Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየአተት ወረርሽኝ ቀድሞ ባልታየባቸው አካባቢዎች መከሰት ጀምሯል

  የአተት ወረርሽኝ ቀድሞ ባልታየባቸው አካባቢዎች መከሰት ጀምሯል

  ቀን:

  –  የውኃ ማከሚያ እንክበሎች እጥረት የዋጋ ንረት አስከትሏል

  ከየካቲት ወር ጀምሮ በመላ አገሪቱ እየተዛመተ የሚገኘው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ ባልተያባቸው አካባቢዎች መታየት መጀመሩ ታወቀ፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች እንደ አዲስ ተከስቷል፡፡ 

  ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የአተት በሽታ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ቀደም ብሎ የታየባቸውና በርካቶችን ለሕመም የዳረገባቸው ነበሩ፡፡ ይሁንና በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች መታየት መጀመሩን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖ  አስታውቀዋል፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ፣ በአማራ ክልል በባህር ዳር ዙሪያ አተት እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ የአማራ ክልል ባስታወቀው መሠረት ከ450 በላይ ሰዎች በአተት የታመሙ ሲሆን፣ የአንድ ሰው ሕይወትም በበሽታው ምክንያት አልፏል፡፡ ወደ ባህር ዳር ከተማ እንዳይዛመት ለማድረግ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

  በአተት ምክንያት የሟቾች ቁጥር መንግሥት ከስድስት እስከ አሥር እንደሚገመት ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ይሁንና የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ግን ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ 19 ሰዎች በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በደቡብ ክልሎች ብቻ በአተት መሞታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ በተመድ ተቋም ሳምንታዊ ሪፖርት መሠረት፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእነዚሁ ክልሎች ብቻ 2,000 ያህል መሆኑን ታውቋል፡፡

  የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በበኩሉ ሰኔ 25 እንዲሁም ሐምሌ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ የሞቱ ሰዎች ስድስት ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ ይሁንና በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ግን ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 29 የሕክምና መስጫ ማዕከላት ተከፍተው ሕሙማኑ እየታከሙ፣ የዳኑም ወደየቤታቸው እየሄዱ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ ይጠቅሳል፡፡

  ከሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአተት ወረርሽኝ ይበልጡን እየተዛመተ በመምጣት በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ተንሰራፍቶ ቆይቷል፡፡ ይሁንና በቦሌ፣ በአቃቂ፣ በየካ፣ በኮልፌ እንዲሁም በነፋስ ስልክ ላፍቶ አተት የሚገኝባቸው ወረዳዎች መኖራቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ የአተት በሽታ በተበከሉና ንፅህናቸው ባልተጠበቀ ምግብና ውኃ አማካይነት የሚከሰት በመሆኑ፣ በተለይ የውኃ ማከሚያ እንክብሎች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ እጥረት ማጋጠሙን መነሻ በማድረግ ከእጥፍ በላይ ዋጋ ጭማሪ መታየቱ ተነግሯል፡፡

  በአገሪቱ የውኃ ማከሚያ እንክብሎችን ከሚያቀርቡት አንዱ የሆነው ሲትረስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኩባንያ ችግሩ መከሰቱን አስታውቋል፡፡ የአየርላንድ ኩባንያ የሆነው መድንቴክ ሊሚትድ የሚያመርተውን አኳታብስ የውኃ ማከሚያ እንክብል በብቸኝነት በማስመጣት አገር ውስጥ የሚያከፋፍለው ሲትረስ ኢንተርናሽናል ነው፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ምናሴ ክፍሌ እንዳስታወቁት፣ ድንገተኛ በሆነው የአተት ወረርሽኝ ምክንያት የተከሰተው እጥረት የአንድ እሽግ አኳታብስ ይሸጥበት ከነበረው ከ6.25 ብር አሻቅቦ ከእጥፍ በላይ ዋጋ ሲጠየቅበት ከርሟል፡፡

  የውኃ ማከሚያ እንክብል ክምችት በሚፈለገው መጠን ባለመኖሩ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትና ከውጭ ለማስመጣት ኩባንያው አንድ ወር እንደፈጀበት የጠቀሱት አቶ ምናሴ፣ መንግሥት እንክብሎቹ በአስቸኳይ እንዲመጡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ቅድሚያ እንዲሰጥ በማድረጉ ከ60 ሚሊዮን በላይ እንክብሎችን ወይም ሁለት ሚሊዮን እሽጎችን አስመጥቷል ብለዋል፡፡ በዓመት እስከ 800 ሺሕ ዩሮ የሚያወጡ እንክብሎችን እንደሚያስመጣም አቶ ምናሴ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል፡፡

  ከሲትረስ ኢንተርናሽናል ባሻገር ፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢንተርናሽናል የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅትም ውኃ አጋር የተባለውን የውኃ ማከሚያ እንክልብል በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡ 

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img