Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምግርታን የፈጠረው የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ

ግርታን የፈጠረው የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ

ቀን:

ዶናልድ ትራምፕ መጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡ፣ በአሜሪካ ሊተገብሩ የሚፈልጓቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሃዮ በነበራቸው መድረክ አሳውቀዋል፡፡ ሆኖም ምክረ ሐሳቦቹ ግርታን የሚፈጥሩና የአሜሪካውያንን ተቻችሎ የመኖርና እንግዳን የመቀበል ባህል የሚሸረሽሩ ናቸው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡

ቀድሞውንም አወዛጋቢ በሆኑ አጀንዳዎቻቸው ከሚታወቁት የአሜሪካ ዕጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አግላይ ያልሆነ አመለካከት ባይጠበቅም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክረ ሐሳባቸውን ሲያቀርቡ ግን ለየትና ጠንከር ያለ አጀንዳ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡

ቢቢሲ እንደ ዘገበው፣ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ ላይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢመረጡ፣ ወደ አገሪቱ በሚገቡ የውጭ ዜጎች በተለይም ከመካከለኛው ምሥራቅ በሚመጡት ላይ ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡ አዲስ የምርመራ አካሄድ በመተግበርም የእስልምና አክራሪነትን እንደሚዋጉ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የእስልምና አክራሪነት አመለካከት ሙስሊሞችን አሜሪካ ከመግባት በማገድ ወይም አመለካከታቸው ላይ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ መገደብ ባይቻልም፣ ትራምፕ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ካስቀመጡት ምክረ ሐሳብ አንዱ ወደ አሜሪካ ለመግባት የቪዛ ጥያቄ በሚያቀርቡ ዜጎች ላይ የአመለካከት ጥያቄና ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግብረ ሰዶማዊ የመሆን ነፃነትና የሃይማኖቶች መቻቻል ላይ ያላቸውን አቋም እንዲያሳውቁም ይደረጋሉ፡፡

በትራምፕ ዕቅድ መሠረት የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች ከኖሩባቸው ወይም ከሚኖሩባቸው አገሮች ወደ አሜሪካ ለመግባት ጥያቄ በሚያቀርቡ ዜጎች ላይ በሙሉ ዕገዳ የሚጥሉ ሲሆን፣ አገሮቹ እነማን እንደሆኑ ግን አልገለጹም፡፡ አይኤስን ለመዋጋት ምን ዓይነት ወታደራዊ ስትራቴጂ እንደሚከተሉም ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

እንደ ትራምፕ የውጭ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ሽብር ከተስፋፋባቸውና ዝቅተኛ የቁጥጥር ሥርዓት ካላቸው አገሮች ወደ አሜሪካ መግባት የሚፈልጉ የውጭ አገር ዜጎች፣ አሜሪካ ከመግባት ይታገዳሉ፡ አሜሪካ ሽብርን ከሚዋጉ አገሮች ጋር ጥምረት ትፈጥራለች፣ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ የቪዛ ጥያቄ የሚያቀርቡ በሙሉ የአመለካከት ምርመራ ይደረግባቸዋል፣ የጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ክፍት ሆኖ ይቀጥላል፣ የሽብር ጥቃትን የሚመረምር ፕሬዚዳንታዊ ኮሚሽን ይቋቋማል፣ እንዲሁም ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጋር ይሠራል፡፡

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሁሉም ሙስሊሞች አሜሪካ እንዳይገቡ እንደሚያግዱና ኔቶም አላስፈላጊ መሆኑን የገለጹ ቢሆንም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ሲያቀርቡ ግን በድፍን በሙስሊሞች ላይ የነበራቸውን አመለካከት የሽብር ጥቃት ከሚበዛባቸው አገሮች በሚመጡ ሙስሊሞች በሚል ምልከታቸውን በትንሹ ገርተዋል፡፡

‹‹ሽብርን ከሚልኩ›› አገሮች ለሚመጡ ዜጎች የአሜሪካ በር ዝግ ይሆናል የሚለው የትራምፕ ንግግርና ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ፣ በተፎካካሪያቸው ሒላሪ ክሊንተን ትችት ገጥሞታል፡፡ ሒላሪ ክሊንተን፣ ‹‹በራስ ወዳድነት ላይ ያጠነጠነ ምክረ ሐሳብ፤›› ሲሉት፣ ቃል አቀባያቸው ደግሞ፣ ‹‹የትራምፕ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ከቁም ነገር አይወሰድም፤›› ብለዋል፡፡

በትራምፕ አመለካከት ላይ ነቀፋ ሲሰነዝሩ የቆዩትን ዴሞክራቶቹን ሒላሪ ክሊንተንና ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ‹‹የአይኤስ ፈጣሪዎች ናቸው›› ሲሉም ኮንነዋቸዋል፡፡ በተለይ ሒላሪ ክሊንተን፣ ‹የሶሪያ ስደተኞችን የመቀበል አቅማችንን አሳድጋለሁ› ማለታቸውን፣ ‹‹ይህ አሜሪካን 400 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣታል›› በማለት እንደማይደግፉት ተናግረዋል፡፡ ‹‹አይኤስን ለመዋጋት የአመለካከትም ሆነ የአካል ብቃት የላትም፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የትራምፕ ንግግር በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ዒላማ ውስጥ አስገብቷል ሲሉ ትራምፕን የወነጀሉት ደግሞ፣ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ናቸው፡፡ ትራምፕ ‹‹ሚስ ክሊንተንና ፕሬዚዳንት ኦባማ የአይኤስ ፈጣሪዎች ናቸው›› ማለታቸው፣ ኢራቃውያን በአሜሪካውያን ላይ ያላቸውን አመለካከት ይበርዘዋል፡፡ አይኤስን ለመዋጋት በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችንም አደጋ ውስጥ ከቷል ብለዋል፡፡ ‹‹ለትራምፕ የኑክሌር ኮዱን እንዳትነግሩት፤›› ሲሉም ኃላፊነት የማይሸከሙ መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

ትራምፕ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ብዙዎቹ የብሔራዊ ደኅንነት ኤክስፐርቶች አለመደሰታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ በጡረታ የሚኙትና የሲኤንኤን ተንታኝ የሆኑት ሌተና ጄኔራል ማርክ ኧርትሊንግ፣ ‹‹የትራምፕ ንግግር ፍርኃት ውስጥ ይከተኛል፤›› ብለዋል፡፡

ትራምፕ አሁን ይዘውት ብቅ ያሉት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ዜጎች ላይ የሚደረግ የአመለካከት ወይም የርዕዮት ዓለም ምርመራ፣ አገሪቷ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ታደርገው እንደነበረው ዓይነት እንደሆነ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

ትራምፕም ቢሆኑ፣ ‹‹በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የአመለካከት ምርመራ ነበረን፡፡ አሜሪካን አሁን ከተጋረጡባት ሥጋቶች ለመከላከል የዚህ ዓይነቱን ምርመራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ጥልቅ ምርመራ (ኤክስትሪም ቬቲንግ) እንለዋለን፤›› ብለዋል፡፡

በየዓመቱ 100 ሺሕ ያህል ስደተኞች ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ አሜሪካ ይገባሉ የሚሉት ትራምፕ፣ አሜሪካ ከእነዚህ አካባቢዎች የሚቀርብ የቪዛ ጥያቄን ማስተናገድ እንደማይገባት ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ በወደፊት የውጭ ፖሊሲያቸው ላይ ያስቀመጧቸው ሐሳቦች ግር የሚያሰኙ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ አይኤስን በወታደራዊ ኃይል እንዴት ማጥፋት ይቻላል? አክራሪዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንዴት ማገድ ይቻላል? እንዲሁም የአሜሪካን እሴቶች በአዎንታዊ መንገድ የሚጋሩ የሌሎች አገር ዜጎች ከማይጋሩት እንዴት እንደሚለዩ አወዛጋቢ ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም ለደጋፊዎቻቸው እንዲህ አቅርበውታል፡፡ አንዳንድ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች የትራምፕ የውጭ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ያሠጋቸው መሆኑን ቢገልጹም፣ ምርጫው የአሜሪካውያን በተለይም በእያንዳንዷ የትራምፕ ንግግር ላይ ድጋፋቸውን ለሚገልጹት የትራምፕ ተከታዮች መሆኑ ግን ብዙዎችን ያስማማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...