Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሙስና ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋና ግጭቶች እንዲስፋፉ በር ይከፍታል

ሙስና ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋና ግጭቶች እንዲስፋፉ በር ይከፍታል

ቀን:

በዳዊት ወልደሱስ

ስለሙስና ብዙ ጊዜ እንሰማለን፡፡ አቶ እገሌ ወይም ወ/ሮ (ወ/ሪት) እገሊት በሙስና ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ፣ በሙስና ወንጀል ታሰሩ፣ ይህን ያህል ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው፣ ወዘተ ሲባል በሚዲያ በተደጋጋሚ አዳምጠናል፡፡ ሙስና ማለት ምን ማለት ነው?

ሙስና የግእዝ ቃል ሲሆን ‹‹ማሰነ››፣ ጠፋ ወይም ጥፋት የሚል ትርጉም አለው፡፡ ይህ የማይገባ ድርጊት መፈጸም መሆኑን ያመላክታል፡፡ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችም ለቃሉ ይስማማዋል የሚለውን ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ ለአብነትም ኦክስፎርድ የእንግሊዝኛው መዝገበ ቃላት አደራን አለመጠበቅ፣ እምነትን ማጉደል፣ በጉቦ፣ በምልጃና በአድልዎ ሀቅን፣ ውሳኔንና ፍትሕን ማዛባት በማለት ለሙስና ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ሥርዓቶችን፣ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ አሠራሮችን፣ መርሆዎችን የመጣስ ማንኛውም ተግባር ሙስና ይባላል፡፡ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ድርጅትም በበኩሉ ሙስና በመንግሥትና በሕዝብ የተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት ለግል ጥቅም ወይም ሌላን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ሲባል ያላግባብ መገልገል ነው ይላል፡፡

እያንዳንዳችንም ትርጉም እንስጠው ብንል ከግብሩ የተነሳ በይዘት ረገድ ተቀራራቢ ፍቺ ልንሰጥ እንደምንችል እገምታለሁ፡፡ በአጭሩ ሙስና ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ ሥልጣንና ኃላፊነትን በመጠቀም ሕግና ሥርዓትን በመጣስ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትና ንብረትን መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር እንዲሁም በጉቦ፣ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በሃይማኖት ትስስር ላይ በመመርኮዝ አድሏዊ በሆነ አሠራር ፍትሕን እያዛቡ የግል ጥቅምን ማካበትና ሌላውን ወገን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥቀም፣ መጉዳት የሚለው ገለጻ ሊያግባባ ይችላል፡፡

ከትርጉሙ እንመለስና የሙስና ውልደቱ ከየት ነው? በአካል ገዝፎ፣ በሰውና በአገር ላይ ጠባሳውን የሚያሳርፈውስ እንዴት ነው? ሊቃውንቱ ኪራይ ሰቢሳቢነት በአመለካከት ተወልዶ ወደ ተግባር ካደገ በኋላ ሙስና ይሆናል ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ሙስና በግብር እንዲገለጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ወሳኝነት አለው ማለት ነው፡፡ ስለኪራይ ሰብሳቢነት ለማስገንዘብ የተጻፉ ሰነዶች እንደሚነግሩንም ኪራይ ሰብሳቢነት ግላዊ ወይም የቡድን ፍላጎትን በሕገወጥ መንገድ ለማሟላት መልካም ሥነ ምግባር በሌላቸው ሰዎች የሚፈጸም ተግባር ሲሆን፣ ዋነኛው መንስዔውም ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ዝቅጠት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ለአብነትም የመስረቅና የስግብግብነት ባህሪ መኖር፣ ሳይሠሩ መክበር፣ የተደላደለና የተንደላቀቀ ሕይወት የመኖር ፍላጎት፣ ለተለያዩ ሱሶች መጋለጥ፣ ግለሰቦች ከሌሎች ጋር ራሳቸውን ሲያወዳድሩ የሚሰማቸው የበታችነት ስሜት፣ ከሕግ በላይ የመሆን ስሜት መኖርና ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው እንደማይችል መገመት፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው እየሆነ መሄድ ወይም የግድ የለሽነት ባህሪ እያዳበሩ መሄድ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ስለሆነም ሙስና የተፈጥሮ ሰብዕናን ለሌላ ባዕድ ነገር ራስን በማስገዛት ኢ-ሥነ ምግባር ለሆነው ድርጊት ባሪያ መሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ሀብታም ወይም ደሃ መሆን፣ ባለሥልጣን ወይም ተራ ሠራተኛ መሆን፣ ፖለቲከኛ ወይም ሃይማኖተኛ መሆን፣ ትልቅ ወይም ትንሽ መሆንን አይመለከትም፡፡ ማንም ሰው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ካለው ያ አመለካከት ወደ ተግባር ያመራዋል፡፡ ያ ደግሞ ሙስና ይሆናል፡፡ በአገር ደረጃም የበለፀጉ፣ ያልበለፀጉ በሚል የሒሳብ ቀመር የሚሠራለት አይደለም፡፡ በአመለካከት ተወልዶ በተግባር የሚገለጥ ነውና!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽንም (The United Convention Against Corruption) ሙስና በሁሉም አገሮች (በሃብታሙም በደሃውም፤ በትልቁም በትንሹም…) የሚገኝ ክፉ ክስተት (Evil henomena) ነው ይለዋል፡፡ ክስተቱም ዘርፍን ሳይለይ የሚገለጥ ነው፡፡ በፖለቲካ ዓለም ወይም በሃይማኖትም ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ የሥነ ምግባር ዝቅጠት በተከሰተበት ሙስና ይኖራል፡፡

ለዚህ ነው አገራችንም ምንም እንኳ በዕድገት ጎዳና ያለች ብትሆንም ይህን ክፉ ጠላት ለመዋጋት በሜክሲኮ ከተማ የዓለም አገሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽንን እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 9 ቀን 2003 ሲፈራረሙ ከአፅዳቂ አገሮች አንዷ የሆነችው፡፡ ሙስናን አምርራ ለመታገል!

