Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአራት ቢሊዮን ዶላሩ የባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክት ግንባታ የተጀመረው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የጠየቀው ፕሮጀክቱ፣ በሦስት የቻይና ተቋራጮች የተገነባ ነው፡፡ ለግንባታ ከወጣው ገንዘብ ውስጥ 70 በመቶው   ከቻይናው የወጪና ገቢ ንግድ ባንክ (ኤግዚም ባንክ) በተገኘ ብድር የተሸፈነ ሲሆን፣ ቀሪው 30 በመቶ በኢትዮጵያና በጂቡቲ መንግሥታት መሸፈኑ ታውቋል፡፡

ከ760 ኪሎ ሜትር በላይ ሐዲድ (ስታንዳርድ ጌጅ) የተዘረጋለት የባቡሩ መንገድ ግንባታው ከአንድ ዓመት በፊት መጠናቀቁ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ዓምና በመስከረም ወር በይፋ መመረቁ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሳይጀምር ከአንድ ዓመት በላይ ቆይቶ፣ ሰኞ ታኅሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የአገልግሎቱ ታሪፍ ይፋ ተደርጓል፡፡  

ለቡ አካባቢ በሚገኘው መነሻ ጣቢያ በተሰናዳ ሥነ ሥርዓት እንደተገለጸው፣ ወደተወሰኑ ከተሞች ለሚደረጉ ጉዞዎች የወጣው የጉዞ ታሪፍም ይፋ ተደርጓል፡፡ ሌሎች 19 የባቡር ጣቢያዎችም ከሰበታ ጀምሮ እስከ ነጋድ ከተማ ድረስ ወደፊት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተጠቅሷል፡፡

የባቡሩ ታሪፍ

የባቡሩን የትራንስፖርት ኦፕሬሽን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር የተባለው ኩባንያ ሲሆን፣ ለአገልግሎቱ በወጣው ተመን መሠረት ከአዲስ አበባ መነሻውን ለቡ ባቡር ጣቢያ አድርጎ 99 ኪሎ ሜትር ወደሚሸፍነው አዳማ ከተማ በወንበር የሚጓዙ መንገደኞች 68 ብር ያስከፍላል፡፡ ወደ ድሬዳዋ በወንበር የሚጓዙም 308 ብር እንዲከፍሉ ተተምኗል፡፡ 665 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደ ምትገኘው ኤልሳቤህ ከተማ በወንበር ለሚጓዙ ተሳፋሪዎች የወጣው ተመን 459 ብር ነው፡፡

ጂቡቲ ጠረፍ አካባቢ ወደሚገኘው ነጋድ ባቡር ጣቢያ ድረስ በወንበር ለመጓዝ የሚከፈለው ገንዘብ 503 ብር ሆኗል፡፡ ነጋድ ከተማ ከለቡ 729 ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡ ከወንበር ባሻገር መኝታ ይዘው መጓዝ የሚፈልጉም፣ ከለቡ ተነስተው አዳማ ድረስ እንደየመኝታው ደረጃ ከ91 ብር ጀምሮ እስከ 181 ብር ይከፍላሉ፡፡

ወደ ድሬዳዋ መኝታ ይዞ ለመጓዝ የሚጠየቀው ከ410 እስከ 821 ብር ነው፡፡ በመኝታ እስከ ነጋድ ጣቢያ ለመጓዝ የወጣው ታሪፍ ከ671 እስከ 1,341 ብር እንደሆነ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያሰራጨው መረጃ ያመለክታል፡፡ የወጣው ተመን አገልግሎቱ የሚጀመርባቸው አምስት ከተሞችን መነሻ ያደረገ ሲሆን፣ ወደ ቀሪዎቹ ቦታዎች የተተመነው ዋጋ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ተመኑ እስከ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሚጓጓዙ መንገደኞች ቅናሽ እንደተደረገበት፣ ቅናሹም እስከ 50 በመቶ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡ መደበኛው አገልግሎት የሚጀመረውም በመጪው ሳምንት፣ ከማክሰኞ፣ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑም ታውቋል፡፡ 

ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለሚዘልቀው የባቡር ትራንስፖርት፣ ተጨማሪ የመጓጓዣ አማራጭ ስለመፈጥሩም ይነገራል፡፡ ለዓመታት ተቋርጦ የቆየው የመንገደኞችና የጭነት የባቡር ትራንስፖርት፣ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ለሚደረግ የደርሶ መልስ ጉዞ በርካታ ተሳፋሪዎች እንደሚያገኝ ታምኖበታል፡፡

ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ድረስ በወንበር ለሚጓዙ የተተመነው 308 ብር ሲሆን፣ ከሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች ክፍያ አንፃር ቅናሽ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ልዩ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት ድርጅቶች አሁን ባለው ታሪፍ መሠረት፣ ከባቡሩ ጋር ተቀራራቢ ገንዘብ ያስከፍላሉ ተብሏል፡፡ ለባቡር ጭነት አገልግሎት በኪሎ ሜትር በአንድ ቶን የሚከፈለው አማካይ ዋጋ 1.173 ብር ተደርጓል፡፡

የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስተዳደር የንግድ ድርጅት ማቋቋም ያስፈልግ ስለነበር፣ በሁለቱ መንግሥታት በባለቤትነት የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል፡፡

የኩባንያውን 75 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲይዝ፣ 25 በመቶው ድርሻ የጂቡቲ መንግሥት ሆኖ ኩባንያው ተመሥርቷል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ እንደገለጹት፣ ኩባንያው በመነሻ ካፒታል የተቋቋመው በ500 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በሁለቱ መንግሥታት ስምምነት መሠረት ኩባንያው  በኢትዮጵያ ሕግ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲሠራና ዋና መሥሪያ ቤቱም በአዲስ አበባ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ የኢትዮጵያና የጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን በጥቅል የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በመንግሥት የልማት ድርጅትነት ይተዳደራል፡፡ ኩባንያውን የሚመራ ቦርድ የተሰየመለት ሲሆን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል፡፡ የኩባንያው የመጀመርያ ሥራ አስኪያጅም አቶ ጥላሁን ሳርካ ናቸው፡፡ አቶ ጥላሁን ላለፉት አሥር ዓመታት የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝን በሥራ አስፈጻሚነት መምራታቸውና የናዝሬት ትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሥራ አስፈጻሚ እንደነበሩ የሥራ ልምዳቸው ይናገራል፡፡ የኢትዮ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ኩባንያ እንዲመሩ ከመሾማቸው በፊት በኮርፖሬሽኑ የባቡር ትራንስፖርት ኦፕሬሽንና ጥገና ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡      

ባቡሩ ለምን ዘገየ?  

ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መዘግየቱ የበርካቶዎች ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሳይጀመር የቆየው መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ በመጨረሻ ተሳክቶለት ወደ ሥራ መግባቱ የተገለጸው አንድ ዓመት ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ መሆኑ ለምን? ለሚለው ጥያቄ የኮርፖሬሽኑና የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ አገልግሎቱን አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ ስለተፈለገ የሚል ነው፡፡ ‹‹የአገልግሎቱን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ሲባል ጊዜ ወስዷ፤›› ይላሉ፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ግርማ ዓመንቴ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፣  ባቡሩ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ በመሆኑ አስተማማኝ አገልግሎት መስጠቱን ማረጋገጥ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡

የምድር ባቡር አገልግሎትን የሚያስተዳድረው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ‹‹በትራንስፖርት ዘርፍ ከአውሮፕላን ቀጥሎ ወደ ሥራ ሲገባ ከፍተኛ ጥንቃቄና የተለያዩ የቴክኒክና የብቃት ምዘናዎችን ማለፍ  ግዴታ በመሆኑ፣ እያንዳንዱን ነገር ፈትሾና አረጋግጦ፣ የማረጋገጫ ሰርቲፊኬት አግኝቶ ወደ ሥራ መግባት ግድ በመሆኑ ጊዜ ወስዷል፤›› ብለዋል፡፡ ማረጋገጫው በገለልተኛ አካል መካሔድ ስለሚገባውም፣ ይህንን ለማሟላት ሲባል የሙከራ ጊዜው ረጅም ጊዜ መፍጀቱ  በበጎ ጎኑ ሊታይ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡

አገልግሎቱ የዘገየበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት  አቶ ደረጀ እንደሚጠቅሱት፣ ሙከራው ጥንቃቄ ይጠይቅ ስለነበር፣ አገልግሎቱም ደኅንነቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ የብቃት ማረጋገጫ መገኘት ስለነበረበት ሊጀመር ከታሰበው ጊዜ ዘግይቷል፡፡ በእያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ላይ የብቃት ማረጋገጫ በማግኘት  አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችል ማረጋገጫ የሚሰጡ ተቋማትን ማግኘትም ሌላው ጉዳይ ነበር ተብሏል፡፡ በመሆኑም ሙከራዎችን ሲያደርግ የቆየውና ‹‹ቻይና አሶሲዬሽን ኦፍ ሬል ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን›› የተባለው ተቋም በአምስት መመዘኛዎች የብቃት ማረጋገጫ የሰጠው ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በመሆኑ፣ ማረጋገጫውን ለማግኘት ጊዜ እንደወሰደ አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡

በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለው ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስም ከማረጋገጫዎቹ አንዱ ነበር ያሉት አቶ ደረጀ፣ የባቡር ትራንስፖርቱን ለመጀመር የሚያስችሉ፣ የአስተዳደር ስምምነቱ ባቀረበው መሠረት ስለመሥራቱም አስተማማኝ ምላሽ መሰጠቱ ከተረጋገጠ በኋላ ግን ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል፡፡  

የፕሮጀክቱ ይዘት

በአፍሪካ ረጅሙ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ የባቡር መስመር ስለመሆኑ የገለጹት፣ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ባቡሩ ከ3,500 ቶን በላይ የመሸከም አቅም እንዳለው የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ በሻህ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ መሠረት፣ ባቡሩ በአንድ ጊዜ የሚያንቀሳቀሰው የክብደት መጠን ከ80 እስከ 100 የሚደርሱ የጭነት መኪኖች ከሚያጓጉዙት የጭነት መጠን ጋር ይስተካከላል፡፡ ከመንገደኞች አኳያም በአንድ ጊዜ ከ1,000 እስከ 1,500 ሰዎችን እንደሚያጓጉዝ ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን ለ30 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረው ባቡሩ፣ ወደፊትም ለአሥር ሺዎች ሥራ እንደሚያስገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡ ከ70 ሚሊዮን ሜትር ኪውብ በላይ የአፈር ቁፋሮና ቆረጣ የተካሄደበት፣ 26 ኪሎ ሜትር በላይ ድልድዮች የተገነቡለት፣ 1,100 ጎታችና ተጎታች ፉርጎዎች ያሉት ትልቅ የትራንስፖርት ፕሮጀክት ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴና በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር ሚስተር ሞሐመድ ኢድሪስ ፋራህም ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጥምረት ኢንቨስት ካደረጉባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚጠቀስ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ በርካታ ፈተናዎች መታለፋቸውን የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ሳይጠቅሱ አላላፉም፡፡ ለፕሮጀክት ገንዘብ ከማግኘት ጀምሮ ያገጠሙ ችግሮችን ጠቅሰዋል፡፡ የወሰን ማስከበር፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ኮንትራት የማስተዳደርና መሰል ፈተናዎች ማጋጠማቸውን አስታውሰዋል፡፡   

ባቡሩ ምን ለውጥ ያመጣል?

የምድር ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር፣ የወጪና ገቢ ምርቶችን በቀላሉ በማጓጓዝ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ችግሮችን ማቃለሉ በተስፋ የሚጠበቅ ለውጥ ነው፡፡ በትንሹ 80 ተሽከርካሪዎች የሚያነሱን ዕቃ ባቡሩ በአንዴ ለማንሳት ያስችላል፡፡ ጊዜ መቆጠቡ ሌላኛው ለውጥ ነው፡፡ ከጂቡቲ በአሥር ሰዓት ውስጥ የሚፈለገውን ሸቀጥ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ ማድረስ ያስችላል፡፡

የኢትዮ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖት የመንገደኞች የባቡር ጉዞ ዋጋ ተመን

የባቡር ጣቢያ መድረሻ

ርቀት በኪ.ሜ

በወንበር ለሚጓዙ

ባለመኝታ

ባለመኝታ ልዩ ክፍል

ከላይ

ከመሀል

በታች

ከላይ

በታች

ለቡ

0.00

ብር

ብር

ብር

ብር

ብር

ብር

አዳማ

99

68

91

125

137

171

182

ድሬዳዋ

446

308

410

564

615

769

821

አልሳቤህ

665

459

612

841

918

1147

1224

ነጋድ

729

503

671

922

1006

1258

1341

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች