በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱና ያልተፈቱ ግጭቶች መነሻ ምክንያት እንዲመረምር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሞ የተሰማራው ግብረ ኃይል፣ ተልዕኮውን አከናውኖ ያጠናቀረውን ሪፖርት ሊያቀርብ ነው።
በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ደም አፋሳሽና ከ900 ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን ያፈናቀለው ግጭት መነሻ፣ እንዲሁም ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ሁኔታ ግብረ ኃይሉ ሲመረምር እንደቆየ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠረውን አለመረጋጋትና የመማር ማስተማር ሒደት መስተጓጎልንም፣ ግብረ ኃይሉ ተዘዋውሮ መገምገሙ ታውቋል፡፡
ፓርላማው ያዋቀረው ግብረ ኃይል ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመገኘት ያከናወነውን ምርመራ አጠናቅሮ በቅርቡ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንደሚያቀርብና ውይይት እንደሚካሄድበት፣ የምክር ቤቱ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል። ምክር ቤቱ ይህንን የምርመራ ሪፖርት በሚያዳምጥበት ወቅትም፣ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ተጠርተው ሪፖርቱን ያጠናቀረው ግብረ ኃይልና የምክር ቤት አባላት ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ውጥረቶችን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምላሽ እስኪሰጧቸው ድረስ መደበኛ ስብሰባዎችን እንደማይሳተፋ በመግለጻቸው ምክንያት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የፓርላማ አባላቱን በድርጅታዊ መዋቅር ታኅሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳነጋገሩ መዘገባችን ይታወሳል።