Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ኤርፖርቶች ድርጅት 1.3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  –  ሰባት ኤርፖርቶች እየገነባ ነው

  የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በተጠናቀቀው የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት 1.3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ድርጅቱ የሰበሰበው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ሲነፃፀር 25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ የሒሳብ ሥራው ያልተጠናቀቀ ቢሆንም የኦፕሬሽን ወጪዎችና የታክስ ክፍያዎች ተቀንሰው ወደ 500 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የተጣራ ትርፍ እንደሚጠብቅ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ገቢውን የሚያገኘው ኤሮኖቲካልና ኤሮኖቲካል ካልሆኑ አገልግሎቶች ሲሆን፣ አብዛኛው ገቢ የሚሰበስበው ከኤሮኖቲካል አገልግሎቶች ነው፡፡ የኤሮኖቲካል አገልግሎት የሚባሉት ለአየር መንገዶች የሚሰጡ መደበኛ የኤርፖርት አገልግሎቶች ሲሆን፣ ኤሮኖቲካል ያልሆኑ የሚባሉት ከኤርፖርት ንግድ ድርጅቶች የሚገኙ ገቢዎች ናቸው፡፡

  በሌሎች አገሮች በተለይ በሠለጠኑት አገሮች ኤርፖርቶች ከፍተኛውን ገቢ የሚሰበስቡት ኤሮኖቲካል ካልሆኑ አገልግሎቶች በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ገቢውን ለማሳደግ የሚያስችለውን ጥናት ዓለም አቀፋዊ አማካሪ ድርጅት በመቅጠር ማስጠናቱን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

  በክልል የሚገነቡ ኤርፖርቶች ትርፍን ማዕከል አድርገው እንዳልሆነና የአየር ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት ካስቀመጠው አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፣ የኤርፖርቶችን ገቢ በማሳደግ ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  ‹‹የመንግሥት የልማት ድርጅት እንደመሆናችን የገቢና ትርፍ ጉዳይ ያሳስበናል፡፡ ይሁን እንጂ ፍትሐዊ የሆነ የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነት መፍጠር መንግሥት የሰጠን ኃላፊነት አለ፡፡ ትርፋማ ኤርፖርቶችን መፍጠርና የአየር ትራንስፖርትን በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ማድረግ ሁለቱን አጣምረን የምንሠራው ሥራ ነው፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ አንዳንድ የክልል ኤርፖርቶች ወጪያቸውን መሸፈን (መንግሥት የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት ሳይጨምር) መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ኤርፖርቶች ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ቱሪዝም መስፋፋት ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው ጥቅማቸው መታየት ያለበት በገንዘብ በሚያስገቡት ገቢ ብቻ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

  በቅርቡ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሐዋሳ ኤርፖርት ለአዲስ አበባ ካለው ቅርበት አንፃር አስፈላጊነቱ ላይ አንዳንድ ወገኖች ጥያቄ አንስተው እንደነበረ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሦስት ቀን የበረራ አገልግሎት ጀምሮ እንደነበር በአሁኑ ወቅት ግን ባለው ከፍተኛ ፍላጐት ምክንያት ሳምንቱን በሙሉ የበረራ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን፣ በረራዎቹም ሙሉ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በቀን እስከ አሥር የሚደርሱ በረራዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ማናችንም ከጠበቅነው በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በ2017 ዓ.ም. በአፍሪካ ግንባር ቀደም የኤርፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ በክልሎች ሰባት ኤርፖርቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የሽሬ፣ ሰመራ፣ ሮቤ፣ ጂንካና ሐዋሳ ኤርፖርቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ የነቀምትና የደምቢዶሎ ኤርፖርቶች ግንባታ በቅርቡ ተጀምሯል፡፡ በላሊበላ ኤርፖርት የማሻሻያ ሥራና በባህር ዳር ኤርፖርት የማስፋፊያ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  በማኅበራዊ ድረ ገጾች ብዙ ትችት ያስነሳው የደምቢዶሎ ኤርፖርት ግንባታ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የደምቢዶሎ ኤርፖርት ግንባታ ሁለት ምዕራፎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ቀደም ሲል ደምቢዶሎ በኤርስትሪፕ ደረጃ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲያገኝ የቆየ ቦታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአነስተኛ አውሮፕላኖች የሚሰጠው አገልግሎት ሲቋረጥ ወይም የዲኤች-6 (DH-6) አውሮፕላኖች ከገበያ ሲወጡ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከተቋረጡባቸው ክልሎች አንዱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ለረዥም ጊዜ የተቋረጠው አገልግሎት እንዲጀመር ጥያቄ ሲያቀርብ በመቆየቱ፣ መንግሥት በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገባ በሰጠው ውሳኔ በሁለት ምዕራፎች እንዲገነባ ሥራው ተጀምሯል፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ የጥርጊያ የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ (Gravel Runway) ግንባታ መሆኑን፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ወደ አስፋልት ሜዳ ማሳደግና የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ግንባታ የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  የመጀመሪያው ምዕራፍ በ76 ሚሊዮን ብር ወጪ መጠናቀቁን፣ 36 ሚሊዮን ብር ከአካባቢው ለተነሱ ነዋሪዎች ካሳ መከፈሉን፣ 40 ሚሊዮን ብር ለአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ ግንባታ ወጪ መውጣቱን፣ እነዚህም በሰነድ የተረጋገጡ ክፍያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቀጣዩ ምዕራፍ የዝናቡ ወቅት እንዳለፈ በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኅብረተሰቡ ከፍተኛ ፍላጐትና ጥያቄ ስለነበረ የጥርጊያ ሜዳው እንዳለቀ የምርቃት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ ወቅቱ የዝናብ ወቅት በመሆኑ ጭቃ ሊፈጠር ችሏል፡፡ የጥርጊያ ማረፊያዎች በክረምት ወቅት ለአገልግሎት ምቹ አይደሉም፡፡ በእኛም በኩል የነበረውን የመረጃ አሰጣጥ ክፍተት በመጠቀም አንዳንዶች ጉዳዩን አጋነው በማቅረብ ለሌላ ዓላማ ተጠቅመውበታል፤›› ብለዋል፡፡

  በክልል ለሚገነቡ ኤርፖርቶች ለመንደርደሪያ ግንባታ ብቻ በአማካይ 500 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ፣ ለመንገደኛ ማስተናገጃ ሕንፃና ሌሎች አገልግሎቶች ከ500 እስከ 800 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡ በ350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በመካሄድ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክት አጠቃላይ ሥራ 25 በመቶ፣ የግንባታ ሥራው ብቻ ሲታይ 75 በመቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡ አሁን ያለው ተርሚናል ስድስት ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጐ የተገነባ ቢሆንም፣ ከታቀደው በላይ በአሁኑ ወቅት በዓመት 8.5 ሚሊዮን መንገደኞች በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡

  የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 22 ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ በቀጣይ የሚኖረውን የአየር ትራንስፖርት ፍላጐት ዕድገት ለማስተናገድና ኢትዮጵያን የአፍሪካ መግቢያና መውጫ ማድረግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ግንባታ ከአዲስ አበባ ውጪ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የቦታ መረጣ ጥናት ተካሂዶ ለመንግሥት ለመጨረሻ ውሳኔ መቅረቡን፣ ውሳኔው ከተወሰነ በኋላ የኤርፖርት ማስተር ፕላን፣ የዲዛይንና ፋይናንስ የማፈላለግ ሥራ እንደሚጀመር አቶ ቴዎድሮስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት 20 ኤርፖርቶችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ አራቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርቶች ናቸው፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ከ20 ወደ 30 የማሳደግ ውጥን የተያዘ በመሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 25 የሚሆኑት ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡ ኤርፖርቶች ሲሆኑ፣ የተቀሩት መደበኛ ያልሆኑ በረራዎችን የሚያስተናግዱ መዳረሻዎች ይሆናሉ፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች