Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከንቲባ ድሪባ ባለፈው ዓመት እንዲጠናቀቅ ያዘዙት ሰነድ አልባ መስተንግዶ ዘንድሮም አልተጠናቀቀም

ከንቲባ ድሪባ ባለፈው ዓመት እንዲጠናቀቅ ያዘዙት ሰነድ አልባ መስተንግዶ ዘንድሮም አልተጠናቀቀም

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ለሰነድ አልባ ባለይዞታዎች ሕጋዊ መብት እንዲፈጥር የተቋቋመው የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በ2009 ዓ.ም. ሥራውን አጠናቆ እንዲፈርስ ትዕዛዝ ቢሰጡም፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመትም ሥራውን ማጠናቀቅ አልቻለም፡፡

ዓርብ ታኅሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ   ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከነዋሪዎች ጋር ባካሄደው ውይይት፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው እንዲወስዱ ጥሪ የተደረገላቸው ከሰባት ሺሕ በላይ ባለይዞታዎች እስካሁን እንዳልቀረቡ ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ለሙ ገመቹ በውይይቱ ወቅት ካርታ ያልወሰዱ ከሰባት ሺሕ በላይ ባለይዞታዎች በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ካርታቸውን የማይወስዱ ከሆነ፣ በመመርያው መሠረት ይዞታቸውን እንደማይፈልጉ ተቆጥሮ ለመንግሥት ገቢ እንደሚደረግ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በዋናነት በሚተገብራቸው መደበኛ ይዞታ አገልግሎቶችና ሰነድ አልባ አገልግሎቶች ላይ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ለ50,681 የመደበኛ ይዞታ አገልግሎቶች ምላሽ ለመስጠት ታቅዶ ለ57,431 ባለይዞታዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በሰነድ አልባ መብት ፈጠራ ደግሞ ለ1,770 ባለይዞታዎች ካርታ ለመስጠት ታቅዶ ለ1,208 ባለይዞተዎች ካርታ ተዘጋጅቷል፤›› ሲሉ አቶ ለሙ ገልጸው፣ ‹‹ሥራው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ለ75,035 ባለይዞታዎች ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሰጠ ነው፤›› በማለት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን የሥራ ደረጃ አመልክተዋል፡፡

ከአዋጅ ቁጥር 47/67 ወዲህ የተገነቡ ነገር ግን ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸውን ባለይዞታዎች ለማስተናገድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ካቋቋመ ከሰባት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ በ2009 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለከተማው ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን በአስቸኳይ አጠናቆ ሠራተኞች ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲመደቡ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡

‹‹ከሰነድ አልባ ይዞታዎች ውስጥ እስከ 1988 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን በተቻለ መጠን አብዛኛውን ሥራ ዘንድሮ ማጠናቀቅ ይኖርብናል፡፡ ዘንድሮ አጠናቀን ወደ ሌላ ሥራ መሄድ አለብን፡፡ ስለዚህ የቢሮና የክፍላተ ከተሞች አመራሮች እዚህ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉ ከንቲባ ድሪባ በወቅቱ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸው ነበር፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን ማጠናቀቅ እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡ በውይይቱ ወቅት ለሥራው አለመጠናቀቅ ከቀረቡ ምክንያቶች ውስጥ በተገልጋዮች በኩል የተሟላ ሰነድ አለማቅረብ፣ ከአገር ውጭ መሆን፣ የፍርድ ቤት ክርክር፣ የሚጠየቀው ክፍያ ከፍተኛ መሆንና በመንግሥት በኩልም ሥራን በአግባቡ አለመሥራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በበኩሉ በአዲስ አበባ ያለውን የሰነድ አልባ ባለይዞታዎች ችግር ለመፍታት፣ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው በክፍያ መክበድ ምክንያት ሰነድ ላልወሰዱ የሰነድ አልባ ባለይዞታዎች አማራጭ የክፍያ ሥልት በማስቀመጥ ካርታውን መስጠት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...