Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግን አክብረው ከሠሩ የሚዘጉበት ምክንያት አይኖርም

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግን አክብረው ከሠሩ የሚዘጉበት ምክንያት አይኖርም

ቀን:

በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ

በአገራችን ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የበጎ አድራጎት ሥራን በአግባቡ የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም፡፡ አዋጅ 621/2001 የበጎ አድራጎት ድርጀቶችና ማኅበራት በአገሪቱ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለመደገፍና ለማሳለጥ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 ለዜጎች የሰጠውን የመደራጀት መብት ተግባራዊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን ዜጎች ተደራጅተው በአገራቸው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ ያለምንም ገደብ እንዲሳተፉ ግልጽ በሆነ መልኩ ደንግጓል፡፡

በአዋጅ 621/2001 መሠረት የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲስፋፉና ተልዕኳቸውን በሕግ መሠረት እንዲወጡ ብሎም ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር እንዲጎለብት ዓላማ አንግቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ 3,115 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተመዝግበው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 416 የውጭ አገር በጎ አድራጎት ድርጀቶች፣ 2,646 በኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጁ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲሁም 53 ኅብረቶች ናቸው፡፡

ኤጀንሲው እነዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ 621/2001 በሚፈቅደው መሠረት በሕዝብ ስም ያገኙትን ሀብትና ንብረት በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ በማዋል የተቋቋሙለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርጉ በሚያግዝ መልኩ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በ2008 በጀት  ዓመት ኤጀንሲው የ2756 በጎ አድራጎት ድርጀቶችና ማኅበራት ፋይል በመመርመር ዓመታዊ ዕቅድ፣ ሪፖርትና የፕሮጀክት ስምምነት ገምግሟል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ 824 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ላይ የመስክ ክትትል አድርጓል፡፡ በተደረገው ክትትል ሕግን የተላለፉ 206 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚደርስ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ከታዩባቸው ችግሮች መካከል ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ መንቀሳቀስ፣ ያለኤጀንሲው ፈቃድ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የገቢ ምንጫቸውን አለማሳወቅ፣ ዓመታዊ የሥራና የኦዲት ሪፖርት በወቅቱ አለማቅረብ፣ የቋሚ ንብረት ዝርዝር አለማሳወቅ፣ የፕሮጀክት ስምምነት ሳይፈራረሙ መሥራት፣ አስተዳደራዊ ወጪዎችን ከዓላማ ማስፈጸሚያ ወጪዎች ጋር መቀላቀል፣ አስተዳደራዊ ወጪ ከ30 በመቶ በላይ መጠቀም፣ ልማትን ከሃይማኖት ጋር ቀላቅሎ መሥራት፣ ያለፈቃድ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ መሰማራት ለአብነት የሚጠቀሱ ግኝቶች ናቸው፡፡

በ2008 በጀት ዓመት 122 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተዘግተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 119 በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በራሳቸው ጥያቄ፣ ፈንድ በማጣትና ለሦስት ዓመታት ምንም እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው የተዘጉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ባክነር አዶፕሽን ኤንድ ማተርኒቲ ሰርቪስ፣ ግሎባል ኢንፋንቲልና ሜዲስን ዱሞንድ የተባሉ ሦስት የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በፈጸሙት የሕግ ጥሰት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ያሉባቸውን ችግሮች ባለማስተካከላቸው ተዘግተዋል፡፡ አብዛኞቹ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከጅምሩ አቅም ፈጥረው ወደ ሥራ ያልገቡ በመሆናቸው መዘጋታቸው በአገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም፡፡ የገንዘብ እጥረት ያጋጠማቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጁ የፈቀደላቸውን የተለያዩ ገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ዓላማቸውን ለማስቀጠል ምንም ጥረት አላደረጉም፡፡ በሌላ በኩል በ2008 በጀት ዓመት መሥፈርቱን ያሟሉ 187 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተመዝግበዋል፡፡ ለ803 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፈቃድ እድሳት ተሰጥቷል፡፡

በአዋጅ 621/2001 መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ከሚያገኙት ገቢ 70 በመቶ የማያንሰውን ለዓላማ ማስፈጸሚያ (በቀጥታ ለተጠቃሚው የሚደርስ) እንዲሁም 30 በመቶ የማይበልጠውን ለአስተዳደራዊ ወጪ እንዲያውሉት ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ይህንን ሕግ ጠብቀው እየሠሩ አይደለም፡፡ ኤጀንሲው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግን ጠብቀው እንዲሠሩ የተለያዩ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ የቆየው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በዘርፉ የወጣውን ሕግ አውቀው እንዲተገብሩ መስመር የማስያዝና የማስተማር ቢሆንም፣ በተሟላ መልኩ ሕግን አክብሮ መሥራት ላይ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ሆኖም ኤጀንሲው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን መዝጋት እንደ መፍትሔ አይወስድም፡፡ ይሁን እንጂ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹና ማኅበራቱ የሚዘጉት መሥራት የሚችሉባቸው ሁሉም አማራጮች ተፈትሸው መቀጠል የማይችሉ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡

እውነታው ከላይ በዝርዝር ሆኖ እያለ አንዳንድ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የጠራ መረጃ ሳይዙ ኤጀንሲው በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እየዘጋ መሆኑን በስፋት ዘግበዋል፡፡ ለአብነት ያህልም በፍሪደም ሀውስና በዶቼ ቬሌ ሬዲዮ ጣቢያ ኤጀንሲው ከ200 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጀቶችን ያላግባብ እንደዘጋ ተደርጎ የተዘገበው መረጃ ከእውነታ የራቀ ነው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው 122 ብቻ ናቸው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግን አክብረው እስከሠሩ ድረስ እንዲዘጉ የተደረገበት ሁኔታ የለም፡፡

በተጨማሪም እነዚህ ሚዲያዎች አዋጁ 621/2001 የበጎ አድራጎት ድርጀቶችና ማኅበራት ጉዳዮች ላይ እንዳይሠሩ ገደብ አድርጓል የሚል ሐሳብ በስፋት አንፀባርቀዋል፡፡ ይህ አስተያየት ሕጉን በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ በአዋጅ 621/2001 መሠረት የገቢ ምንላቸው ከአሥር በመቶ በላይ ከአገር ውጭ የሚያገኙ በኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋሙ የነዋሪዎችና የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በዜጎች መብት ነክ ጉዳዮች ላይ መሥራት አይችሉም፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ እነዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ፈቅዷል፡፡

የገቢ ምንጫቸው 90 በመቶ ከአገር ውስጥ እንዲሁም አሥር በመቶ የማይበልጠውን ከውጭ የሚያገኙ በአገሪቱ ዜጎች የተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በልማት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በመብት ነክ ጉዳዮች ላይ መሥራት ይችላሉ፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ውስጥ የዜጎች መብትና ጥቅሞች ማስከበር ለኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ብቻ የተሰጡ ናቸው፡፡ አገር በቀል የሙያና ብዙኃን ማኅበራት የሚቋቋሙት ይህን ዓላማ ዕውን ለማድረግ ነው፡፡ የዜጎችን የዴሞክራሲ መብትና ጥቅሞችን ለማስከበር የሚሠራው ሥራ እንደ ልማቱ ትልቅ ሀብት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዜጎች ብቻ ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ አዋጁ ሁሉም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በልማት ሥራዎች ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ አዋጁ የአገርን ደኅንነትና ጥቅምን በሚያስጠብቅ መልኩ ተቃኝቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከምንም በላይ ለሰፊው ሕዝብ ጥብቅና የቆመ ሕግ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡

ምንም እንኳን ክፍተቶች ቢኖሩም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በልማቱ ዘርፍ ላበረከቱት መልካም ሥራ ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የኅብረተሰባችንን ችግር በመቅረፍ ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት በማመንጨት ክፍተት በሚታይባቸው የልማት ሥራዎች ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል የኤጀንሲው ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በ2008 በጀት ዓመት 641 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ብቻ 19,155,771,263 ብር (አሥራ ዘጠኝ ቢሊዮን አንድ መቶ ሐምሳ አምስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰባ አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስልሳ ሦስት ብር) በጀት ይዘው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በዘርፉ በሕዝብ ስም የሚመጣው ሀብትና ንብረት በግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋል ከቻለ የበጎ አድራጎት ድርጀቶችና ማኅበራት በጥቅሉ ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽኦ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ መረዳት አያዳግትም፡፡

ነገር ግን ሁሉም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግ በሚፈቅደው መልኩ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚሰበስቡትን ገንዘብ በትክክል ለሚፈለገው ዓላማ እያዋሉት ነው ወይ የሚለው ጥብቅ ክትትል የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሚሠሩ እንዳሉ ሁሉ ልማትን ሽፋን በማድረግ በአቋራጭ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በአገሪቷ ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተልዕኳቸው ስኬትማ የሚሆነው ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት አሠራር መሠረት ተንቀሳቅሰው በቀጥታ ኅብረተሰቡ ከልማት ሥራቸው ተጠቃሚ መሆን ሲችል ነው፡፡ ይህ ዕውን የሚሆነው ሕግ በአግባቡ ተግባራዊ ሲደረግ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ለአገር ካላቸው ጠቀሜታ አንፃር ተገቢው ድግፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ሕግን ተረድተው በአግባቡ እንዲሠሩ ድጋፍ ከተደረገላቸው አቅም ፈጥረው አገሪቷ ሁለተኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ በምታደርገው ርብርብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...