እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከስታዲዮም ወደ መርካቶ ነው። ተሳፋሪዎች ቦታችንን ከያዝን ቆየት ማለት ጀመርን። ከብዙ ዓይነት የሕይወት መንገድ፣ አስተሳሰብና እምነት ያለቀጠሮ ታክሲያችን ውስጥ መሰባሰባችን እየቆየ የሚደንቀን ጥቂት ነን። መንገዱ ገና በዓል በዓል መሽተት አልጀመረም፡፡ ነዋሪው የዕለት እንጀራውን ብቻ ለማሳደድ ታጥቆ የተነሳ ይምስላል። የቀናው ከእንጀራው ያልፍና እስከ ጫፍ ይጓዛል፣ ይፋቀራል፣ ይዛመዳል፣ ይወልዳል፣ ይከብዳል። ዕድለ ጠማማ ከሆነ ግና ከመፋቀር መጉደሉ ሳያንስ፣ በሰላም መለያየት ሳይቀናው በዘር ይቧደናል። በጎሳ ይቀምራል። ደግሞ ዞሮ ዞሮ የጊዜውን ፋሽን ለብሶና ተጫምቶ ሲመጣ ታዩታላችሁ። ወንድሙን ጠልቶ፣ የቅርቡን ንቆ፣ እኔ የዓለም ዜጋ ነኝ የሚል ‘ቲሸርት’ የሚለብሰው መንገዱን አጣቦታል። ንክኪ የሚባል የሕይወት ጥበብ እዚህ ውስጥ ነው ፈትሉ። የሚያውቀው ሲረዳው፣ ያላወቀው ሲያልፈው የሕይወት ፍሰትን የሚያስቆመው የለም። ትናንት ዛሬ እንደ ደረሰ ዛሬ ነገን ሊያደርስ ከንፎ ያከንፈናል።
ሽበታሙ ሾፌራችን የመቀመጫ ቀበቶውን አጠባብቀው ሞተሩን አስነስተዋል። እሳቸውም የወያላውን ብቅ ማለት እንደ ሎተሪ ዕጣ በጉጉት የናፈቁ መስለዋል። ወያላው በበኩሉ የቆመበት አልታይ የደረሰበት አልታወቅ ያለ ይመስላል። ‹‹የት ሄደ ደግሞ?›› ይላሉ ሾፌሩ በለሆሳስ። እሱ ግን ሊከሰትልን አልቻለም። ‹‹ወያላችን ቀረ ብለን እንዝፈን እንዴ? መቼም ሳይዘፈንለት አልያም ሳይዘፈንበት የቀረው እሱ ብቻ ነው መሰለኝ፤›› አለ ቀጠን የሚል ወጣት። አጠገቡ የተቀመጠ እሱን መሳይ፣ ‹‹ተው ተው የሚቀርብን እንደ ኢኮኖሚያችን በሁለት አኃዝ በጨመረ ቁጥር ለስንቱ ዘፍነን እንችለዋለን?›› ብሎ በስላቅ ሲመልስለት፣ ‹‹አይዞህ ተምረው ሲከስሩ እንጂ ዘፍነው ሲከስሩ እያየን አይደለም። ግን መቼ ነው በዘርና በጎሳ ፀብ እየተፈናቀሉ ላሉ ወገኖቻችን የሚዘፈንላቸው?›› ብሎ ከማዶ ጎልማሳው ጮኸ። ‹‹በዘፈን ሊገላገላቸው ያምረዋል እንዴ?›› ብሎ ተሳፋሪው በአሽሙር ሲወጋው እሱ አልሰማም። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነዋ።
ወያላው ራቅ ብሎ ቆሟል። ‹‹የት ነው?›› እያለ እርስ በርሱ ተጠያይቆ የሚሳፈረው መንገደኛ ብዙ ነው። ‹‹የመረጃ እጥረት ብሎ ብሎ ታክሲ ተራ ገባ?›› ሲል አንድ ወጣት መንገደኛ፣ ‹‹ከላይ ከተጀመረ ወደ ታች መውረዱ መቼ ሊከብድ? ኧረ ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዴት ነው መረጃ በትክክል እየደረሳቸው ነው? መቼ ነው አንድ ጊዜ እኔ ራሱ የሚነገረኝ ሌላ የሚሠራው ሌላ ሲሉ አስታውሳለሁ…›› ብሎ አንድ ጎልማሳ ነገር አደመቀ። ‹‹ሰው ምን እንደሚታየው እንጃለቱን ታክሲ ሲሳፈር የአሜሪካን አፈር የረገጠ ይመስለዋል እኮ?›› ይለዋል አንዱ አብሮት ለሚጓዘው ጓደኛው። ‹‹እንዴት?›› ሲለው፣ ‹‹አትታዘብም ታክሲ ውስጥ በነፃነት ሰው እንዴት እንደሚናገር?›› በአግራሞት እያየ ጠየቀው። ‹‹መብቱ ወረቀት ላይ ብቻ ነው ቢባልም የትም ይሠራል። ይልቅ የሚገርመኝ ሰው ታክሲ ሲሳፈር የሚያመጣው የማውራት ድፍረት ነው፤›› እየተባባሉ ቀጠሉ። አዳማጩ ጆሮውን አንቅቷል። የሚጥለውን እየጣለ የሚለቅመውን ልቦናው ይቁጠረው። አላምጦ መብላትና መስማት ሕመሙ ሲከብደን አላውቀው ብለናል። አዳሜ ሳያላምጥ ሲውጥ ከነገር እስከ እንጀራ እያነቀው አለሳዝን ማለት ጀምሮላችኋል። አለመተዛዘን ለካ እንዲህ ቅርብ ነው? እንበል ይሆን?
ጉዟችን ተጀምሯል። መጨረሻ ላይ የገባው ተሳፋሪ አርቲፊሻል የገና ዛፍ ይዞብን ገብቶ ዳርና ዳር የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ተጨናንቀዋል። ‹‹በዚህ ኑሮ እንጀራ እያነቀን ስንባክን፣ ነገር እያነቀን ስንባክን ጉድ አይደል? ብክነትና ብክለት ምነው መንገዱን ሞላው? ይኼ አልበቃን ብሎ ደግሞ በዚህ ገንዘቡንም እንበትነዋለን፤›› ሲል እንሰማለን ከኋላ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፈሪ ዛፉን እየጠቆመ። ‹‹መባከን የመንገድ አንዱ ምልክት ነው ሲባል ስትሰሙ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ደግሞ የብዙ ሰው አቅምና ዕድሜ ሲባክን አይታያችሁም?›› ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ባለ ጉዳይ መሳይ ወይዘሮ።
ታክሲያችን አጠገብ ካለው የመንገዱ ቋሚ ግንብ ሥር ማንም አያየኝም ባይ ሰካራም ሽንቱን በሰመመን ይሸናል። በጭራሽ አላየንም። ‹‹እግዚኦ!›› ይላል በኃፍረት ተሸማቆ አብዛኛው መንገደኛ። እፍረቱ ከድምፁ ቃና ይፈልቃል። ሰካራሙን ላለማየት የታክሲዋ ጣራና መሬት ላይ ያፈጣል። ‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ ክልክል ነው ሲባል፣ ይቻላል ሲባልም ተቃራኒ መሆን የምንወደው ነገር ነው። ማጨስ ክልክል ነው፣ ማለፍ ክልክል ነው፣ ወዘተ ሲባል ቡራ ከረዩ። እልህ ያንቀናል። መለወጥ ይቻላል፣ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል ሲባል ቁዘማና መታከት። ምንድን የሚሻለን?›› ሲል፣ ‹‹ፉከራና ቀረርቶ እንጂ እሺ ባይነትና ሥራ ስላለመደብን አይመስልህም?›› አለው ጎልማሳው። ‘ስንቱን አሳለፍኩት ስንቱን አየሁት…’ ይላል የትዝታው ንጉሥ ከወደ ስፒከሩ!
ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጨርሶ መልስ እየሰጠን ነው። ከወደ ሬዲዮኑ ሙዚቃው አልቆ ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ጋር በተያያዘ ከኢንተርኔት የተቃረመ መረጃ ይረጫል። ይኼኔ አንዱ መጨረሻ የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹ከዘንድሮ ወሬኛ እኮ ወጣቱ ተሻለ እናንተ። መብትና ግዴታውን ማውቅ እየጀመረ ነው። መቼ ነው ግን እነዚህ ሰዎች የሚማሩት?›› ካለ በኋላ ዝም ስንለው፣ ‹‹የኢንተርኔት መረጃ መጎርጎር ሥራ ሆነ እንዴ? ሰሞኑን ደግሞ ያበሩታል፣ ያጠፉታል…›› ብሎ ስልኩን መጎርጎር ጀመረ። ‹‹ኢንተርኔቱማ ይሠራል ጭንቅላታችን ነው እንጂ አልሠራ ያለው፤›› ትለዋለች ከጎኑ የተሰየመች ልጃገረድ። ‹‹እንዴ እንደዚያ አይባልም፤›› ይላታል። ‹‹እንዴት አይባልም? ሰው ማሰብ እስከሚችለው ድረስ (ተማረም አልተማረም) ማሰብ የሚያቅተው ፍጡር አይደለም። ሰላም፣ ፍቅር፣ ደግነትና እርስ በርስ መተሳሰብ በልቦናችን ያሉ እሴቶቻችን ናቸው። ታዲያ ከዚህ ውጪ ሲሆን ሰው ምን ሊባል ነው?›› ስትለው፣ ‹‹ልክ ነሽ። ግን አየሽ ልቦና የሚባል ነገር አለ።
እስከ ዛሬ ይኼ ልቦና የሚባል ነገር መቀመጫው የት እንደሆነ አልታወቀም። ጭንቅላት ውስጥ ይሁን ደም ሥር ውስጥ ተስማምቶ የሚነግረን ጠፍቷል። ታዲያ ይኼ ልቦና የሚባል ነገር ፍቅር ሰላም መረዳዳት ብቻ ሳይሆን የሚያመነጨው እልህ፣ ቂም፣ በቀል እብሪት አምባገነንነትና መሰል እኩይ እሳቤዎችም አለው። ጭንቅላት ሥራው የፈቀዱለትን ማቀነባበር ነው እንጂ፣ ሥራ ፈታ ማለትማ አበቃ ማለት እኮ ነው…›› ይላታል። ‹‹ዋት ኤቨር›› ትለዋለች። ይኼኔ አዛውንቱ ገልመጥ ብለው ወደኋላ እያዩ ‹‹ቅዱሱ መጽሐፍም የሰው ልብ ውስጡ እጅጉን ክፉ ነው ይላል እኮ? ምን ዙሪያ ጥምጥም ያስኬዳችኋል?›› ብለው ከራሳቸው ጋር ማውራት ሲቀጥሉ፣ ‹‹ልብ ብቻውን ምን ዋጋ አለው? ቢከፋም ቢለማም ምን ያመጣል?›› አላቸው አጠገቤ የተሰየመው ወጣት። ነገረ ሥራው አልዋጥላቸው እንዳለ ነው። ‹‹እኮ ምን ልትል ነው?›› ሲሉት፣ ‹‹ዘመን ካላገዘው ማለቴ ነው። አንዳንድ ዘመን አለ የሰላም፣ የተድላና የፍቅር። አንዳንድ ዘመን ደግሞ አለ ሳይወዱ በግድ ነገር ሠርቶ ለነገር አሿሪ አሳልፎ እየሰጠ በአጭር የሚቀጭ፤›› ሲላቸው፣ ‹‹አሁን እውነት አወራህ፤›› ብለው ፈገግ አሉ። ‘አንዳንድ ዘመን አለ ምን ቢያምጡ ሳቅ የማይወለድበት’ ያለው ደራሲ ማን ነበር?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ያዝለት?›› ብሎ ወያላው ተሳፋሪ ያስገባል። ‹‹ከዚህ ወዲያ ቢቀርብህ ምን እንዳትሆን ነው?›› ትለዋለች አንዷ። ‹‹የተገኘውን መጠቀም ነው። እናንተ ውላችሁ ግቡ። የእኛ ገንዘብ እናንተ ናችሁ። በባከነ ሰዓትም ቢሆን እናንተን መሰብሰብ የእኛ ፈንታ ነው፤›› ይላታል። ይኼን ሲባባሉ አዲሱ ተሳፋሪ የሚያውቀውን ሌላ ተሳፋሪ ከወደ መጨረሻ ወንበር አይቶትኛ ይጯጯሁ ጀመር። ‹‹አንተ አለህ በአገር?›› ይለዋል አዲሱ። ‹‹የት አባቴ እሄዳለሁ? ሂድስ ብባል ማን ይለቀኛል? ይህች ምድርና ይኼ አፈር እኮ እንዲህ እንደ ዋዛ አይላቀቁህም፤›› ይለዋል። ‹‹እኔ ደግሞ አሜሪካ ገባ ሲባል ሰምቼ ደስ ብሎኝ ብታይ። እንዲያው የምትወደው መድኃኔዓለም ደረሰልህ ብዬ ተወኝ። እና እዚህ ሆነህ ነው ስልክ የማትደውለው?›› ሲለው፣ ‹‹አይ ለጨዋታ ብዬ እንጂ ለአዲስ ዓመት መጥቼ ነው አልነበርኩም፤›› አለው። ‹‹ኧረ ባክህ?›› ጠየቀ ያኛው። ‹‹እውነት፤›› ሲለው፣ ‹‹መቼ መጣህ?›› ቋምጦ በድጋሚ ጠየቀ። ‹‹ገና ሳምንቴ…›› ሲለው፣ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት እንባባላ…›› ብሎ ‹‹ወራጅ! ወራጅ!›› ካለ በኋላ ታክሲዋን አስቁሞ ወዳጁን ጎትቶ ወረደ።
ተሳፋሪዎች በግርምት እየተያዩ ይስቃሉ። ‹‹እኔ ምለው›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹2011 ሳይነግሩን ገባ እንዴ? ገና የገና ዛፍ ሳይፈርስ ፆሙን ሳንፈታ የምን አዲስ ዓመት ነው የሚያወራው ሰውዬው?›› ስትል፣ ‹‹የአውሮፓውያኑ 2018 ነው። የእኛን አይደለም…›› ትላታለች ከጎኗ ሦስተኛ የተደረበች። ‹‹ታዲያ የእኛን ካልሆነ ምን ወስዶን ነው ያደረሰን? እንኳን አደረሰህ አደረሰሽ የሚባለው እኮ የወሰደሽና ያመጣሽ መንገድ ሲኖር ነው፡፡ እንዲሁ በአየር ላይ መድረስ አለ እንዴ?›› ብላ ወይዘሮዋ ስትኮሳተር፣ ‹‹ዘመኑ የግሎባላይዜሽ ነው። የተገኘውን እያከበሩ ሳይከበሩ የመኖር አባዜ ስለያዘን ምንም ማድረግ አይቻልም። አሁን እስኪ አገር እንደ ቆዳ ተወጥሮ ስንት የሚያሰባስበን የሚያነጋግረን የጋራ ጉዳይ ባለብን ጊዜ በፈረንጅ አዲስ ዓመት ማበድ አለብን? ሰበብ ተገኝቶ በእሑድ ምድር አዲስ አበባ በአልኮል ታጠበች አሉ። ይታያችሁ እስኪ። የእኛ ጨልሞ የሌላውን ማብራት ምናችን ነው? የት ላይ ነው ኃላፊነት? የት ላይ ነው አገርን መውደድ? አገር ለመወደድ ቢራና አልኮል መንቆርቆር አለበት ማለት ነው?›› ሲለን ከመጨረሻ ወንበር ላይ አንድ ልጅ እግር ዕድሜና ቋንቋው ገርሞን ተፋጠጥን። ወያላው ወዲያው ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ተንጋግተን ወርደን ተበታተንን። ‹‹የዘንድሮ ነገርን ከማክረር ማላላት ሳይሻል አይቀርም፡፡ ወጣ ገባ እያሉ በመመላለስ ማለት ነው…›› እያሉ አዛውንቱ ሲያዘግሙ ሰማናቸው፡፡ ይኼንን የሰማ አንዱ ጎረምሳ በፉጨት ‹‹በምን አወቅሽበት በመመላለሱ…?›› የሚለውን ዜማ ሲለቀው ፍጥነታችን ጨመረ፡፡ መልካም ጉዞ!