- መንግሥት በሲጋራ ላይ 70 በመቶ ታክስ ለመጣል በዝግጅት ላይ ነበር
ብሔራዊ ትምባሆ ድርጅትን በከፍተኛ ዋጋ ከገዛው የጃፓን ኩባንያ ጋር ምክክር ሳይደረግ በሲጋራ ምርቶች ላይ ታክስ እንዳይጣል፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ ማስተላለፉን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር በሆኑት አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ሰሞኑን ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ትዕዛዙ እንደ ደረሳቸው ለሪፖርተር የደረሱ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል (JTI) የተባለው ኩባንያ ባለፈው ዓመት መንግሥት በብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት ውስጥ ከያዘው ድርሻ 40 በመቶ በ510 ሚሊዮን ዶላር የገዛ ሲሆን፣ በቅርቡ በተደረገ ስምምነት ደግሞ ቀሪውን የመንግሥት 30 በመቶ ድርሻ በ434 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ይህ የጃፓን ኩባንያ ከየመን እህት ኩባንያው ሼባ ግሩፕ ጋር በመሆን ብሔራዊ ትምባሆ ሞኖፖል ድርጅትን ሙሉ በሙሉ ሲጠቀልል፣ መሰንበቻውን የመንግሥትን 30 በመቶ ድርሻ በገዛበት ወቅትም መንግሥት ለብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት በሕግ የሰጠውን በብቸኝነት ትምባሆ (ሲጋራ) የማምረትና የማከፋፈል ንግድ (ሞኖፖሊ ራይት)፣ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የጃፓኑ ኩባንያ እንዲጠቀምበት አስተላልፏል፡፡
የጃፓኑ ኩባንያ ትምባሆ ድርጅትን ሙሉ ለሙሉ ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ መንግሥት ሕገወጥ የሲጋራ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር በጀመረው እንቅስቃሴ፣ በሲጋራ ምርት ላይ ከፍተኛ ታክስ ለመጣል በመወሰን ሕግ የማርቀቅ ተግባር በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የተረዳው የጃፓኑ ኩባንያ፣ ግዥውን ከመፈጸሙ በፊት ሥጋቶቹን ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረቡን የተገኙ መረጃዎች ያመለከታሉ፡፡
በኮንትሮባንድ የሚገባ ሲጋራ ሕገወጥ ንግድ ከጠቅላላ የኢትዮጵያ ሲጋራ ገበያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 44 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ በተለይ በምሥራቁ የኢትዮጵያ አካባቢ 90 በመቶ የሚሆነው የሲጋራ ገበያ በኮንትሮባንድ የሲጋራ ንግድ ቁጥጥር ውስጥ መውደቁን፣ እ.ኤ.አ. በ2012 እና በ2017 የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ምሥራቁን የአገሪቱ አካባቢ የተቆጣጠረው የሲጋራ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ በአካባቢው የሥርዓተ አልበኝነት ምንጭ እንደሆነ፣ የሚገኘውም ገቢ የኮንትሮባንድ ተዋናዮችን ጉልበተኛ እያደረጋቸው በመሆኑ መንግሥት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ዘመቻ ለመጀመር እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን፣ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከዚህ ንቅናቄ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሲጋራ ችርቻሮ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የአጫሾች ቁጥር ዕለት ከዕለት እንዲያሻቅብ ምክንያት እንደሆነ በማመን በችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ እስከ 70 በመቶ ታክስ እንዲጣል ለመንግሥት ያቀረበው ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ሲጋራ በሚሸጡና በሚያከፋፍሉ ንግድ ቤቶቸ ላይ ሲጋራን በሚታይ ቦታ እንዳያስቀምጡ፣ ሲጋራን የማስተዋወቅ ማናቸውንም ተግባራት እንዳይፈጽሙ ሕግ የማርቀቅ ተግባር በማከናወን ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተጠቀሱትና ሌሎች በዝግጅት ላይ ያሉ የቁጥጥር ሥርዓቶች የአጫሾችን ቁጥር ማሻቀብ መግታትና ሕገወጥ የሲጋራ ንግድን መቆጣጠር ዋነኛ ዓላማቸው ነው፡፡
ይሁን እንጂ የጃፓኑ ኩባንያ ሊተገበር የታቀደው የቁጥጥር ሥልትና ከፍተኛ ታክስ መጣል የተባለውን ውጤት ያመጣል ብሎ እንደማያምን፣ ይልቁንም በሕግ አግባብ የሚከናወን የሲጋራ ንግድን እንደሚጎዳ ሥጋቱን ለመንግሥት አስታውቋል፡፡ በሥራ ላይ በሚገኘው የአገሪቱ ሕግ የሲጋራ ኮንትሮባንድንና ሕገወጥ ንግድ የሲጋራ ገበያውን 44 በመቶ እንደተቆጣጠረ በማስታወስ፣ በታቀዱት አዲስ የቁጥጥር ዕርምጃዎች ሕጋዊ የሲጋራ ንግድን የሚያቀጭጩ ካልሆነ በስተቀር ሕገወጥ ንግዱን ለመቆጣጠር ያስችላል የሚል እምነት ብሔራዊ ትምባሆ ድርጀት እንደሌለው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግራንት ምዋት ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከአንድ ወር በፊት አቤቱታ አቅርበው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህም ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የታቀዱት ዕርምጃዎች ከጃፓኑ ኩባንያ (ከትምባሆ ድርጅት) ጋር ግልጽ ምክክርና መግባባት ሳይደረስበት እንዳይፈጸሙ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡
ማሳሰቢያው ከተላከላቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ይገኙበታል፡፡