Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአገር በቀል ዕውቀትን በውጪ መሥፈርት መመዘን ለምን?

አገር በቀል ዕውቀትን በውጪ መሥፈርት መመዘን ለምን?

ቀን:

ሲሳይ በገና የዜማ መሣሪያዎች ማሠልጠኛ ተቋም ከተመሠረተ አራት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ያሳለፍነው እሑድ በትምህርት ቤቱ የበገና፣ መሰንቆ፣ ክራርና መለከት ሥልጠና የወሰዱ ተማሪዎች የሚመረቁበት ቀን ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም በሦስት ዙር ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፣ በእሑዱ አራተኛ ዙር 77 ተማሪዎች ተመርቀዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል በበገና 49፣ በክራር 23፣ በመሰንቆ ሦስትና በመለከት ሁለት ሠልጣኞች ይገኙበታል፡፡

በዕለቱ ትምህርት ቤቱ ለሁለት ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ መምህር አለማየሁ ወልደዮሐንስ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎችን በማስተማር፣ የመሰንቆ፣ ክራርና ዋሽንት ማስተማሪያ በመጻፍና የኢትዮጵያ ቅኝቶች ኢትዮጵያዊ ስያሜ እንዲኖራቸው በማድረግ›› በሚል ነበር የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው፡፡ በተጨማሪ መቶ አለቃ ተስፋዬ ኃይሌ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች መሰንቆና ክራር ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው በመሥራት ለትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ›› የሚል የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የዕለቱ ከዋክብት የነበሩት ተመራቂዎች፣ በየሠለጠኑበት የዜማ መሣሪያ ለ120 ሰዓታት በትዝታ፣ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ ለኔና አምባሰል ቅኝቶች ትምህርት መውሰዳቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ተረክበዋል፡፡ በምስክር ወረቀታቸው ግርጌ፣ ወረቀቱ ሥልጠና ስለማጠናቀቃቸው ማስረጃ እንጂ የብቃት መመዘኛ ባለመሆኑ፣ በሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል መመዘን እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከተማሪዎቹ አብዛኞቹ የዜማ መሣሪያዎቹን የሚማሩት ለግል ፍላጎታቸው እንደመሆኑ ከምዘና ሒደቱ በበለጠ ሥልጠናው ላይ ያተኩራሉ፡፡ ሆኖም በትምህርት ቤቱ የሚያስተምሩ መምህራንና ተማሪዎችም የሙያ ብቃት ምዘና ማድረግ አለባቸው መባሉ አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው የትምሀርት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና መምህር ሲሳይ ደምሴ ይናገራል፡፡ ችግሩ ችሎታቸው መመዘኑ ሳይሆን፣ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ተምረው በዘመናዊ የምዕራባውያን የሙዘቃ መሣሪያዎች መፈተናቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎችን ከተማሩ በኋላ ፒያኖና ጊታርን በመሰሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይፈተኑ መባሉ፣ ትምህርት ቤቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እንደሚጣረስ መምህሩ ይናገራል፡፡ ሲሳይ፣ በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ የመጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋን የበገና ዜማ ከሰማበት ጊዜ አንስቶ፣ ለበገና ልዩ ፍቅር ያድርበታል፡፡ በገናን ተምሮ፣ ማስተማር ብቻ ሳይሆን እየሠራ ማከፋፈል እንዳለበት በማመንም ትምህርት ቤቱን ከፈተ፡፡

የኢትዮጵያ የዜማ መሣሪያዎችን የሚጠቀምና የሚንከባከብ ትውልድ መፍጠርን ዓላማ አድርጎ ትምህርት ቤቱን መክፈቱን ይናገራል፡፡ በገና፣ መሰንቆ፣ ክራርና ዋሽንት የሚያስተምሩ እንዲሁም መሣሪያዎቹን ሠርተው ለገበያ የሚያቀርቡም እምብዛም ስላልሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት መነሳሳቱን ይገልጻል፡፡ በዋነኛነት በገና እና ሌሎቹም የዜማ መሣሪያዎች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው በመሆኑ፣ የዜማ መሣሪያዎቹን የሚጫወቱ ሰዎችን ማብዛትና ገበያ ላይ የሚገኙ መሣሪያዎችን ቁጥር መጨመር አስፈላጊ ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ በሆኑ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ዙሪያ መሥራት ያለብን እኛ ነን፤ የውጪ ባለሙያ መጠበቅ የለብንም፤›› ይላል፡፡ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎቹ በማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወትም ካላቸው ጉልህ ሚና አንፃር፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነቱ በሁሉም ሰው ላይ እንደሚወድቅ ይገልጻል፡፡ ‹‹አገር ስትወረር አገርን ለመጠበቅ ያነሳሱ፣ በሰላም ወቅትም በማኅበረሰቡ ውስጥ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው፤›› ሲል የዜማ መሣሪያዎቹን ይገልጻል፡፡

ትምህርት ቤቱ መሣሪያዎቹን የማስተዋወቅና ተደራሽነታቸውን የማስፋፋት ግቡን ለማሳካት ሲነሳ፣ ከገጠሙት መሰናክሎች በግንባር ቀደምነት የሚገልጸው የምዘና መስፈርትን ነው፡፡ ትምህርት ቤቱን ለመክፈት እንዲሁም በቀጣይ ዓመታት ዘላቂነት እንዲኖረውም ፒያኖ መቻል እንደሚጠበቅበት እንደተገለጸለት በአግራሞት ይናገራል፡፡ ከዚህ ቀደም የፒያኖ ትምህርት በመውሰዱ የቀረበለትን ፈተና ለማለፍ አልተቸገረም፡፡ ቢሆንም በትምህርት ቤቱ የምታስተምር መምህርትም ተመሳሳይ የምዘና ፈተና እንድታልፍ በሚል ፒያኖ ለማስተማር ተገዷል፡፡

ሲሳይ እንደሚለው፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ለማስተማር በባህር ማዶ የሙዚቃ መሣሪያዎች መፈተን ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የዜማ መሣሪያዎች ዕውቀትን መመዘን ትርጉም ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ መሣሪያዎች ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ስለ ኢትዮጵያ ቅኝቶች ወይም የዜማ ጽንሰ ሐሳብ መፈተንም ይችላሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በምዕራባውያን የሙዚቃ መሣሪያ መመዘኛችን ሲሆን ያሳዝናል፤›› ይላል፡፡

መምህሩ ጉዳዩን የሚመለከተው ለኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ዋጋ ካለመሰጠቱ አንፃር ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ይጠፉ ይሆን በሚል ሥጋት ውስጥ ያሉ ባህላዊ መሣሪያዎችን መጠበቅ ሲያሻ፣ በተቃራኒው ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ያምናል፡፡ በኢትዮጵያ ባህላዊ የትምህርት ሥርዓት ተማሪዎችን ማብቃት ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወስድ በማጣቀስ፣ በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ላይ ያለውን ጥያቄ ይሰነዝራል፡፡

በመሰንቆ እንደ ዓለማየሁ ፋንታ፣ በበገና እንደ መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ ያሉ ባለሙያዎችን ለማፈራት ሥርዓቱ አልጋ በአልጋ መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡ የውጪ አገር የሙዚቃ መሣሪያዎችን ለኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች ዕውቀት መሠረት ማድረግ ‹‹በገዛ እጅ ቅኝ ከመገዛት አይተናነስም፤›› ሲል ይገልጸዋል፡፡

ማንኛውም ሰው አንዳች ትርጉም የሚሰጠውን መሣሪያ የመማር ነፃነት እንዳለው እሙን ነው፡፡ የዜማ መሣሪያውን ተምሮ ለግላዊ ደስታ ማዋል አልያም በሙያነት ይዞ መቀጠልም ይቻላል፡፡ በየትኛውም መንገድ ቢሆን ግን መመዘኛው መሆን ያለበት የመረጠው መሣሪያ መሆኑን ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያን ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች የሚያስተምሩ፣ የሚማሩ፣ በመሣሪያዎቹ ዙሪያ ጥናት የሚሠሩ ሰዎችን ማበረታታት እንጂ በተለያየ ምክንያት ማደናቀፍ እንደማይገባም በአጽንኦት ይናገራል፡፡

በኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎችና በምዕራባውያን የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በየትኛውም አገር ለራስ ባህላዊ ሀብት ቅድሚያ መስጠት የተለምደ ነውና፣ ኢትዮጵያውያንም ለአገር በቀል የዜማ መሣሪያዎች ትኩረት ቢሰጡ መልካም ነው ይላል፡፡

‹‹የራሳችን ፊደል፣ የራሳችን ቋንቋ፣ የራሳችን የዜማ መሣሪያና የራሳችን ማንነት እያለን እንዴት በሌላ አገር ዕውቀት እንለካለን?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች እንደ ማሳያ ቢወሰዱም፣ በሌሎች ዘርፎችም ለአገር በቀል ዕውቀት አናሳ ግምት እንደሚሰጥ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ‹‹ከውጪ የመጣ ሁሉ የተሻለ ነው›› የሚል የተዛባ አመለካከት የወረራቸው የሙያ ዘርፎች በርካታ ናቸው፡፡

በተያያዥ የባህላዊ መሣሪያዎች ትምህርት የሚሰጥበት ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ የዜማ መሣሪያዎቹን አሠራርና አጨዋወት ያማከለ መማሪያ መዘጋጀት አለበት፡፡ የዜማ መሣሪያዎቹን የሚማሩ ሰዎችም በወሰዱት ሥልጠና ተመዝነው፣ የተማሩትን መሣሪያ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

መምህሩ በሚሰጠው ምሳሌ መሠረት፣ አንድ ሰው ክራር የሚማርበትና ችሎታው የሚፈተንበት መንገድ የክራር አያያዝ፣ የጣት እንቅስቃሴ፣ የምት ጊዜ አጠባበቅ፣ የድምፅ አወጣጥ፣ ዜማ መሥራትና ሌሎችም መስፈርቶች መሆን አለባቸው፡፡ ‹‹በመቀጠል በክራር ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት በማለት ደረጃ ሊቀመጥ ይገባል፤›› ይላል፡፡ ለአገር በቀል ዕውቀት መፈተሻው አገር በቀል መስፈርት እንጂ የውጪ የሙዚቃ ችሎታ መሆን የለበትም፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዜማ መሣሪያዎችን የተመለከተ ሥርዓተ ትምህርትና የምዘና ሥርዓትን በማስጠበቅ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥያቄ ማቅረቡን ሲሳይ ይናገረል፡፡ በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎችን በማምረት ረገድ ያሉ ችግሮች መቀረፍ አለባቸው፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ የዜማ መሣሪያዎች ጥበቃ የሚያደርግ አካል በጽሑፍ እንጂ በተግባር የለም፤›› ይላል፡፡

መምህሩ፣ ፍፁም ግሩም  ከተባለ ሸሪኩ ጋር የዜማ መሣሪያዎችን ያመርታል፡፡ ሆኖም ባህላዊ መሣሪያዎች መሥራት በሚል ዘርፍ መንቀሳቀስ ከባድ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ለኢትዮጵያ የዜማ መሣሪያዎች ሥራ የንግድ ዘርፍ ስያሜ ሊሰጠው እንደሚገባም ያሳስባል፡፡ ‹‹አገር በቀል ሐሳብን ለማራመድ ከባድ ነው፤›› የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡ አሁን እየሠሩ ያሉት የዕደ ጥበብና ገጸ በረከት መሸጫና ችርቻሮ ንግድ በሚል ዘርፍ ነው፡፡

ባህላዊ የዜማ መሣሪያዎችን ጨምሮ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ዘርፍ በማምረቻ ግብአት ዕጥረት፣ በማምረቻና የመሸጫ ቦታ ውስንነት ይፈተናል፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባት በዘርፉ የሚሰማሩ ሙያተኞች ድገፍ እንዲያገኙ ይጠይቃል፡፡ ለባህላዊ የዜማ መሣሪያዎች የአሠራር ደረጃ መውጣት እንዳለበት በርካታ ባለሙያዎች ለዓመታት ተናግረዋል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ባህላዊ የዜማ መሣሪያ የሚያመርቱ ባለሙያዎች ቦታ ተሰጥቷቸው፣ ሥራዎቻቸው በአግባቡ ለገበያ መቅረብ  አለበት፡፡

ባህላዊ መሣሪያዎችን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት የነበረው ውጣ ውረድ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር መፍታት መቻሉን ይገልጻል፡፡ የዜማ መሣሪያዎቹ አዲስና እንደ ቅርስ ተቆጥረው ለዝውውር የማይከለከሉ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመጻፍ፣ መሣሪያዎቹን ገዝተው ወደተለያዩ አገሮች የሚወስዱ ሰዎችን አንቅስቃሴ ሕጋዊ ማድረግ ተችሏል፡፡ አዳዲስ የዜማ መሣሪያዎችን ከአገር ውጪ ይዞ ለመዘዋወር፣ ትምህርት ቤቱ ላቀረበው ጥያቄ ባለሥልጣኑ አፋጣኝ ምላሽ እንደሰጠው፣ ሌሎች ችግሮቻቸውም እንዲፈቱ የሚመለከታቸው ተቋማተ እንዲተባበሩ ይጠይቃል፡፡

‹‹መስዋዕትነት የተከፈለላት አገር ናት፡፡ ያለፈው ትውልድ ባህላዊ ቅርሶቿን ጠብቆ እንዳስተላለፈልን እኛም ለሚመጣው ትውልድ ማሸጋገር አለብን፤›› ይላል፡፡ ባህሉን የማያውቅና የማያከብር ትውልድ፣ ባህሉን ለመጠበቅ ተቆርቋሪነት እንደማይሰማው በመግለጽ፣ የባህል መገለጫዎች ዕውቀትን ማስፋፋት ትኩረት እንዲሰጠው ይጠይቃል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የዜማ ሊቁ የቅዱስ ያሬድ አገር ሆና የኢትዮጵያን የዜማ መሣሪያዎች ችሎ

ታ በምዕራባውያን መለካት ያሳፍራል፤›› ይላል፡፡ አገር በቀል ዕውቀት እንደ ‹‹ኋላ ቀርነት›› እያየ የውጪውን የሚናፍቅ ትውልድ አገሪቷን ጠራርጎ ከመውሰዱ በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ የራስን ነገር ለመውደድ የራስን ማወቅ የግድ በመሆኑ፣ ባህል ላይ ያተኮሩ ተቋሞች እንዲበረታቱም ያሳስባል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...