Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ አንድምታ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ አንድምታ

ቀን:

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያህል አገሪቱ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ሰፊና ዝርዝር ግምገማ በማካሄድ፣ ቅዳሜ ታኅሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ግምገማ ላይ በነበረበት ወቅት ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሒደትና የደረሰበትን ደረጃ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የሚታዩ የበፊትና ወቅታዊ ችግሮችን ከእነ ዝርዝር መገለጫቸው በመለየት፣ በመንስዔና በመፍትሔዎቻቸው ላይ በመምከር የሐሳብ አንድነትና መተማመን መፍጠሩን አስታውቋል፡፡ አገሪቱ በአንድ በኩል ኢሕአዴግ በተከተለው መሠረታዊና ትክክለኛ አቅጣጫ በተገኙ መልካም ውጤቶች እጅግ የሚያስጎመጅ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ፣ በሌላ በኩል ራሱ ኢሕአዴግ በፈጸማቸው ስህተቶችና ከአገሪቱ ዕድገት ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች መወጠሯን በትኩረት መገምገሙን አስታውቋል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንታት በላይ ባካሄደው ግምገማ፣ በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ዕጦት ሥር እየሰደደ መምጣቱን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ይህም የአመለካከትና የተግባር አንድነት እንዳይኖርም ማድረጉንም አክሏል፡፡ ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመንሰራፋቱ በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመሥርቶ ከመታገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነት መስፈኑን ጠቁሟል፡፡ በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ መርህ አልባ ያለውም ግንኙነት ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶችን ማዳከሙን አረጋግጧል፡፡ በዚህ ምክንያት ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በየትኛውም ክልል ሆነ ብሔራዊ ድርጅት የሚከሰቱ መርህ አልባ ጉድኝቶች በጥልቅ እየተፈተሹ ሊወገዱ እንደሚገባ በመተማመን በአንድነት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ፣ ለአሥራ ሰባት ቀናት በዝግ ሲመክር ቆይቷል፡፡ የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወደ ስብሰባ ከመግባቱ በፊት ብዙ አዳዲስ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው ነበር፡፡ በአንድ በኩል በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተከሰተ ባለው ግጭት የንፁኃን ዜጎች ሕይወት እየጠፋና በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉ ባለበት ጊዜ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀስቅሶ በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት የመማር ማስተማር ሒደት ከመስተጓጎሉ በተጨማሪ የተማሪዎች ሕይወት እየጠፋ ባለበት ወቅት፣ የግንባሩ አመራሮች ወደ ስብሰባ መግባት አዳዲስ ለውጦችንና ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ሲጠበቅ እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአሥራ ሰባት ቀናት ሲያካሄድ የነበረውን ዝግ ስብሰባ ዓርብ ታኅሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አጠናቋል፡፡ በቆይታውም አገሪቱ ካለችበት የፀጥታ ችግር እስከ ግንባሩ አባል ድርጅቶች ውስጠ ዴሞክራሲና ግንኙነት በሰፊው መምከሩን በማግሥቱ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ዝግ ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ከኃላፊነት ለመነሳት ጥያቄ አቅርበው የነበሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ አባዱላ ገመዳ ጥያቄያቸውን እንዳነሱ ተሰምቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) መሥራችና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የሕዝቤና የድርጅቴ ክብር ተነክቷል በሚል ምክንያት ከአፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ መጠየቃቸውን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ የአቶ በረከት ስምኦን መልቀቂያ ተቀባይነት እንዳገኘና የአቶ አባዱላ ገመዳ ጉዳይ ግን ገና ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዝግ ስብሰባው በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ላሉ ጥፋቶች ኃላፊነቱን አመራሩ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡

መግለጫውን በተመለከተም የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቅዳሜ ታኅሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ በጎ ጎኖች እንዳሉት ጠቁመዋል፡፡ ችግሮችን ውጫዊ ለማድረግ አለመሞከር፣ በድፍረት ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅና ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት የችግሮች ምንጭ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ናቸው በማለት ያነሳቸው የነበሩትን ትቶ፣ አገራዊና የብሔር ማንነት ጉዳይ ሚዛናዊ ባለመሆኑ የተከሰቱ ችግሮች ናቸው ብሎ ማመኑ በበጎ ጎን የሚወሰዱ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚያስችል መጠን የችግሩ ምንጭ ተዳሷል ብለው እንደማያምኑ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዋና ዋናዎቹ የችግሮቹ ምንጮች ሳይነኩ ነው ያለፉት፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ በበኩላቸው፣ መግለጫው ከዚህ በፊት ግንባሩ ያወጣቸው ከነበሩት መግለጫዎች የተለየ ነገር የለውም ብለዋል፡፡

በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች፣ በተለይ ደግሞ በከፍተኛው የአመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ዕጦት ሥር እየሰደደ እንደመጣ ማረጋገጡን የሚገልጸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርባቸውን የመታገያ መድረኮች የሚገድብና የሚያጠብ፣ በአመራር ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነትና ጥራት እንዳይፈጠር መሰናክል ሆኖ እንደቆየ መመልከቱን መግለጫው ጠቅሷል፡፡ ዴሞክራሲ እየጠበበና አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመሥርቶ ከመታገል ይልቅ፣ መርህ አልባ ግንኙነትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ሥልት ወደመሆን መሸጋገሩን መግለጫው አስነብቧል፡፡

 ይህን በተመለከተ አቶ ጥሩነህ ሲናገሩ፣ ‹‹ዛሬ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን አጥብበናል ያሉ  ሰዎች ለግጭት ካልሆነ በስተቀር በፊትም ሲሉት የነበረ ነገር ነው፡፡ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲው እየጠበበ ነው ማለታቸውን አድንቁልን ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉምና ፋይዳ የሌለው ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መርህ አልባ ግንኙነት ሲሉ መርሀቸው አንድ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደግሞ አሳታፊ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይኼ መርህ አሳታፊ አለመሆኑን እንደሚያመላክትና ሌሎች ዜጎችን ቀርቶ እነሱንም ሊያስማማቸው እንዳልቻለ የሚያስረዳ ነው፤›› ሲሉም አቶ ጥሩነህ አክለዋል፡፡

አቶ ልደቱ በበኩላቸው ቀደም ባሉት ዓመታት የኢሕአዴግ ትልቁ ችግር ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በሒደት ይኼ እየጠፋ ነው የመጣው፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት የመፍታት ባህል ነበር፡፡ ይኼ እየናረ ቡድናዊ ግንኙነትና ከድርጅቱ ውጪ በሆነ ግንኙነት የመፍታት ባህል እያደገ መጥቷል፡፡ የኃይል ሚዛኑን የሚያዛቡ ግንኙነቶች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ከመረዳት የመነጨ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

መርህ አልባ ግንኙነትን በተመለከተ አቶ ልደቱ ሲናገሩ፣ ‹‹ግንባሩ እንደ ግንባር መሥራት አቅቶታል፡፡ በሥሩ ያሉ አራት ድርጅቶች ነገሮችን በየራሳቸው እየወሰዱ በመሆናቸው ሳቢያ ኢሕአዴግ ችግር ውስጥ እንደሆነ የሚያመላክት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ችግሮችን በብሔር ግንኙነትና በአካባቢያዊ ስሜት ለመፍታት የሚደረገውን ሙከራ ለማውገዝ የተሞከረበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ምንጮቻቸው እንዳልተጠቆመ አቶ ልደቱ ገልጸዋል፡፡ አቶ ጥሩነህ በዚህ ሐሳብ ላይ ይስማማሉ፡፡ አቶ ጥሩነህ እንደሚሉት፣ በመግለጫው ላይ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ጉዳይ ማድረግ የሚገባንን ነገር ሳናደርግ በመቅረታችን የሚል ነው፡፡ ይህ በራሱ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ማድረግ የሚገባውን ማድረግ ባለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ማድረግ የሌለበትን እያደረገ በመምጣቱ ጭምር ነው ለዚህ ሁሉ ችግር አገሪቱ የበቃችው፤›› ሲሉ የሚሞግቱት ደግሞ አቶ ልደቱ ናቸው፡፡

አቶ ልደቱ አሁን የሚባሉት ነገሮች ሁሉ አገሪቱ ካሉባት ችግሮች ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡ አንድም የኅብረተሰብ ከፍል ወጥቶ ኢሕአዴግ ችግር ገጥሞሃል፣ እባክህ ተስተካከል የሚል ጥያቄ ያነሳ አካል እንደሌለ ጠቁመው፣ የሕዝቡ ጥያቄ ከሕዝቡና ከአገሪቱ ጋር ግንኙነት ያለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ አብዛኛው ግምገማ በውስጠ ፓርቲ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ እያልን ያለነው አገሪቱ ስለገጠማት ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከገመገማቸው ጉዳዮች መካከል ሌላው መርህ አልባ ቡድናዊ ትስስር እየዳበረ መምጣቱን የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በየትኛውም ክልል ሆነ ብሔራዊ ድርጅት የሚከሰቱ መርህ አልባ ጉድኝቶች በጥልቅ እየተፈተሹ ሊወገዱ እንደሚገባ መወሰኑን ጠቁሟል፡፡ በአንድ ወይም በሌላ ብሔር፣ ሕዝብና ድርጅት ስም ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን እንቅስቃሴ ማክሰም እንደሚገባም በመግለጫው ጠቁመዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ ሁከት የዕለት ክስተት እየሆነ መምጣቱ ተወስቷል፡፡

ድርጅቱ ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ ረገድ ዳተኝነት እንዳሳየና በዚህም ሳቢያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ችግር እንደገጠመው መግለጫው አትቷል፡፡ አቶ ጥሩነህ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየቀጨጨና የአንድ ፓርቲ የበላይነት እየጎላ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ አመራሮች ከሥርዓቱ ውጪ እንዲሆኑ መደረጉን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ልደቱ በበኩላቸው ኢሕአዴግ በሚከተለው ሥርዓት ምርጫ ቦርድን የራሱ መጠቀሚያ በማድረግና ምርጫን መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ በማለት ሥልጣን በመያዝ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውድድሩ ሜዳ እንዲወጡ በማድረግ የአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀጨጨ መምጣቱን አውስተዋል፡፡

ሥርዓቱ ለበላይነትና ለበታችነት የማይመች ሆኖ እንደተዋቀረ የሚያትተው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ፣ ይኼንን የእኩልነት ሥርዓት ለማዳከም የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለውና ሊመከት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ይኼን በተመለከተ አቶ ጥሩነህ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ‹‹በግንባሩ ውስጥ የበላይነትና የበታችነት አለ ሲባል እንሰማለን፡፡ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) የበላይ ነው ብለው የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ለእኛ ግን የኢሕአዴግ ችግር ከዚህም በላይ ነው፡፡ ፌዴራላዊ አስተዳደር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሰፍኖ ቢገኝም ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ሕዝብ ተንገላቷል፡፡ ሜዳው ጠቧል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ያስራሉ፡፡ ይደበድባሉ፡፡ ይኼ የሚያሳየው ዴሞክራሲያዊነትን ሳይሆን የበላይነታቸውን ነው፡፡ ከድርጅቶች መካከል አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሆነው ሊተያዩ ይችላሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ልደቱ ይኼ ራሱ የኢሕአዴግን ውስጠ ድርጅት ድክመት የሚያሳይ እንጂ፣ የአገሪቱንና የሕዝቡን ትክክለኛ ችግር የሚያሳይ አይደለም ይላሉ፡፡

የአገሪቱ ሚዲያ በሚገባው ደረጃ ነፃነቱ ተጠብቆና የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ያገለግል ዘንድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መገምገሙ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልልም ሆነ በፌዴራል ያሉ የሕዝብ የሚዲያ አውታሮች ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው የማይሠሩበት ሁኔታ እያመዘነ፣ የሕዝቡን ሰላምና አብሮ የመኖር ባህል እየሸረሸረ፣ ብሎም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ አጥፊ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ ለመምጣታቸው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚውም ሆነ የሚመራው መንግሥት ድክመት አስተዋፅኦ እንዳደረገ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

አቶ ልደቱ የሚዲያዎች ግጭት የመፍጠር ሚና ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ›› የተፈጠረ ተደርጎ መገለጹ የሚለው ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የሚዲያዎች ሥራ የተበላሸ የሆነው ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዴሞክራሲው ሁሉ መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴ በአመራር ድክመት ምክንያት ለበርካታ ችግሮች እንደተጋለጠ መግለጫው አትቷል፡፡ ‹‹በዚህ ረገድ የሕዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን ለማንገሥና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶች ያስገኙትን መልካም ፍሬ መጠበቅና ማስፋት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፤›› ሲል መግለጫው አብራርቷል፡፡

ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ በሚገባው ደረጃ ሳይፈጽም መቅረቱ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ጥሩነህ ይህ የሚያሳየው የችግሩን ውጤቶች እንጂ ምንጮች ወይም ምክንያቶች እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ወንጀለኞች ለሕግ ተጠያቂ ሆነው የሚታዩበት ሥርዓት መፈጠር እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት እጃቸው ያሉባቸው ግለሰቦችና አመራሮች ተጠያቂ እየሆኑና ለሕዝቡ ይፋ ባለመደረጋቸው ምክንያት፣ በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ ይኼም ባለመሆኑ ሳቢያ ግጭቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሠረቱ እየሰፋና የከፋ ጉዳት እያደረሰ መምጣቱን አክለዋል፡፡

በአገሪቱ በየደረጃው እየተካሄዱ ያሉና ሊካሄዱም የሚገባቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች የድርጅቱን አገራዊ ራዕይና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚያጠናክር መንገድ በማስኬድ ረገድ ቁጥራቸው የማይናቅ ጉድለት በአመራሩ መፈጸሙ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

አገሪቱን ለአደጋ ማጋለጥ የጀመሩ ጉድለቶች በዋነኛነት የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ድክመቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ችግሮችን የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍትሔ መንገዶችን የመተለምና የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ እንዳላደገና የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም እንደተያዘ ተብራርቷል፡፡ ለተፈጸመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የኢሕአደግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ መግለጫ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል የሚለው የሚታየው ወደፊት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ የተሰበረውን የሕዝብ ልብ የመጠገን ተግባር የተጣለው በድርጅቱ እጅ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹የተባለው እንኳ ተግባር ላይ ይዋል ቢባል በቂ አይደለም፡፡ ሕጎቻችን መፈተሽ አለባቸው፡፡ ብሔር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀቱ መፈተሽ አለበት፡፡ የፌዴራል አደረጃጀቱ መገምገም አለበት፡፡ ችግሩን ማመኑ ጥሩ ሆኖ የምፈታው እኔ ብቻ ነኝ ከሚለው አባዜ መውጣት አለበት፤›› ሲሉ አቶ ልደቱ አብራርተዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ መሠረት በስምንት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመንቀሳቀስና ችግሮችን ለመፍታት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

የመጀመርያው ጉዳይ የሕዝቦችን ሰላማዊ ኑሮ የሚያውኩ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ከሕዝብ ጋር በመሆን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መንግሥት ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ እንደሚያስፈጽም መወሰኑ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ ጥሰቶችን መቆጣጠር፣ መንገድ የሚዘጉ፣ የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት የሚያውኩ  እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መወሰኑን መግለጫው አትቷል፡፡

ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ ከውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሩ የሚታይበትን ድክመት በጥልቀት ገምግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመረኮዘ የማስተካከያና የእርምት ዕርምጃ እንደሚወስድ ተብራርቷል፡፡

ሦስተኛው ጉዳይ እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ የሚታዩ የልማት አቅርቦት ልዩነቶች እንዳሉና ይኼን ለማስተካከል ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ መወሰኑ ነው፡፡

አራተኛው የመንግሥት መዋቅሩን ለሕዝቦች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲችል ለማድረግ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ፣ መስተካከል ያለባቸውን አቅጣጫዎች እንደገና ከሕዝቡና ከፈጻሚ አካላት ጋር በመከታተል ሙሉ ትግበራ ውስጥ እንዲገቡ መወሰኑ ነው፡፡

አምስተኛው ጉዳይ የሕዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ መታቀዱ ነው፡፡

ስድስተኛው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከሕዝቡ ጋር በመሆን ለመቅረፍ አቅጣጫ ማስቀመጡ ነው፡፡

ሰባተኛው የትኩረት አቅጣጫ ደግሞ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የመጣስ አዝማሚያዎችና ተግባራት እንዲመከቱ ውሳኔ ላይ መድረሱ ነው፡፡

የመጨረሻው የትኩረት አቅጣጫ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያራርቅ አፍራሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት፣ አካሄዳቸውን የሚያስተካክሉበት ሁኔታ ለመፍጠር እንቅስቃሴ እንደሚጀምር መወሰኑ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ በአንድነትና በመተማመን አገሪቱ ካለችበት የፀጥታ ችግር በመነሳት የችግሩን ምንጮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በመተለም፣ ተዋናይ የነበሩ አመራሮችና ግለሰቦችን ከሥልጣን ከማውረድ ባሻገር በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሠራር ይዞ ከመጣ እንደ እፎይታ በሚቆጥሩ አሉ፡፡

እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች ውስጥ እጃቸው አሉባቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ሳይውል ሳያድር ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት እንዲዘረጋና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ የፖለቲካ ተንታኞች ያሳስባሉ፡፡ በግጭቶች ውስጥ እጃቸው ያሉባቸውና ከጀርባ ሆነው ተዋናይ የነበሩ አመራሮች በሕግ ጥላ ሥር ሆነው ማየት የብዙ ኢትዮጵያዊያን ምኞት እንደሆነም ይነገራል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት መግለጫዎች ብዙም የተለየ ነገር እንደሌለው የፖለቲካ ተንታኞች ቢገልጹም፣ ድርጅቱ ራሱን ተጠያቂ በማድረጉና ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ በመጠየቁ ጥሩ ጅምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዋናው ጉዳይ ወደ ተግባር በመግባት አገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ቀውስ የማውጣት አሁንም ትልቁ ፈተና እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመግለጫው እንዳስታወቀው በአንድነት የጋራ አቋም ይዞ ከመጣ፣ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የፖለቲካ ቀውስ በማስቆም ሁሉንም ወገን የሚያስማማ አመቺ ሁኔታ መፍጠር የግድ ነው ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...