በአገራችን በየዘመናቱ በሚነሱ መንግሥታት ሙስና እንደ አረም በአገሪቱ እየበቀለ በዕድገት ላይ ማነቆ በመሆን የምንፈልጋትን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማምጣት፣ እንዲሁም ወደ ቀደመ ክብሯ እንዳትመለስ እንቅፋት በመሆን ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ አሁንም ውስጥ ለውስጥ እንደ አሜባ እየተከፋፈለ ቀጥሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እኔ ብቻ በአቋራጭ ልበልፀግ የሚለውን ክፉ አስተሳሰብ ተሸክመው በሚጓዙ ግለሰቦች ያለማቋረጥ ክፋቱ እየጨመረ በመሄዱ ነው፡፡

በየጊዜው አስፈላጊው ዕርምጃ በጥፋተኞች ላይ ቢወሰድም ችግሩን ለማጥራት ግን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በየጊዜው በአገር ሀብት ላይ የሚካሄደው ዘረፋንም ለመቆጣጠር ፈታኝ ሆኗል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የስርቆት ባህሪው እንደ እስስት መልኩን እየቀያየረ መሄዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው የሰውን አመለካከት በቀላሉ ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ሙስና በተግባር እየተወለደ የሕዝብና የአገር ሀብት እየተዘረፈ የሚገኘው፡፡

በማደግ ላይ በምትገኝ አገር ደግሞ ይህ ክፉ ጠላት ብርሃኗን ሊያጨልም እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ በዓለም አገሮች ምስክርነትን ያገኘው የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣን በመሆኑ በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ እንደሚያስችለን አመላካች ነው፡፡ ይህን ዕድገት የሚያስቀጥሉ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ ዕድገት በሕዝቦች መካከል ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለማምጣትና ድህነትን እስከወዲያኛው ለመፋታት መንገዱ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ብርሃኗን ሊያጨልሙ፣ ዕድገቷን ሊገቱና ሰላሟን ሊነሱ ፊት ለፊት ተጋርጠዋል፡፡

ለዚህ ነው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አመለካከትና ተግባር በአገራችን እየተመዘገበ ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ናቸው ተብለው ከተለዩት ዋነኛ ችግሮች ውስጥ አንደኛው የሆነው ነው፡፡ ችግሩ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን፣ እየተገነባ ላለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ጠንቅ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ተገምግሞ ተረጋግጧል፡፡ ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ለመናድና በልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚና አስተሳሰበ ለመተካት ደግሞ የሁሉንም ሰው ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ካልሆነ ሕዝብ በመንግሥትና በሕግ የበላይነት ላይ አመኔታ እንዲያጣ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረውና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ ልማት እንዲቀጭጭ፣ የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲገታና ድህነት እንዲስፋፋም መንገድ ይከፍታል፡፡

አሁን ይህ የተዛባና ጤናማ ያልሆነ አመለካከት ሊስተካከል ይገባል፡፡ ስለኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ብዙ ከማውራት በተግባር ማስተካከል ይገባል፡፡ ማንም አካል በሚያከናውነው እኩይ ተግባርም አስፈላጊውን ሕጋዊ ቅጣት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ችግሩን ለመከላከልም ጉዳዩን ለመንግሥት ብቻ መስጠት ተገቢ አይሆንም፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በጉዳዩ ላይ የራሱን ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡ አገር የሕዝብና የመንግሥት ናትና፡፡

ከድህነት መውጣት የማይፈልግ አይኖርም፡፡ ከድህነት በመውጣት የበለፀገች አገር መገንባት የሚቻለው ደግሞ ጠላትን በተባበረ ክንድ መቋቋም ሲቻል ነው፡፡ ‹‹ድር ቢያብር …›› አይደል ተረቱ፡፡ ድህነትን አምርሮ የሚጠላ ሕዝብ እንዲኖር ደግሞ አመለካከት ላይ በስፋት መሠራት እንዳለበት ሁሉንም የሚያግባባ ሐሳብ ነው፡፡ አመለካከት ከተቀየረ ቀሪው ነገር ሁሉ በሚፈለገው ደረጃና ፍጥነት ይሄዳል፡፡ ሙስናም ከመወለዱ በፊት ይመክናል፡፡ ስለሆነም በዕድገት ላይ ያለው ሥጋት ይቀንሳል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ካልተቀረፈ ሙስና በየጊዜው በዝቶ መወለዱ አይቀርም፡፡ ድርጊቶች የሚገለጡት ‹‹ላድረገው?›› በሚል የሐሳብ መነሻነት ነውና፡፡ ስለሆነም አገራችን እያደረገችው ላለው የህዳሴ ጉዞ መሰናክልነቱ የበረታ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ፣ የጥቅም ግጭቶች እንዲስፋፉ፣ አገራዊ ስሜት እንዳይኖር፣ አንዱ በሌላው ላይ ግፍ እንዲፈጽም፣ ሰብዓዊነት እንዳይኖርና አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ያደርጋል፡፡

‹‹ችግርን ለይቶ ማወቅ የጉዳዩን ግማሽ በመቶ መፈጸም›› እንደሆነ ይነገራል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የአገራችን ሥርዓት አደጋ መሆኑ ተለይቷል፡፡ ቀሪው በችግሩ ላይ በኅብረት መዝመት ነው፡፡ ያኔ ሥጋቱ ይቀንሳል፡፡ የምናልማትን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ እናወርሳለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...