Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአሥር ቢሊዮን ብር በጀት የሚካሄደው የጋራ ቤቶች ግንባታ በኮንትራክተሮች አቅም ማነስ እየተስተጓጎለ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት በአሥር ቢሊዮን ብር በጀት ከሚያስገነባቸው 94,070 የጋራ ቤቶች መካከል፣ በሰኔ 2010 ዓ.ም. 50 ሺሕ ቤቶችን ለማጠናቀቅ የያዘው ዕቅድ በኮንትራክተሮች አቅም ማነስ እየተስተጓጎለ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ በመጋቢት 2010 ዓ.ም. 22 ሺሕ ቤቶችን፣ እንዲሁም በሰኔ 2010 ዓ.ም. ደግሞ 28 ሺሕ ቤቶችን፣ በአጠቃላይ 50 ሺሕ ቤቶችን ለማጠናቀቅ ዕቅድ አውጥቶ ነበር፡፡

ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ለ20/80 የጋራ ቤቶች ፕሮግራም አሥር ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ የቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስፈልገው የግብዓት አቅርቦትም በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት ግን፣ በግንባታ ሒደት የተወሰኑ ኮንትራክተሮች የአቅም ማነስ እያጋጠማቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀን ሠራተኞች ችግርም እየገጠመ በመሆኑ የግንባታ ሒደቱ እየተስተጓጎለ ነው ተብሏል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በገቡት ውል መሠረት ግንባታ ማካሄድ ያልቻሉ ኮንትራክተሮች፣ ተጠያቂ በሚሆኑበት መንገድ ውላቸው እየተቋረጠ ነው፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮንትራክተሮች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ክፍያ እየተፈጸመ ነው፡፡ ሲነሳ የቆየውንም የብረት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ክምችት ካላቸው ቅርንጫፎች ወደ ሌሎች ቅርንጫፎች እየተጓጓዘ ነው፡፡ ‹‹ኮንትራክተሮች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በቁጥጥር ሥር በመሆናቸው በታቀደው ጊዜ ቤቶቹ ይጠናቀቃሉ፤›› ሲሉ እኚሁ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በመላ አገሪቱ 750 ሺሕ ቤቶች የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ 320 ሺሕ ቤቶች በአዲስ አበባ ይገነባሉ ተብሏል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ለ20/80 እና ለ40/60 ቤቶች ፕሮግራም በድምሩ 20 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፣ ይህ በጀት በ2009 ዓ.ም. ከተመደበው በጀት በአምስት ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ ነገር ግን በ2009 ዓ.ም. ተይዞ የነበረው 15 ቢሊዮን ብር በጀት ዘግይቶ በመለቀቁ፣ የቤቶቹ ግንባታ በታቀደው መጠን አለመፈጸሙን በወቅቱ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰኔ 2009 ዓ.ም. ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸው ነበር፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 187 ሺሕ የጋራ ቤቶች ተጠናቀዋል፡፡ እነዚህን ቤቶች ለነዋሪዎች ለማስተላለፍ መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር ወጪ አውጥቶ የመሠረተ ልማት ማሟላቱ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ዕጣቸውን በመጠባበቅ ላይ ቢሆኑም፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ግን ዜጎች በሚፈልጉት ፍጥነት እየተጓዘ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች