Monday, July 22, 2024

ከመግለጫው በላይ ተግባር ይጠበቃል!

መሰንበቻውን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ለ17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በመምከር፣ የሐሳብ አንድነትና መተማመን በመፍጠር ውሳኔዎች ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአገሪቱ የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከእነ ዝርዝር መገለጫቸው በመለየት፣ በመንስዔና በመፍትሔዎቻቸው ላይ በመነጋገር ችግሮችን ለመቅረፍ ቃል ገብቷል፡፡ ጥፋቱን ከማመን ጀምሮ አገሪቱንና መላ ሕዝቧን ሥጋት ውስጥ የከተቱ ችግሮች መከሰታቸውንና ለዚህም አመራሩ ኃላፊነት ይወስዳል ብሏል፡፡ በመሠረቱ ጥፋትን ማመንና ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ለመፍታት የጋራ አቋም በመያዝ ለመፍትሔ መነሳት ጥሩ ነው፡፡ ከልብ ከሆነም ድጋፍ ይቸረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የተስፋ ቃል ተግባራዊ መሆኑ ላይ ከሕዝብ ጋር መተማመን ያስፈልጋል፡፡ አገሪቱንና መላውን ሕዝብ ካጋጣሙ ችግሮች በፍጥነት በማውጣት ሰላምና መረጋጋት መፍጠር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አመቺ ሁኔታዎችን መዘርጋትና ለዕድገትና ለብልፅግና ለሚረዳ አገራዊ መግባባት ዝግጁ መሆን የግድ ይላል፡፡ ከቃል በላይ ተግባር ሊቀድም ይገባል፡፡

ኢሕአዴግ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠሙ ችግሮች ሳቢያ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ውስጥ በመግባት የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተስፋ ቃላትን ቢደረድርም አልተሳካለትም፡፡ ይልቁንም በአባል ድርጅቶች መካከል ተፈጠረ በተባለው አለመግባባትና አለመተማመን ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በወጡ መግለጫዎችም ይኼው ጉዳይ ብዙ ተብሎበታል፡፡ አሁን ደግሞ የሐሳብ አንድነትና መግባባት ተፈጥሮ ግምገማው መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡ ሌላው የፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ ብዙ አይባልበትም፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ የፌዴራል መንግሥቱንና አራቱን ትልልቅ ክልሎች እንደ ማስተዳደሩና ሌሎቹን ክልሎች ከሚመሩ ገዥ ፓርቲዎች ጋር አጋር በመሆን በአገሪቱ የማይደርስበት ሥፍራ ስለሌለ፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ አካላት ጋር የሚያደርገው ሽኩቻም ሆነ ትንቅንቅ በቀጥታ ሕዝቡንና አገሪቱን ይመለከታል፡፡ በእያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይም ተፅዕኖው የጎላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ ከኢሕአዴግ ብዙ ነገሮችን ይጠብቃል፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ለአንድ አገር ወሳኝ በመሆናቸው ገዥው ፓርቲ በብዙ ነገሮች ይጠበቃል፡፡ ከቃል በላይ ተግባር እንዲቀድም ይፈለጋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከምንም ነገር በላይ በአመራሩ ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎችና ሥጋቶች ለመቅረፍ በሚያስችል ስምምነትና መግባባት ግምገማው መጠናቀቁን ሲያስታውቅ፣ ይህ መተማመንና መግባባት ከተነገረው በላይ በተግባር እንዲታይ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነት አገርን ከሥጋት ለመታደግና ሕዝብን ከጭንቀት ውስጥ ለማውጣት ይረዳል፡፡ አንድ ድርጅት አገር እያስተዳደረ በውስጡ አለመግባባት መፈጠሩ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን አለመግባባቱ ከመጠን በላይ እየጦዘና ግንኙነቶችን እያበላሸ ጎራዎችን ሲፈጥር የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የፈሰሰው የንፁኃን ደም ይህንን ሥጋት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ በአንድ በኩል ለዓመታት የተቆለሉ የመብት፣ የነፃነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ፣ በሌላ በኩል በውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ዕጦት ሳቢያ በሚፈጠሩ ግጭቶች ዜጎች ሕይወታቸው በከንቱ ይጠፋል፣ አካላቸው ይጎድላል፣ የደሃ አገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ የአገር ህልውና ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ በዚህም ሳቢያ ዜጎች ከሰብዓዊና ከዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በበለጠ በሰላም ወጥቶ የመግባታቸው ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ የአገራቸው ዕጣ ፈንታ እንቅልፍ ይነሳቸዋል፡፡ በሥልጣንና በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የበላይነት ይዞ ለመውጣት የሚደረገው ሽኩቻ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ባለመሆኑ ንፁኃን ሰለባ ሆነዋል፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ባለመከበሩም በሙስና እስከ አንገታቸው የተነከሩ ጭምር ሕዝብ አጋጭተዋል፡፡ መሬት በወረራ የቸበቸቡ ሳይቀሩ የነውጥና የግጭት መሪ ሆነዋል፡፡ ከአገር በላይ የግልና የቡድን ጥቅም በልጦ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህንን ደግሞ ሕዝብ በዓይኑ ዓይቷል፡፡ ይህንን በመገንዘብ ቃልና ተግባርን ማቆራኘት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ የሚፈልገው በሕግና በሥርዓት የምትመራ አገር እንድትኖረው ነው፡፡ መላውን ሕዝብ ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ የልማትና የዴሞክራሲ አጀንዳ እንዲቀረፅ ነው፡፡ አገርን የሚመራ መንግሥት ደግሞ ሕዝብ የሥልጣኑ የመጨረሻ ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ፣ የሕዝቡ ኑሮ በእኩልና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ማድረግ፣ ወጣቱ ትውልድ ጥራትና ተደራሽነት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ በቁርጠኝነት መሥራት፣ የሕዝብ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻልና በተቻለ መጠን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ በአግባቡ እንዲያገኝ ማገዝ፣ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ወገኖች የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት፣ የወጣቶች ሥራ ፈጠራ በየመስኩ ባለሙያዎች እየተመራ ውጤታማ እንዲሆን ዕድሉን መስጠት፣ ኢፍትሐዊነትን የሚያንሠራፉ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ወዘተ. ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና በነፃነት እንዲኖሩ ድጋፍ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ልማትና ዴሞክራሲ የተነጣጠሉበት አገር ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ልማትና ዴሞክራሲ ተጣጥመው የሚሄዱበት ፍትሐዊ ሥርዓት መኖር የሚችለው በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በዚህች ታሪካዊች አገር ውስጥ ለሕግ የበላይነት ትልቅ ክብር ይሰጥ፡፡ በተግባር ይረጋገጥ፡፡  

ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ለሕዝብ ቃል ገብቷል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያደረገውን ጥረት ያህል ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ባለማድረጉ ከፍተኛ የሆነ ቅራኔ ተፈጥሯል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲው በተለይ በአመራር ደረጃ በመበላሸቱ ችግር መፈጠሩን ራሱ አምኗል፡፡ ዴሞክራሲው እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ በመመሥረት ከመታገል ይልቅ፣ መርህ አልባ ግንኙነት ማስፈን የተለመደ ሥልት ወደ መሆን መሸጋገሩን መገምገሙን አስታውቋል፡፡ በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ መርህ አልባ ግንኙነት ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹን ማዳከሙን አስታውቋል፡፡ አገር የሚመራ ድርጅት በዚህ ደረጃ መታመሙን ሲገልጽ ያስደነግጣል፡፡ እንደተባለው በእነዚህ ችግሮች ላይ ስምምነት ተደርሶ መግባባት ከተቻለ ለአገር በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር የወረረው ትልቁ በሽታ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ዴሞክራሲያዊ ቢሆን ኖሮ ችግሩ በፊት ተፈቶ በሕግ ብቻ በመመራት የትና የት መድረስ ይቻል ነበር፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በእኩልነትና በነፃነት የሚወዳደሩበት ዓውድ ተፈጥሮ የሕዝብ ነፃ ፍላጎት ተፈጻሚ ይሆን ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጥቶ መቀበል መርህ ግንኙነታቸውን እያዳበሩ ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት መሆኑ በተግባር ይረጋገጥ ነበር፡፡ መልካም አጋጣሚዎች በከንቱ ባክነው የቀሩት በተበላሹ ግንኙነቶች ምክንያት ነው፡፡ አሁን በተግባር የሚያስፈልገው ስህተትን በፍጥነት አርሞ ለሕዝብ ፍላጎት መገዛት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅና ታሪካዊት አገር ናት፡፡ ሕዝቧም በታሪክ የተመሰከረለት አገሩን የሚወድ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ እጅ ለእጅ በማያያዝ በአንድነት ለአገሩ ዕድገትና ብልፅግና ማሠለፍ ከተቻለ፣ ይህችን ታሪካዊት አገር ገነት ማድረግ ይቻላል፡፡ ዋናውና ትልቁ ቁም ነገር ግን ሁሉንም ወገን የሚያግባባ አንድነት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና የሚያመጣ ሥራ ለማከናወን ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው በላይ የሚያፈቅሩት ነገር የላቸውም፡፡ የአገራቸው ህልውና ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ እርስ በርስም ተሳስበውና ተፋቅረው በአንድነት ዘመናትን የዘለቁት ለአገራቸው ባላቸው ጥልቅና የጋለ ፍቅር ነው፡፡ ይህንን ትልቅ ፀጋ አስከብሮ ወደፊት መገስገስ የሚቻለው ቡድናዊ ጥቅሞችንና መሳሳቦችን አደብ በማስገዛት ለአገር አንድነት ቁርጠኛ ሆኖ በመነሳት ነው፡፡ ብሔርተኝነትን ብቻ እያቀነቀኑ አንድነት ማምጣት አይቻልም፡፡ አገር በብሔርተኞች አስተሳሰብ ተተብትባ መራመድ አትችልም፡፡ ከሥልጣንና ከጥቅም በላይ አገር ትቀድማለች፡፡ ሕዝብ ይቀድማል፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ሕዝብ መጉዳት፣ አገርን መበደል ለማንም አይበጅም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አገር መሆኗን ማመን ይገባል፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሆነበት ሥርዓት እንዲኖርም መፈቀድ የለበትም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በዚህ ዘመን መቀንቀን የለበትም፡፡ በዚህ መሠረት በሀቅ መሥራት ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ከመግለጫው በላይ ተግባር ይጠበቃል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...