Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተገናኘ የምስክሮች አቀራረብ መዘግየት ተቃውሞ አስነሳ

ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተገናኘ የምስክሮች አቀራረብ መዘግየት ተቃውሞ አስነሳ

ቀን:

በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቂሊንጦ እስረኞች ማቆያ ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በመቃጠሉ የ23 እስረኞች ሕይወት ካለፈ በኋላ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉ 38 ተጠርጣሪዎች ተከሰው፣ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች እያቀረበ ነው፡፡ በምስክሮቹ አቀራረብ መዘግየት ምክንያት  ተከሳሾቹ ሰኞ ታኅሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቃውሟቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛው ወንጀል ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ፣ ዓቃቤ ሕግ ቆጥሯቸው የነበሩት ምስክሮች ማረሚያ ቤት የነበሩ ናቸው፡፡ ምስክርነት ሳይሰጡ ከእስር በመፈታታቸው ሊያገኛቸው እንዳልቻለ ለፍርድ ቤት አስረድቶ በአድራሻቸው አፈላልጎ ለማቅረብ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመግለጹ፣ አምስት ወራት እንደተሰጠው አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ምስክሮቹ ስንት እንደሆኑና እያንዳንዳቸው ምንና በማን ላይ እንደሚመሰክሩለት በዝርዝር ለፍርድ ቤቱና ለተከሳሾች ማስረዳት ሲገባው፣ ሁለትና አራት ምስክሮችን በማቅረብ ጊዜ እየወሰደ መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ምንም ባልሠሩበት ሁኔታ ለማይክሮ ሰከንድ እንኳን መታሰር እንደማይፈልጉ የተናገሩት እስረኞቹ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ማረጋገጡንና ለቂሊንጦ ቃጠሎና ሕይወታቸው ላለፈ እስረኞች ማረሚያ ቤቱ ኃላፊነት እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወስኖ እያለ እነሱ መታሰራቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጥፍራቸው መነቀሉንና ጀርባቸው በምስማር መመታቱን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ጠቁመው፣ ኮሚሽኑ በፓርላማ የተናገረው ወይም ያቀረበው ሪፖርት እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተከሳሾቹ ከላይ የተጻፈውን የገለጹት ፍርድ ቤቱ ‹‹አንሰማችሁም፣ ስሜት አናዳምጥም፣ ተረጋጉና ከጠበቆቻችሁ ጋር ተመካክራችሁ በጠበቃችሁ አማካይነት ተናገሩ፣ ወይም በጽሑፍ አቅርቡና ትዕዛዝ እንሰጥበታን፤›› እያለ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ግን መናገራቸውን አላቆሙም፡፡ ፍርድ ቤቱ ማዳመጥ የሚችለው በሥርዓትና በሕጉ መሠረት መሆኑን ደጋግሞ በመግለጹ፣ ከተከሳሾቹ አንዱ ሁሉንም ወክሎ ተመሳሳይ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ እንደገለጹት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/99 (ስለፌዴራል ታራሚዎች አያያዝ የወጣ ደንብ ነው) እንደሚደነግገው፣ ተከሳሽ በችሎት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ በአንድ ተከሳሽ ተወክለው አቤቱታቸውን እንዲያሰሙ ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

በዕለቱ ታኅሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን ቀጥሮ የነበረው፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ ጠይቆት አራት ምስክሮችን ማቅረቡን ገልጿል፡፡ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ ከተከሰሱት 38 ተከሳሾች ውስጥ በተወሰኑት ላይ ምስክርነት እንዲሰጡ የቀረቡት ምስክሮች፣ ስለክሱ ያዩትንና የሰሙትን እንዲመሰክሩ ጭብጥ ሲያሲዝ ፍርድ ቤቱ ለዓቃቤ ሕጉ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በክሱ ላይ ይመሰከራል የሚባል ጭብጥ እንደሌለ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክር በማንና ምን እንደሚመሰክር በዝርዝር እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

‹‹ፍርድ ቤቱ ካዘዘ እኛ ባናምንበትም ምስክሩ የሚመሰክረው. . .›› ሲሉ ዓቃቤ ሕጉ፣ ፍርድ ቤቱ አስቁሞ ‹‹ሥነ ሥርዓት፣ ትርጉም የሚሰጡ ነገሮች እንዳይናገሩ ፍርድ ቤቱ በአጽንኦት ያዛል፤›› በማለት ፍሬ ነገር ማስመዝገብ ግዴታ እንዳለባቸው በማሳሰቡ ዓቃቤ ሕግ ጭብጥ አስመዝግበዋል፡፡ የመጀመርያ ምስክር በቂሊንጦ እሳት ቃጠሎ ላይ ተከሳሾች የተሳተፉ መሆኑን እንደሚያስረዱላቸው ተናግረዋል፡፡

ምስክሩ ማንነቱን አስመዝግቦ እንደጨረሰ የሚያውቃቸውን ተከሳሾች በስም ከጠራ በኋላ በአካል እንዲለያቸው ሲደረግ ጥቂቶቹን አሳይቶ፣ ቀሪዎቹን መለየት ባለመቻሉ ወደ ምስክርነቱ ገብቷል፡፡ ምስክሩ እስረኛ እንደነበርና በቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ቤት የአንድ ማደሪያ ቤት አስተዳዳሪ እንደነበር አሳውቆ፣ ቃጠሎው እሱ ከሚያስተዳድረው መኝታ ቤት መጀመሩን ገልጿል፡፡ ከቃጠሎው ሁለት ቀናት በፊት የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳር የአተት በሽታ መከሰቱን ገልጾ፣ ከቤተሰብ የሚመጣ ምግብ ለእስረኞች እንደማይገባና በማረሚያ ቤቱ ምግብ እንዲመገቡ የሚገልጽ ማስታወቂያ መለጠፉን አስታውሷል፡፡

የተለፈጠውን ማስታወቂያ ተከሳሾቹ ካነበቡ በኋላ አድማ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ምስክሩ ገልጿል፡፡ በሻሸመኔ፣ በአምቦና ሌላ ቦታ የተገደሉ ወገኖችን በሚመለከት ፀሎት እናድርግ በማለት በቡድን መደራጀትና ማረሚያ ቤቱን ሰብረን ወጥተን ኦነግን እንቀላቀላለን፣ ምግብ እንበላም፣ ድምፃችን ይሰማ ማለታቸውን ገልጿል፡፡ ዩኒፎርማቸውን ከማደሪያ ቤታቸው አውጥተው ይወረውሩ እንደነበርም አስረድቷል፡፡

በመቀጠልም ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ሦስት ሰዓት አካባቢ ቃጠሎው መነሳቱን፣ እሳቱም የተነሳው መፀዳጃ ቤት ውስጥ የነበረ ፍራሽ በላይተር ተለኩሶ መሆኑንና በግቢው ውስጥ ሐሺሽ ይጨስ እንደነበር መስክሯል፡፡ ነፃነት አበበ የሚባል እስረኛን ለፖሊስ ወሬ ያመላልሳል በሚል ቀደም ብሎ ይዝቱበት እንደነበርና በዕለቱ ግን ደብድበው እንደ ገደሉት መስማቱን አስረድቷል፡፡ ተከሳሹ ከቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተገናኘ አየሁት ያለውን በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት መስቀለኛ ጥያቄ ከመሰከረባቸው ተከሳሾች ጋር የት እንደሚተዋወቅ ጠይቀውት፣ እሱም ታሳሪ ስለነበር ቂሊንጦ እንደሚተዋወቁ ገልጿል፡፡ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. መታሰሩንም አክሏል፡፡ በአምቦ፣ በሻሸመኔና በነቀምት ለሞቱ እንፀልይ ያሉት መቼ እንደሆነ ሲጠይቁት እንደማያስታውስ ተናግሯል፡፡ በቂሊንጦ እስር ቤት መሰብሰብ እንደሚቻልና እንደማይቻል ተጠይቆ፣ ባይቻልም እንደሚሰበሰቡ ገልጿል፡፡ ተከሶሾችን መለየት ያልቻልው ስለሌሉ ነው ወይም መለየት ስለልቻለ መሆኑን ጠይቀውት፣ ስለሌሉ መሆኑን ገልጿል፡፡ እስረኞቹ ግን አሉ ተብሏል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀውት የተወሰኑትን ሲመልስ የተወሰኑትን እንደማያስታውስ በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄው ማረሚያ ቤቱን ማን አቃጠለው ሲለው ስም በመጥቀስ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አይተኸዋል ሲባል ግን አላየሁም ብሏል፡፡ እንዴት እንዳወቀ ሲጠይቀው ታሳሪ ነግሮት መሆኑን ገልጿል፡፡ እሳቱ የተለኮሰበት ላይተር እንዴት እንደገባ ተጠይቆ፣ ‹‹አይቻለሁ እንጂ እንዴት እንደገባ አላውቅም፤›› ብሏል፡፡

ሐሺሽ እንደሚያውቅ ሲጠየቅ ከሲጋራ እንደሚለይ ገልጿል፡፡ እንዴት እንዳወቀ ሲጠየቅ ሲያጨሱ ማወቁን ተናግሯል፡፡ እሳቱን የለኮሰው እስረኛ ያቃጠለው እሱ መሆኑን የነገረው ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት መሆኑን ሲናገር፣ እንዴት ችሎት ውስጥ እንደጠፋበት ሲጠየቅ እንደማያውቀው ተናግሯል፡፡

ሌላው የዓቃቤ ሕግ ምስክርም ማንነቱን ለፍርድ ቤቱ ከገለጸ በኋላ በአንድ ተከሳሽ ላይ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ እሱም በተመሳሳይ ሁኔታ ከተከሳሽ ጋር ቂሊንጦ ታስሮ እንደሚተዋወቁ ገልጿል፡፡ ተከሳሽ ስለግንቦት ሰባት መግለጫ ይሰጥ እንደነበር፣ ግንቦት ሰባት ጎንደርን መቆጣጠሩን፣ ሻሸመኔ ላይ የግንቦት ሰባት ባንዲራ እየተውለበለበ መሆኑን ለእስረኛ መግለጫ ይሰጥ እንደነበር አስረድቷል፡፡ ወያኔ ሦስት ወራት እንደቀሩት፣ እህል ጭነው የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን፣ በተለይ በቡድን ሦስትና ከዚያም በላይ ሲሆኑ እንደሚናገር ገልጿል፡፡ ከእስር ቤቱ ውጪ ሰላም እንደሌለ ይናገር እንደነበር፣ በቴሌቪዥን የመንግሥት ኃላፊዎችን ሲያይ የማጥላላትና ቻናሉ እንዲቀየር ያደርግ እንደነበር አስረድቷል፡፡ በአጠቃላይ ምስክርነቱን ከመጀመርያው ምስክር ቃል በተመሳሰለ ሁኔታ ሰጥቷል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች ከተከሳሽ ጋር እስከ መቼ እንደሚተዋወቅ ጠይቀውት እስከ ቃጠሎው ቀን እንደሚተዋወቁ ገልጿል፡፡ ጓደኛው ስለነበር የሚናገረውንና የሚያስተላልፈውን መልዕክት ሁሉ ይሰማ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ቃጠሎውን በስንት ሰዓት እንደነበር ሲጠየቅ 2፡30 ሰዓት ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ በማረሚያ ቤቱ ክልክል ስለመሆኑና አለመሆኑ ተጠይቆ ክልክል መሆኑን ገልጿል፡፡ ከግንቦት ሰባት ጋር የተገናኘ ወሬ ሲወራ ሪፖርት ስለማድረጉ ተጠይቆ አለማድረጉን ተናግሯል፡፡ ከቃጠሎ በፊት ተኩስ እንደነበርና በቃጠሎ ወቅት ወደ ውጭ መውጣት እንደማይቻል አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም በማጣሪያ ጥያቄው ከመኝታ አልጋቸው ላይ በተገነጠለ ብረት ተመትቶ መሞቱን ስለገለጸው ታሳሪ ጠይቆት፣ ከመኝታ ክፍል ወደ ውጭ ወጥቶ በጥይት መመታቱን አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ማሰማት እንደሚቀጥል ተናግሮ በዕለቱ ያቀረባቸውን ምስክሮች አልፈልጋቸውም በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ ቀሪ አድርጓቸዋል፡፡ ምስክርነቱ ታኅሳስ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጥሎ ውሏል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...