Tuesday, April 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገርን ከጥፋት መጠበቅ የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነው!

አገርን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶችና ከሚቃጡ አደጋዎች መጠበቅ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ለአገር ነፃነት፣ ሰላምና ብልፅግና መመኘት፣ ምኞትንም ወደ ተግባር መለወጥ የሚቻለው ዜጎች ለአገራቸው የሚኖራቸው አስተዋጽኦ በተገቢው መጠን ሲገኝ ነው፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸውና አስፈላጊውን አስተዋጽኦ በምልዓት እንዲያበረክቱ ደግሞ፣ ከምንም ነገር በላይ ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ፣ የተለያዩ አቋሞች ያሉዋቸው የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነትና በኃላፊነት ሲንቀሳቀሱና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ ከስሜት የፀዱና ምክንያታዊ ሲሆኑ፣ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ዕድሉ ይኖራል፡፡ እያንዣበበ ካለው የአደጋ ሥጋት መውጣትም ይቻላል፡፡

በዚህ ዘመን ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው ትልቁ የአገር ጉዳይ ተረስቶ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን ብቻ የሚደረገው ኃላፊነት የጎደለው አጓጉል ድርጊት ነው፡፡ መነጋገርንና መደማመጥን እርም ያለውና ምክንያታዊነት የጎደለው ሽኩቻ ለአገር ህልውና የሥጋት አደጋ ደቅኗል፡፡ ዴሞክራሲ ከሌለ ሰላም የለም፡፡ ሰብዓዊ መብት ካልተከበረ መረጋጋት አይታሰብም፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ከሌለ ጉልበተኞች ይበዙና ለዕልቂት የሚዳርግ ቀውስ ይከተላል፡፡ በዚህ ላይ ብሔርን፣ ማንነትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ ሃይማኖትንና መሰል ልዩነቶችን በመንተራስ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የጥላቻ ንግግሮች ይሠራጫሉ፡፡ ጥላቻ ሌላ ጥላቻ እየወለደ ለአገርና ለሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸው የጥፋት ድግሶች ይፈበረካሉ፡፡ በዚህ መሀል ፈጽሞ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመቆጣጠር አገር የሚበትኑ ፕሮፓጋንዳዎችን ይነዛሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጊዜ ነው ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች የሚፈለጉት፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በቀጥታ ባለቤት የሌላቸው በርካታ የተቃውሞ ሠልፎች ተካሂደዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን የተቃውሞ ሠልፎች የሚመራቸው ሁነኛ አካል በመጥፋቱ የጥያቄ አቀራረቦቹ ገጽታቸው እየተለወጠ ለዜጎች ሕይወት ሕልፈት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በጥያቄዎቹ አቀራረብ ስሜታዊነትና በምላሽ አሰጣጡ ክብደት ሳቢያ ከዜጎች ጉዳት በተጨማሪ ለአገር ህልውና ጠንቅ የሆኑ ሥጋቶች ተፈጥረዋል፡፡ የዜጎች ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ቀርበው መፈታት ሲገባቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚቀሰቀሱ የጥላቻ ንግግሮች እየተዋጡ፣ አንዳንዴም የጥያቄዎቹ መልዕክት በሚገባ ሳይተላለፍ ውጤቱ ትርምስና ውድመት እየሆነ ነው፡፡ ጥያቄ ባላቸው ወገኖችና ምላሽ መስጠት በሚገባው መንግሥት መካከል መኖር የሚገባው የመተማመን ድልድይ ተሰብሮ አየሩን የሞሉት በማንነት፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ላይ ያጠነጠኑ የጥላቻ ንግግሮች ናቸው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ድምፅ ጠፍቶ የአጥፊዎች ድምፅ በጉልህ እየተሰማ ነው፡፡ ለአገር ህልውና ለሕዝቡ በሰላም አብሮ መኖር ጠንቅ የሆነ የጥፋት ድምፅ፡፡

የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ወዘተ. ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚመራ የአስተሳሰብ ልዕልና ይፈጠር ዘንድ ድምፃቸው ጎልቶ ሊሰማ ይገባል፡፡ ዜጎች በመንግሥት ላይ የሚሰማቸውን ማናቸውንም ዓይነት ቅሬታዎች ሲያቀርቡ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩና የሚያቀርቡት ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ያገኝ ዘንድ፣ መንግሥት እስካሁን የመጣበትን አጓጉል መንገድ መፈተሽ አለበት፡፡ በተለይ የፖለቲካ ምኅዳሩ በጣም ከመጣበቡ የተነሳ የሕዝብ ጥያቄዎች መደራረብ የፈጠረው ችግርና አሁንም ለሚቀርቡ ጥያቄዎች እየተሰጠ ያለው  ዘገምተኛ ምላሽ፣ እንዲሁም ችግሮችን አቃልሎ ማየት ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት አገርን ችግር ላይ እንዳይጥል ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በብርቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በተለይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዜጎች አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ከማንም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡

ዘወትር እንደምንለው የሕግ የበላይነት መኖር ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ይኖራል፡፡ ቅሬታዎች ሲኖሩ የሚፈቱበት ሕጋዊ አሠራር ይሰፍናል፡፡ መልካም አስተዳደር ዕውን ይሆናል፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል፡፡ ሙስና አከርካሪው ይሰበራል፡፡ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ ለአሉባልታና ለሐሜት የሚዳርጉ እኩይ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከሽኩቻ ይልቅ መነጋገር፣ ከኩርፊያ ይልቅ መደማመጥ፣ ከጠባብ ፍላጎቶች ይልቅ የአገር የጋራ ጥቅሞች ይቀድማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የተቀደሱ ተግባራት ይረጋገጡ ዘንድ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አገርንና ሕዝብን ከሚያስመርሩ አጓጉል ድርጊቶች ውስጥ በፍጥነት ለመውጣትና በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር፣ ሁሉም ዜጎች አገራዊ ግዴታቸውን የሚወጡበት መድረክ ይመቻች፡፡

ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ከሚያኮሩ ተምሳሌታዊ ተግባሮች መካከል በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት ይዘው መዝለቃቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የመሳሰሉት ያልገደቡት ልዩነት ኢትዮጵያዊያን በፈጠሩት የሚያኮራ የትስስር እሴት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሕዝባችን በደጉም ሆነ በክፉ ጊዜ ትስስሩን አጥብቆ ዘመናትን የተሻገረው በነበረው አርቆ አስተዋይነትና ታላቅ የአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ ይህንን አኩሪ ታሪኩን በታላቁ የዓድዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል አሳይቶ ተምሳሌትነቱን በመላው ዓለም በማረጋገጥ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ፋና ወጊ መሆን ችሏል፡፡ በዚህ ዘመን ለእንዲህ ዓይነቷ ታላቅ አገር የሚመጥን አመራር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ የሚመጥኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ደማቅና አኩሪ ተጋድሎ የሚመጥን ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁንም ደግሞ ደጋግሞ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አገር ትሁን ማለት ያስፈልጋል፡፡ ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት አገር ትሁን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመላ ዜጎቿ ኩራት፣ የሰላምና መረጋጋት፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ማማ ትሆን ዘንድ ዜጎች በሙሉ በከፍተኛ ኃላፊነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

አገሪቱን ወደ ብተና፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ዕልቂትና ስደት የሚያመቻቹ አጓጉል ድርጊቶች በሁሉም ወገኖች መወገዝ አለባቸው፡፡ ሥልጣንን ለማጠባበቅም ሆነ በአቋራጭ ለማግኘት ሲባል ወደ ቀውስ የሚያንደረድሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ በተለይ ብሔርንና መሰል ልዩነቶችን እያቀነቀኑ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ለማለያየት፣ አገሪቷንም ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ወገኖች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በአገር ባለቤትነት ስሜት ተንቀሳቅሰው እሳት ለማቀጣጠል የሚፈልጉ ወገኖችን መገሰጽ አለባቸው፡፡ የሕዝብ ጥያቄም በአግባቡ ተሰምቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ዜጎች ቅሬታ ሲያቀርቡ በአግባቡ እንዲደመጡና ምላሽ እንዲያገኙ፣ ምላሽ የሚሰጠው አካልም በሕጉ መሠረት ኃላፊነቱን እንደወጣ መደረግ አለበት፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች ኃላፊነት በማይሰማቸው ወገኖች እየተጠለፉና አቅጣጫቸውን እየሳቱ ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ የጥላቻ ንግግሮች አገር መፍታት የለባቸውም፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች በእርግጠኝነት እንዲከበሩ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሁሉ ድምፃቸው ይሰማ፡፡ አገርን ከጥፋት መጠበቅ የዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነውና፡፡    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...

የአገሪቱ ባንኮች የመጭበርበር ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል ቀሲስ በላይ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ...

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...