‹‹ለአገሬ ያለኝ ፍቅር ለሥልጣን ካለኝ ፍላጎት የላቀና የጠነከረ ነው። ለዚህም ነው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን አሸናፊ ጆርጅ ዊሃን በስልክ እንኳን ደስ ያልዎት ያልኋቸው። በማንኛውም መንገድ ልረዳቸውም ራሴን አዘጋጅቻለሁ። የመርከቧ ካፒቴን ባልሆን እንኳ የመንግሥታችን መርከብ በሰላም እንድትቀዝፍ ጥልቅ ምኞቴ ነው።››
የቀድሞው የላይቤርያ ምክትል ፕሬዝዳንትና ሰሞኑን በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በጆርጅ ዊሃ የተሸነፉት ጆሴፍ ቦዓካይ የተናገሩት፡፡ በዳግም ምርጫ ፉክክር ጊዜ ባሰሙት ቅስቀሳዊ ዲስኩር ‹‹ከአሸናፊነቴ የሚገታኝ አንዳችም አይኖርም›› ያሉት ቦዓካይ መሸነፋቸውን አሜን ብለው ለመቀበል አላቅማሙም፡፡ እንዲያውም አገሬን የማገለግልበት ሌሎች መንገዶች ይኖሩኛል በማለትም አክለዋል፡፡ ተመራጩ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ጆርጅ ዊሃ በአንድ ወቅት የፊፋ የዓለም የእግር ኳስ ኮከብ ተጫዋች ሆነው የተመረጡ በኤሲ ሚላን፣ ፓሪሴን ዠርሜን እና ቼልሲ ክለቦች የተጫወቱት ናቸው፡፡ ዊሃ መንበረ ፕሬዚዳንቱን ከመጀመርያዋ አፍሪካዊት ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ በቀጣዩ ወር ይረከባሉ፡፡