በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄድ ዝቅተኛ ተሳትፎና ውጤት የሚታይባቸውን የአትሌቲክስ ተግባራት ለማጠናከር ሻምፒዮና ሊዘጋጅ እንደሆነ ተጠቆመ፡፡
ከጥር 15 እስከ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የዕርምጃና የሜዳ ተግባራት የሚያጠቃልለውን የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚካሄድ የፌዴሬሽኑ ድረ ገጽ አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሻምፒዮናው ለሁለት ዓመታት ተከታታይ ሥልጠና ለመስጠት፣ ዕጩ አትሌቶች ለመምረጥና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ዓላማን ያነገበ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ዝናን ካተረፈችባቸው የረዥም ርቀት ባሻገር አጭር ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ላይ ያላትን እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ዓመታዊው ሻምፒዮና ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ሲነግር ቆይቷል፡፡ በተለይ ባለፉት የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ በመካከለኛ ርቀት ወቅታዊ ብቃቷን እያሻሻለች የመጣችው ኬንያ ማሳያ መሆኗን ጭምር እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ኬንያ ከመካከለኛ ርቀት ባሻገር በሜዳ ተግባሩም ሜዳሊያን ማግኘት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይኼንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ታዳጊዎችን በመመልመል እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን የተሻለ ውጤት ያመጡትን አትሌቶችን የሥልጠና ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም ተገልጿል፡፡
በውድድሩ በግል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ አትሌቶችና ለቡድን የሪሌ (የዱላ ቅብብል) ውድድሮች ከዚህ በፊት የገንዘብ ሽልማት ያልነበረ ሲሆን፣ በዘንድሮ ግን ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል ተብሏል፡፡
በግል አንደኛ ለወጣ 2,000፣ ሁለተኛ ለወጣ 1,500 እና ሦስተኛ ለወጣ 1,000 ብር ሽልማት የሚበረክተላቸው ሲሆን፣ በቡድን 4 በ 400 ድብልቅ፣ 4 በ 800፣ 4 በ 1,500 ሜትር እንዲሁም 4 በ 100 ሜትር ከብር 5,000 እስከ 2,000 የገንዘብ ሽልማት እንደየደረጃቸው የሚሸለሙ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራትን የአትሌቲክስ ገደል ዳግም እንድትመልሰና እያሽቆለቆለ የመጣው ውጤት እንዲሻሻል ፌዴሬሽኑ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡
በቀድሞ አትሌቶች እየተመራ ያለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ አትሌቲክሱን ወደ ተሻለ ለማምጣት በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