Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለተኛውን ኤርባስ ኤ350 አውሮፕላን ተረከበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ከተረከበው የመጀመሪያው ኤርባስ ኤ350-900 XWB በተጨማሪ ሁለተኛውን አውሮፕላን፣ ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. መረከቡንና አውሮፕላኑም በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት መድረሱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት፣ የመጀመርያው አውሮፕላን ‹‹የሰሜን ተራሮች›› የሚል ሥያሜ ተሰጥቶት፣ በተለያዩ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች እንዲሁም በቅርቡ በለንደን ከተማ በረራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከአሥር ዓመት በኋላ በአፍሪካ ግንባር ቀደሙ የአፍሪካ አቪዬሽን ግሩፕ ለመሆን የተነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ የ25 ከመቶ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ለአጭር በረራዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ አውሮፕላኖችን ሲጠቀም የቆየው አየር መንገዱ፣ ለመካከለኛና ረዥም በረራዎች በአብዛኛው ቦይንግ ሠራሽ አውሮፕላኖችን ብቻ ሲጠቀም ኖሯል፡፡

የጀት አውሮፕላኖች መመረት ከጀመሩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1962 ዓ.ም. ለአፍሪካ የመጀመርያ ጄት አውሮፕላን የሆነውን ቦይንግ 720 አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ አስገብቷል፡፡ በ1984 ዓ.ም. ቦይንግ 767 አውሮፕላንን በመግዛት የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በ2012 እጅግ ዘመናዊ የሆነውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ወደ አፍሪካ በማስገባት ቀዳሚ አየር መንገድ ሲሆን፣ የድሪምላይነር አውሮፕላንን ከቦይንግ ኩባንያ በመረከብ ኢትዮጵያ ከጃፓን ቀጥላ ከዓለም ሁለተኛዋ አገር ናት፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው የሚገለገልባቸው የቦይንግ ሥሪት አውሮፕላኖች ናቸው፡፡ ቦይንግ 737፣ 757፣ 767፣ 777 እና 787 አውሮፕላኖችን በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ የ14 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ባለቤት ሲሆን፣ ስድስት ተጨማሪ ድሪምላይነሮች ገዝቶ ለመረከብ በዝግጅት ላይ ነው፡፡

ከቦይንግ አውሮፕላኖች ባሻገር ግን የኤርባስ አዲስ ምርት የሆነውን ኤ350-900 XWB ግዙፍና ዘመናዊ የመንገደኞች አውሮፕላን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲገዛ ለማግባባት የኤርባስ የማርኬቲንግ ቡድን ከፈረንሣይ ቱሉዝ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ተመላልሷል፡፡

የአውሮፓውያኑ ምልልስ ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ. በ2009 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 12 ኤርባስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡ የ12ቱ አውሮፕላኖች ጠቅላላ ዋጋ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2019 ለአየር መንገዱ ለማስረከብ ኤርባስ መስማማቱ ይታወሳል፡፡ እነዚህ አውሮፕላኖች እስኪደርሱ ሁለት ኤ350 XWB አውሮፕላኖች በወቅቱ አይኤልኤፍሲ (አሁን ስሙ ተለውጦ ኤርካፕ) ከሚባል ታዋቂ የአየርላንድ ኩባንያ የረዥም ጊዜ የኪራይ ውል ተዋውሏል፡፡

የኤርባስ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ቶም ዊሊያምስ የመጀመርያውን ኤ350 አውሮፕላን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ቱሉዝ ብላኛክ ኤርፖርት በሚገኘው በኤርባስ የማስረከቢያ ማዕከል በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ወቅት ማስረከባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኤ350 XWB 343 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ሁለት ግዙፍ ሮልስ ሮይስ ትሬንት ሞተሮች ተገጥመውለታል፡፡ አውሮፕላኑ ከሌሎች አውሮፕላኖች ሲነፃፀር አነስተኛ ነዳጅ እንደሚጠቀም፣ የበካይ ጋዝ ልቀቱ ዝቅተኛ በመሆኑም ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑን የኤርባስና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

የሰሜን ተራሮች ተብሎ የተሰየመው ኤ350 አውሮፕላን በመጀመሪያ እንደ ዱባይና ሌጐስ ባሉ አጭር በረራ መስመሮች የሚመደብ ሲሆን፣ ሁለተኛውና ሰሞኑን የመጣው ኤ350 አውሮፕላን ሁለቱ አውሮፕላኖች በአንድነት ለንደን መስመር ላይ እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል፡፡ ሌሎቹ አውሮፕላኖች ሲመጡ ወደ አሜሪካና ቻይና መዳረሻዎች እንደሚበሩ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ መሆኑን የገለጹት ሚስተር ዊሊያምስ፣ መንገደኞችን በማመላለስ ብቻ ሳይሆኝ በአውሮፕላን ጥገና፣ በአብራሪዎችና ቴክኒሽያኖች ሥልጠና ቀዳሚ አየር መንገድ እንደሆነ መስክረዋል፡፡

የኤርባስ አውሮፕላን ከመምጣቱ በፊት ለሁለት ዓመት ያህል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኤርባስ ባለሙያዎች በጋራ በርካታ ጥናቶችና ሥልጠናዎች አካሂደዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የፓይለቶችና ቴክኒሽያኖች ሥልጠና ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡

16 አብራሪዎች (ካፒቴንና ረዳት አብራሪዎች) ለሁለት ወራት ያህል በቱሉዝ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አባት ተደርገው የሚታሰቡት ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በ1920ዎቹ የመጀመሪያውን አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት አውሮፕላን ፈረንሣይ ሠራሽ የሆነውን ፓቴዝ አውሮፕላን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊውን ኤ350 አውሮፕላን ከፈረንሣይ ወደ አፍሪካ በቀዳሚነት አስገብቷል፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች