Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሃቨላንጅ በ100 ዓመታቸው አረፉ

የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሃቨላንጅ በ100 ዓመታቸው አረፉ

ቀን:

የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሃቨላንጅ በ100 ዓመት ዕድሜያቸው ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪዮ ዲጄኔሮ ሳማሪታኖ ሆስፒታል አረፉ፡፡

ብራዚላዊው ሃቨላንጅ የዓለምን እግር ኳስ የሚመራው አካል ፊፋን እ.ኤ.አ. 1974 እስከ 1998 ድረስ አገልግለውታል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ በአመራር ላይ በነበሩበት ጊዜ በፊፋ ውስጥ በነበረ የአሠራር ክፍተትና ብልሽት ዙሪያ በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. የተደረገው ምርመራ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከፊፋ የክብር ፕሬዚዳንትነት ራሳቸውን ማግለላቸው በዓመቱም በሳምባ ምች ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ሃቨላንጅ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባልነት እ.ኤ.አ. 1963 በጤና እክል ሳቢያ ራሳቸውን እስካገለሉበት 2011 ድረስ አባል ነበሩ፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን 1908 ዓ.ም. የተወለዱትና ድንቅ ዋናተኛ የነበሩት ሃቨላንጅ፣ ከ80 ዓመት በፊት በ1936 በተደረገው የበርሊን ኦሊምፒክ በ400 ሜትርና በ1,500 ሜትር ነፃ ዋና ተወዳድረው ነበር፡፡ ከ64 ዓመት በፊት በ1952 በተደረገው የሔልሲንኪ ኦሊምፒክ የውኃ ላይ ኳስ ጨዋታ (ወተር ፖሎ) ቡድን ውስጥም ነበሩበት፡፡

አውሮፓውያን በፊፋ ውስጥ የነበራቸው ገደብ የሌለው የበላይነት ያልተደሰቱት አፍሪካና እስያ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት እንግሊዛዊውን የፊፋ ፕሬዚዳንት ሰር ስታንለይ ሮውስን በድምፅ ቀጥተው ሃቨላንጅ መንበሩን እንዲቆናጠጡ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ለ24 ዓመታት ፊፋን ሲመሩ መሠረታዊ ለውጥ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው ሃቨላንጅ አንዱ ተግባራቸው የዓለም ዋንጫ ተካፋይ አገሮች ቁጥር ወደ 32 ማድረሳቸውና የአፍሪካ፣ የእስያና ኦሺያና ኮታ ከፍ ማድረጋቸው ነው፡፡ ካሜሩን በ1982 ዓ.ም. በዓለም ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ በመግባት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት መሆን የቻለችበትም ጊዜ ነበር፡፡

ፊፋ በድረ ገጹ እንዳወሳው፣ ሃቨላንጅ ሰኔ 4 ቀን 1966 ዓ.ም. የፊፋን ፕሬዚዳንትነት ከተቆናጠጡ በኋላ በስድስት ዙር የአመራርነት ጉዟቸው 50 አዲስ ፌዴሬሽኖች (ማኅበሮች) የዓለምን እግር ኳስ በሚመራው አካል ውስጥ አባል ሆነዋል፡፡ ፊፋ የዓለም ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን ማዘጋጀት የጀመረበት 1983 ዓ.ም. በርሳቸው ፕሬዚዳንትነት ዘመን ነበር፡፡ እንዲሁም የዓለም ወጣቶች ዋንጫ (ከ20 ዓመት በታች)፣ የዓለም ታዳጊዎች ዋንጫ (ከ17 ዓመት በታች)፣ እንዲሁም የመጀመሪያው የፉትሳል ውድድር እንደቅደም ተከተላቸው በ1969 ዓ.ም.፣ በ1977 ዓ.ም. እና በ1981 ዓ.ም. አስጀምረዋል፡፡  

ጆአዎ ሃቨላንጅ ከኢትዮጵያ ጋር በተለይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ከነበሩት ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ቁርኝት ነበራቸው፡፡ ከ44 ዓመት በፊት ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ የአፍሪካውያንን ድምፅ ለማግኘት የሚያስችላቸው ድምፅ የሚያገኙት በይድነቃቸው ተሰማ ፊታውራሪነት መሆኑን በመተማመን ከቅስቀሳ ቡድናቸው ጋር በመጀመሪያ ጎራ ያሉት አዲስ አበባ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በመገኘት መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

ብራዚል ከሁለት ዓመት በፊት ያስተናገደችውን የዓለም ዋንጫ በ98 ዓመታቸው ከቤታቸው ሆነው የተከታተሉት ሃቨላንጅ እየተካሄደ ያለውን የሪዮ ኦሊምፒክ በሕይወት እያሉ አይተውታል፡፡ አልማዝ አያና አስደናቂውን የ10,000 ሜትር ድሏን ያጣጣመችበት የኦሊምፒክ ስታዲየም በሃቨላንጅ ስም የሚጠራ ነው፡፡

ከሦስት አሠርታት በፊት ጋዜጠኞች ‹‹ከርስዎ በኋላ የፊፋ ፕሬዚዳንት ማን ይሆናል?›› ብለው ለጠየቋቸው የሰጡት ምላሽ ባጭር ቋንቋ ‹‹ሚስተር ተሰማ ነዋ!›› ብለው በወቅቱ የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ (1914 – 1979) ለቦታው እንደሚመጥኑ ተናግረው ነበር፡፡ ይኽንኑ ተከትሎ በወቅቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ይድነቃቸው፣ ለሃቨላንጅ ጥቆማ አክብሮታቸውን ገልጸው፣ በጤና ምክንያት እንደማያስቡት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ዓመት ሳይቆዩ አቶ ይድነቃቸው ነሐሴ 13 ቀን 1979 ዓ.ም. ማረፋቸው አይረሳም፡፡ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ሆነና ሁለቱም ያረፉት በተመሳሳይ ወር ሆነ፡፡ ሃቨላንጅ ያረፉት ነሐሴ 10 ቀን (ኦገስት 16) ሲሆን፣ ይድነቃቸው ያረፉት ነሐሴ 13 ቀን (ኦገስት 19) ነበር፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...