Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያሸለሙ ፈጠራዎች

ያሸለሙ ፈጠራዎች

ቀን:

መብቱ አበበ ይባላል፡፡ በኮሙኒኬሽንና ኔትወርኪንግ ኢንጅነሪንግ የትምህርት ዘርፍ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀው አምና ነበር፡፡ ለጤናው ዘርፍ የሚያገለግል ኢኤምኤስ ስማርት ኤሌክትሮኒክስ ሜዲካል ሲስተም የተባለ ሶፍትዌር ሠርቷል፡፡ የሶፍትዌሩ ሚናም የጤና ተቋማት ማለትም የሆስፒታሎች፣ የክሊኒኮችና የፋርማሲዎችን አሠራር ሙሉ በመሉ በኮምፒዩተር የታገዘ ማድረግ ነው፡፡

‹‹አንድ ታካሚ ካርድ አግኝቶ መታከም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አስፈላጊውን መረጃ ነርሶች፣ ካሸሮች፣ ዶክተሮች፣ ፓቶሎጂስቶች፣ ፋርማሲስቶችና ሌሎችም በሕክምና ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የታካሚው መረጃ በኮምፒውተር በታገዘ መረጃ ተቀነባብሮ እንዲገኝ ያደርገዋል፤›› የሚለው መብቱ፣ ፕሮጀክቱን የጀመረው በ2005 ዓ.ም. እንደነበር፣ በተለያዩ የጤና ተቋማት ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑንና ጥሩ ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራል፡፡

ሶፍትዌሩን ለመሥራት አራት ዓመታት ያህል ፈጅቶበታል፡፡ አንድን ሶፍትዌር ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የሚወስደው ጊዜ ከፍተኛና አድካሚ በመሆኑ ባለሙያዎች ተባብረው ቢሠሩት እንደሚመረጥ፣ በሌላው ዓለምም የተለመደ አሠራር መሆኑን ይናገራል፡፡ በሠራው ሶፍትዌር በኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደው የአይሲቲ ፈጠራ ውድድር ላይ በመሳተፍ ከ579 ተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ በመሆን ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በተዘጋጀው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የ75,000 ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

በሁለት መርሐ ግብር ማለትም በአጠቃላይና በሴቶች ብቻ ተብሎ በተዘጋጀው ውድድር 77 ሴቶች ተካተው ነበር፡፡ በሴቶች ምድብ አንደኛ በመሆን የ75,000 ብር ተሸላሚ ለመሆን የበቁት የምልክት ቋንቋ ማስተማሪያ የሞባይል አፕሊኬሽን የሠሩት ጓደኛሞቹ እንግዳወርቅ ከበደና ትዕግስት ታደሰ ናቸው፡፡

በዕለቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘችው እንግዳወርቅ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ የተመረቀችው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የአማርኛ ምልክት ቋንቋን የሚያስተምረውን የሞባይል አፕሊኬሽን ለምን እንደሠሩት ስትናገር፣ ‹‹በአገራችን ለሚገኙ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ተብሎ እስካሁን የተሠራ የሞባይል አፕሊኬሽን የለም፡፡ እኛም እንደ ኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ተመራቂ መስማት የተሳናቸውን ለመረዳት የሠራነው ሥራ ነው፤›› ብላለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ አፕሊኬሽኑ የተለያዩ ሞጁሎች አሉት፡፡ መዝገበ ቃላት፣ ቃልና ተመሳሳይ ምሥል ያሳያል፣ ጥያቄዎችን ከምሥልና ከመረጃዎች ጋር አጣምሮ ያቀርባል፡፡ መዝገበ ቃላቱ የአማርኛ ፊደሎችን፣ ቃላትንና ቁጥሮችን ወደ ተመሳሳይ ምሥል ይቀይራቸዋል፡፡ ይህም መስማት የተሳናቸው ቃላትን በምሥል እንዲመለከቱ ያስችላቸዋል፡፡ አፕሊኬሽኑ መስማት ለተሳናቸው ብቻ የተሠራ ግን አይደለም፡፡ መስማት የተሳናቸውና መስማት የሚችሉት መግባባት እንዲችሉ በምሥልና በድምፅ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ ምሥልን ከእንቅስቃሴ ጋር የማሳየት አቅምም አለው፡፡

አፕሊኬሽኑን ለመሥራት የሚያስፈልጉ የተዘጋጁ ምስሎች አለመኖር ሥራቸውን ከባድ አድርጐት ነበር፡፡ ምሥሎችን ከማኅበራዊ ድረገጾች ላይ ለማግኘት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ማግኘት የቻሉት ምሥል ሳይሆን ቪዲዮ ብቻ ነበር፡፡ ቪዲዮውን በስልክ ላይ ጭኖ ለመጠቀም ከፍተኛ ቦታ ስለሚያስፈልግና ለአሠራር አመቺ ስለማይሆን የተሻለ አማራጭ መፈለግ ነበረባቸው፡፡ የነበራቸው ብቸኛ አማራጭም መስማት ለተሳናቸው ተብለው የተዘጋጁ መጻሕፍትን በመግዛት፣ በመጻሕፍቱ ላይ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ምልክቶች ከነምሥላቸው ለይቶ በማውጣት ምልክቶቹን ለሞባይል በሚመች መልኩ ማዘጋጀት ነበር፡፡

‹‹ሥራው በጣም አድካሚ ነበር፡፡ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ምሥሎቹን ለሥራ አመቺ በሆነ መልኩ ኢንተርኔት ላይ ቢያስቀምጡ በቀላሉ መሥራት እንችል ነበር፤›› ስትል የተዘጋጁ ምሥሎች ባለመኖራቸው ሥራውን አክብዶባቸው እንደነበር ተናግራለች፡፡ አፕሊኬሽኑን በተለያዩ ደረጃዎች ማለትም ለጀማሪዎችና በብቃት ለመግባባት ለሚችሉ የማዘጋጀት ሐሳብና የሚያግዛቸው አካል ቢያገኙ ለገበያ ለማቅረብ ፍላጐት እንዳላቸው እንግዳወርቅ ተናግራለች፡፡

የውድድሩ ዓላማ አገራዊ ጥቅም ያላቸውን አፕሊኬሽኖች ለማግኘት፣ አቅሙ ያላቸውን የፈጠራ ሰዎች ወደ ገበያው ለማምጣት፣ ለሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች እውቅና መስጠትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ውድድሩን በሦስት ቋሚ ዳኛዎች መዳኘቱን የሚናገሩት አቶ የማነብርሃን ለማ የፈጠራ ውድድሩ ዳኛና አማካሪ፣ ለውድድሩ የተዘጋጁ 17 መስፈርቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ የተሠራው የፈጠራ ሥራ ምን ያህል የማኅበረሰቡን ችግር ይፈታል፣ ምን ያህል አስፈላጊ ነው፣ በተግባር ላይ የመዋል ዕድሉ ምን ያህል ነው የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መስፈርቶች ናቸው፡፡

አቶ የማነብርሃን እንደሚሉት፣ በተወዳዳሪዎች ላይ የተለያዩ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡ አንድን ሶፍትዌር ለመሥራት በቂ ጥናት ማድረግ፣ ምክንያታዊ መሆንና ጊዜና ዋጋ ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች ይህ አልገባቸውም፡፡ በውድድሩ አንዱ ከአንዱ መብለጥ የቻለውም በእውቀት ማነስ ሳይሆን፣ አስፈላጊውን ሥራዎች ባለመሥራታቸው ነው፡፡ ሥራው በሚጠይቀው መሠረት ለመሥራት የሞከሩትም ቢሆኑ ከችግር የፀዱ አይደሉም፡፡ ጥናቱንና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮችን በጋራ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ተባብሮ መሥራት ግድ ነው፡፡ ይሁንና አብሮ መሥራት አልተለመደም፡፡ አብዛኞቹ ለውድድሩ የቀረቡት ሥራዎች በአንድ ሰው ብቻ የተሠሩ ናቸው፡፡

‹‹የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች በሥራ ላይ እንዲውሉ እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም የተለያዩ ዐውደ ርዕዮችን በማዘጋጀትና የኢንዱስትሪ ኔትወርክ በመፍጠር የፈጠራ ሥራዎች ገበያ ላይ እንዲወጡ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው እናደርጋለን፤›› ያሉት አቶ የማነብርሃን፣ በውድድሩ የተሳተፉ አንዳንድ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ ማግኘት መቻላቸውን፣ እንዲሁም ለተቋማት ተሸጠው ተግባር ላይ የዋሉ የፈጠራ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...