሳብ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ብድር መክፈል፣ በሱቆች ወይም በምግብ ቤት መጠቀምና መግዛት የሞባይል ካርድ መግዛት እንዲሁም የኦንላይን ግብይቶችን ማከናወንና የመሳሰሉትን ማከናወን እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ኤም ብር የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ክፍያ፣ የስልክ ክፍያ፣ የትምህርት ቤትና የውኃ ክፍያዎችንና የመሳሰሉትን ወርኃዊ ወጪዎች አገልግሎቱን የማስተናገድ አቅም እንዳለው የሞስ ኮንሰልታንሲ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኩባንያ ኃላፊ አቶ መስፍን ተፈራ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

 ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ የገባው የኤም ብር አገልግሎት፣ እስካሁን ያሉትን የቀጥታ ተጠቃሚዎች ቀጥር ጨምሮ ከ250 ሺሕ በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡

ገንዘቡን ለግብይት ከመጠቀም ባሻገር፣ ለማኅበራዊ ጉዳይ ክፍያዎች፣ ለሴፍቲኔት ፕሮግራምና ለሌሎች የዕርዳታ ሥራዎችን ለማገዝ ከዓለም ባንክና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በዚህ መስክም 140,000 አባራዎች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የሚገኙ እነዚህን አባወራዎች ጨምሮ ኤም ብር በሥራ በቆየበት አንድ ዓመት ውስጥ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ማገበያየት እንደተቻለ ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር አስርድተዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ግብይትም በተለይ አዲስ አበባ ላይ የሞባይል ካርድ ብዙ ተጠቃሚ ሲኖረው፣ አማራ ክልል ገንዘብ ለማስተላለፍ፣ ትግራይ ደግሞ ለማኅበራዊ ጉዳዮችና ለእርዳታ ክፍያ በሰፊው እየተጠቀሙበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሞባይል ቴክኖሎጂ ግብይት የሚከናወንበትና ኤምፔሳ የተባለው የኬንያው ቴክኖሎጂ 17 ሚሊዮን ተገልጋዮች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ቶታል ኢትዮጵያና ኤም ብር በጋራ ለመሥራት በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም. ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች