Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ለወደፊት ስኬት መሠረት የሚጣልበት ልጅነት

ወ/ሮ አሰፋች ኃይለ ሥላሴ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (ዩኒሳ) በሳይኮሎጂ ከሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ላይ አተኩሮ አግኝተዋል፡፡ ሥራ የጀመሩት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በማማከር ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ ሠርተዋል፡፡ በጎል ኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የስደት ድርጅት በአማካሪነትና በፕሮግራም ኦፊሰርነት አገልግለዋል፡፡ የሰዎችን አስተሳሰብ በማቅናት በውስጣቸው ያለውን ችሎታ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ቤዝና ካውንስሊንግና የሥልጠና ማዕከልን አቋቁመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ልጆች አስተዳደግ ላይ አዎንታዊ መሠረት መጣል ለወደፊት ሕይወታቸው ስኬት ነው በማለት ‹‹የልጄ ስኬት›› የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በሥራቸውና በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የሥራ ልምድዎም ሆነ ትምህርትዎ ከቤተሰብ ወይም ከግለሰብ ማነፅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ለመጽሐፍዎ መነሻ ነው?

ወ/ሮ አሰፋች፡- አዎ፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ የሠራሁት ከእናቶች፣ ከወጣቶች፣ ከቤተሰቦችና ከልጆች ጋር ነው፡፡ በተሞክሮዬ ያየሁት የሰው ልጅ ትንሽም ቢሆን አመራር፣ ሥልጠናና ምክር ካገኘ የተሻለ ሆኖ መውጣት እንደሚችል ነው፡፡ የተለያየ ችግር ውስጥ የገባ ሰው መቀየርና ውስጡ ያለውን ችሎታ ማውጣት እንደሚችል አምኛለሁ፡፡ መጽሐፉም የዚህን ሁሉ ልምድና ሙያ አካቶ፣ በተለይም ወላጆች ከትዳር አጋር ጀምሮ በልጆች አስተዳደግና ሕይወትን በመምራት በኩል እንዴት መጓዝ እንዳለባቸው የያዘ ነው፡፡ ወላጆች ስንቸገር ምን የምናነበው ማጣቀሻ እናገኛለን? ስለሚሉ የእነሱም ጥያቄ ለመጽሐፉ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ልምዴንም አካትቼ መጻፍ እፈልግ ነበርና የልጄ ስኬት የተባለውን መጽሐፍ ልጅ በማሳደጊያም ሆነ ከቤተሰብ ወይም በእናት አባቱ እጅ ቢያድግ በየትኛውም ሁኔታ ስኬታማ እንዲሆን ከተሞክሮዬ፣ ከሙያዬና ከሥነ ልቦና አንፃር ከእኛ የተሻለ ትውልድ እንዲኖር አልሜ ያዘጋጀሁት ነው፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው የተሻለ ስኬታማ ሆነው እንዲያድጉም ያግዛል፡፡ ይህ ደግሞ የማንኛችንም ወላጆች ምኞት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከሥራ ልምድዎ በልጆችና በወላጆች ላይ የሚንፀባረቁ ክፍተቶች ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ አሰፋች፡- የልጅ አስተዳደግ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ሠለጠኑ በሚባሉት እንኳን ሳይሠለጥኑ የሚገባበት ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ማንም ሰው በቂ ሥልጠና ሳያገኝ የሚገባበት ጉዞ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገር ላይ ክፍተት አለ፡፡ በአገራችን ቀላል የሚመስለን ግን የባለሙያ ዕገዛ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ልጅ ምን ይፈልጋል? የሕይወት ጓደኛ ስንመርጥ ልጅ አስተዳደግ ላይ መክረናል ወይ? ሰዎች ልጅ ከመውለዳቸው በፊት በሕይወታቸው ምን እንደሚፈልጉ ያውቃሉ? የሚሉትና ሌሎችም መታወቅ ባለባቸው የሕይወት ጉዞ ላይ ክፍተቶች አሉ፡፡ ልጅ ከእርግዝና ጀምሮ ምን ይፈልጋል? የእናትና የአባት መስተጋብር ከፅንስ ጀምሮ በልጅ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምንድነው? ምን መደረግ አለበት? የሚለውም መታወቅ አለበት፡፡ ወላጆች ከፅንስ ጀምሮ ነው ልጆቻቸውን በመልካም ሰብዕና ማነፅ ያለባቸው፡፡ ልጆች የሚያዙበት ሁኔታ ላይም ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ በመዋለ ሕፃናት የሚያዙበት አገባብ ላይም እንዲሁ፡፡ ልጆቻችንን ራሳቸውን ላልቻሉ ታዳጊዎች ጥለን እንሄዳለን፡፡ በየሕፃናት እንክብካቤ ተቋማት ያለውም ከሕፃናት ዕድገት አንፃር መታየት አለበት፡፡ ትምህርት ቤት፣ መሰናዶና ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ፣ በወላጆች በኩል ያለው አያያዝ ክፍተት አለበት፡፡ በመጽሐፉም እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ተሞክሯል፡፡ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ፣ በአነስተኛና ጥቃቅንም ሆነ በሌላ የሥራ ዘርፍ ተሠማርተው ራሳቸውን ማስተዳደር ሲጀምሩ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ይህን የፈጠረው በወላጆች ላይ የነበረው ጥገኝነት ነው፡፡ ይህም ሕይወትን ተጋፍጠው መምራትን እንዲፈሩ አድርጓል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ልጆች ከወላጆች ሲለዩ ወላጆች በብቸኝነት ይዋጣሉ? ይህም አንድ ችግር ነው፡፡ ለወላጆች ምን ይመክራሉ?

ወ/ሮ አሰፋች፡- ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲም ሆነ በትዳር ከሸኙ በኋላ በቤታቸው ትልቅ የጊዜ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ከልጆች ጋር የነበረው መስተጋብር ብዙ ጊዜ የሚይዝ ስለነበር ወላጆች ምን ልሥራ ብለው ይቸገራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ባላቸው ሕይወትን እንዴት አጣጥመው መሄድ እንዳለባቸው ማወቅ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ መጽሐፉም ለወላጆች እንደ መምርያ ያገለግላል ብዬ የማስበው ይህንን ሁሉ ስላጠቃለለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በልጆች አስተዳደግ ውስጥ የወላጆች የጤንነት ጉዳይ ዋናው ነው፡፡ ወላጆች ሲታመሙ ልጆች ይጨነቃሉ፡፡ ለምሳሌ አካል ጉዳተኛ ቢሆኑ፣ ኤችአይቪ ቢኖርባቸው ልጆቻቸው ሳይጎዱ እንዴት ማሳወቅ ይችላሉ?

ወ/ሮ አሰፋች፡- ይህ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ወላጆች ራሳቸውን ጠብቀው ከማንኛውም ሕመምና ጉዳት ጋር መኖር ይችላሉ፡፡ ይህንን ቀድሞ ለራስ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ግንዛቤን እያሳደጉም መኖር ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን ሕመምና ጉዳት ውድቀት ባይሆንም ለልጆች መንገር ይከብዳል፡፡ ሆኖም በሕመሙ ምክንያት ለሚመጣው እክል ልጅን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለልጆች ለመንገር የልጆች ዕድሜ ቢያንስ አሥር መሙላት አለበት፡፡ በተለያዩ ምሳሌዎች አድርጎ ከሕመም ጋር መኖር እንደሚቻል መንገር፣ በኋላም ስለራስ በግልጽ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለቅርብ ዘመድ ማሳወቅም መልካም ነው፡፡ ልጆች ምኑንም ሳያውቁት ወላጆቻቸውን በሕመም ሳቢያ አጥተው ከሚበተኑም ቀድሞ መፍትሔ ማበጀቱም ይመከራል፡፡ ኤችአይቪ፣ ልብ ድካምና ሌሎችም ሕመሞች ያሉበት ወላጅ ለልጆቹ ቢያሳውቅ ይጠቅማል፡፡  

ሪፖርተር፡- ልጆች ከወላጅ ሲለዩ ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲ መግባት ሊሆን ይችላል ሲደናገሩ፣ በራሳቸው መተማመን ሲያጡና ሲፈሩ ይታያሉ፡፡ ቤት የለመዱትን ትተው ምግብን ጨምሮ ያሉበትን ድባብ ለመልመድ ሲቸገሩ፣ ወላጆች በየዩኒቨርሲቲው የልጆቻቸውን ደኅንነት አላምን ብለው በየጊዜው እየሄዱ ሲጠይቁ፣ በተገኘው አጋጣሚ ምግብ ሲልኩና ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ ይህ ልጆች በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ መኖር እንዳይችሉ አስተዋጽኦ አያደርግም?

ወ/ሮ አሰፋች፡- ራስን መቻል ከልጅነት ጀምሮ እየተቀረፀ የሚሄድ ቢሆንም፣ ልጆች ከወላጅ ዕይታ ውጪ ሲሆኑ ራሱን የቻለ ሌላ የሕይወት ምዕራፍ ነው፡፡ ወፍ ከጎጆዋ እንደምትወጣ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለልጆች ስለገንዘብ አጠቃቀምም ሆነ ከወላጅ ተነጥሎ በሚኖርበት ጊዜ ሊገጥም ስለሚቸል ሁኔታ ማስተማር አለብን፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ መሆን የሚፈልጉትን ቀድመው እንዲያልሙ ማድረግም ይገባል፡፡ ወላጆች ከአቅም በላይ ብር እየሰጡ ልጆቻቸው ያሉበት ቦታ ምግብ የሌለ እስኪመስል ምግብ እየተሸከሙ ሲሄዱ ይታያል፡፡ ወላጆች ፍቅር አይግለጹ፣ ለልጆቻቸው አያስቡ አላልኩም፡፡ ነገር ግን ወላጆች እያተኮሩ ያሉት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ላይ ነው ወይ? የሚለውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ እኛም ዩኒቨርሲቲ ስንማር የምንበላው እንጀራ ከድርቀቱ የተነሳ ቅፅል ስም ነበረው፡፡ ያን በልተን ተምረናል፡፡ ምን ሆንን? በሥፍራው  ያለውን ተግዳሮት እንዲያዩት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከእናት ጎጆ እየወጡና ሕይወትን እያዩት ነው፡፡ ዓላማ የለሽ ተግባር ላይ እንዳይሠማሩ ማድረጉ ላይ ማተኮር፣ ሕይወታቸውን በራሳቸው ኃላፊነትና ውሳኔ እንዲሞክሩት ዕድል መስጠት አለብን፡፡ ሁል ጊዜም የተሻለ ሕይወት መኖር ይቻላል፡፡ ይህንን መርህ ያደረገ ተማሪ ከወላጆቹም ቢወጣ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸውን ማዘጋጀት ያለባቸው ዓላማ ይዘው እንዲያድጉ ነው፡፡ ለልጆች እጅግ በጣም እንክብካቤ ሲበዛም ስስ ቆዳ ያላቸው፣ ምንም እክል መቋቋም የማይችሉ ይሆናሉ፡፡ ፈተናንም ማየት አለባቸው፡፡ ወላጆች ችግርን አልፈው ለውጤት ከበቁ ልጆችም ይህን የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው ማድረግ እንጂ ጥገኛ እንዲሆኑ መተው የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም በውስጡ ሊጠቀምበት የሚችል ችሎታ አለው፡፡ ልጆች ራሳቸውን እንዲችሉ አዘጋጅቶ መልቀቅ ያስፈልጋል፡፡     

ሪፖርተር፡- ወንድ ልጅና ሴት ልጅ ማሳደግ በመጽሐፍዎ ያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ ቤት ውስጥ ለሴትና ለወንድ ሥራን ለይቶ መስጠት ወይም ጭርሱኑ ሥራ አለማሠራት ይስተዋላል፡፡ ሥራን ቤት አስለምዶ ማሳደጉ ለወደፊት ሕይወት ተፅዕኖው ምንድነው?

ወ/ሮ አሰፋች፡- ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ መብላት የሚፈልግ ሁሉ መሥራት መቻል አለበት፡፡ ሴትም ሆነ ወንድ በቤት ውስጥ ከልጅነት ጀምሮ የሚመጥን ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ለትምህርት ከዚህ ወደ ውጪ ከሚሄዱት ልጆች አብስለው የሚበሉት ገዝተው ከሚበሉት በኢኮኖሚ የተሻሉ ናቸው፡፡ ቤት ውስጥ ምግብ ማብሰልን ጨምሮ ሥራ መሥራት የሕይወት ክህሎት ነው፡፡ ልጆችን ከልጅነት ጀምሮ ሥራን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ልጆች ፆታን ሳይለይ ሙያ ማወቅ አለባቸው፡፡ ሁለቱም እኩል ሠርተው ካደጉ ወደፊት ተቀጥረውም ሆነ የራሳቸውን ሥራ ሲሠሩ ነገሮችን እንዴት መምራትና ማቃናት እንዳለባቸው መሠረት ይጥላሉ፡፡ በቤት ውስጥ፣ ወጥ ቤትም የሁሉም መሆን አለበት፡፡ ሠርቶ መብላት የሚፈልግ ራሱ አብስሎ የሚበላበት፣ ለሌሎችም ሠርቶ የሚያቀርብበት ሊሆን ይገባል፡፡ ወላጆችም ይህንን ማበረታታት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ ጥሩ ቤተሰብ፣ ጥሩ ወላጅ፣ ጥሩ የአገር ዜጋ እንዲሆኑም ያግዛል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ አሊያም ሙሉ ለሙሉ ሲለቁ ይታያል፡፡ ወላጆችም የቴክኖሎጂ ምርኮኛ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ በመጽሐፍዎም ይህንን ዳሰዋል፡፡ ምን ይመክራሉ?

ወ/ሮ አሰፋች፡- ያደጉት አገሮች ቴክኖሎጂን በረከትም፣ እርግማንም ይሉታል፡፡ ማንኛውንም ቴክኖሎጂ አያያዙን ካላወቅንበት የጥቅሙን ያህል ጎጂም ነው፡፡ በቤተሰብና በአገር ደረጃ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም የጊዜ አጠቃቀም፣ ማኅበራዊ ተግባቦት ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ጊዜውን በብዛት ቲቪ፣ ስልክ ወይም ላፕቶፑ ላይ ያጠፋ ሰው ማኅበራዊ ተግባቦቱም ይጠፋል፣ ለሌሎች ሥራዎች ማዋል ያለበት ጊዜም ይባክናል፡፡ የግለኝነት ሕይወትንም ያመጣል፡፡ ውጭ ያሉ ሰዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመርጧት ብቸኝነት ሰልችቷቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ሰብሰብ ብሎ በዓል ማክበርም ሆነ መኖር ይናፍቁታል፡፡ እነሱን ለግለኝነት ሕይወት ያበቃቸው ቴክኖሎጂን በአግባቡ አለመጠቀማቸውም ነው፡፡ እኛም ጋ ቴክኖሎጂ ቤተሰብ ውስጥ ፈተናን ይዞ ገብቷል፡፡ ልጅ አይፎኑን ይዞ ይቀመጣል፣ ወላጆች በቲቪ ይጠመዳሉ፡፡ ይህንን ሥርዓት ካላስያዝን፣ ወላጆች ዕውቀታቸውን ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉበትና አብረው ቁጭ የሚሉበት ጊዜ ካላመቻቹ የቴክኖሎጂው መምጣት ጥቅምን ብቻ ሳይሆን ጉዳትንም ያስከትላል፡፡ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም የቴክኖሎጂው ሰለባ እየሆኑ ስለሆነ ይህንን ማጤንና መለወጥ ይስፈልጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...