የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀድሞውን ብራሌ እርሻ ልማት ድርጅት ለሳግላ ትሬዲንግ ኩባንያ በኪራይ ለመስጠት ተስማማ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቀድሞ የብራሌ እርሻ ልማት ድርጅት ባለቤቶች (ጌታቸውና ሚካኤል) የሰጠው ብድር ባለመመለሱ ይህንን ግዙፍ እርሻ መረከቡ ይታወሳል፡፡ 5,490 ሔክታር ስፋት ያለውን ይህን ሰፊ እርሻ የአሚባራ ቢዝነስ ግሩፕ ለአሥር ዓመታት በኪራይ ሲያስተዳድረው ቆይቶ፣ ጊዜው በ2007 ዓ.ም. በመጠናቀቁ ንግድ ባንክ መልሶ ተረክቧል፡፡ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን እርሻ ለመሸጥ በተደጋጋሚ ጨረታ ቢያወጣም ሁነኛ ገዢ ማግኘት ባለመቻሉ፣ እርሻውን በኪራይ ለመስጠት ሐምሌ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ጨረታ አውጥቷል፡፡
ንግድ ባንክ ይህንን እርሻ በ137 ሚሊዮን ብር መነሻ ዋጋ ለመሸጥ ያወጣው ጨረታ የኩባንያዎችን ትኩረት መሳብ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ምክንያቱም ባንኩ ድርጅቱን ለጨረታ ሲያቀርብ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውን የጥጥ መዳመጫ በመነጠሉ መሆኑን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በኋላም በተደጋጋሚ በአሥር ሚሊዮን ብር ወርኃዊ ክፍያ ለማከራየት ጨረታ ቢያወጣም ሁነኛ ገዥ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
በመጨረሻ ሐምሌ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. ድርጅቱን የሚፈልጉ ኩባንያዎች የሚጫረቱበትን ዋጋ፣ የአሠራር ሁኔታና የድርጅታቸውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ እንዲያቀርቡ ባንኩ ጋብዟል፡፡
በዚህ ጨረታ አሚባራና ሳግላን ጨምሮ ስድስት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኩባንያዎች የተወዳደሩ ሲሆን፣ ሳግላ ትሬዲንግ ያቀረበው የፋይናንስና የቴክኒክ መወዳደሪያ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
‹‹ድርጅትዎ (ሳግላ ትሬዲንግ) በተጓዳኝ ከሚሠራቸው ሥራዎች በተጨማሪ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማራ በመሆኑና የተሻለ ዋጋ በማቅረቡ የጨረታው አሸናፊ ሆኗል፤›› በማለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የኩባንያውን አሸናፊነት አስታውቋል፡፡
ሳግላ ትሬዲንግ ለዚህ እርሻ ቫትን ሳይጨምር በዓመት ሰባት ሚሊዮን ብር፣ ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ስምንት ሚሊዮን ብር የኪራይ ዋጋ አቅርቧል፡፡ ይህንን እርሻ ከሦስት ዓመት በኋላ በመደርደሪያ ዋጋ ሙሉ በሙሉ የመጠቅለል ሐሳብም እንዳለው፣ የሳግላ ትሬዲንግ ዋጋ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሞዝ ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የብራሌ እርሻ ልማት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ 665 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር በና ፀማይ ወረዳ ይገኛል፡፡ ይህ የእርሻ ልማት ድርጅት በአጠቃላይ 5,490 ሔክታር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 4,000 ሔክታር የለማ ነው፡፡ ድርጅቱ ከእርሻ መሬት በተጨማሪ ቢሮዎች፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ የነዳጅና የውኃ ቦቴዎች፣ ገልባጭ ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ንብረቶችን ያካትታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአውሮፕላን ማረፊያም አለው፡፡
የእርሻ ልማቱ የሚካሄደው በመስኖ ሲሆን በዋነኛነት ጥጥ ያመርታል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ አሸናፊ የሆነው ኩባንያ ሳግላ ትሬዲንግ ውል እንዲፈርምና ድርጅቱን እንዲረከብ ጥሪ አስተላልፏል፡፡