ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንዛቤን ለመፍጠር፣ የዓለም ባንክ የሦስቱን አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች በአሜሪካ የሚገኘውን ሑቨር ዳም አስጎበኘ፡፡
በዓለም ባንክ አመቻችነት የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባውን ሑቨር ግድብን እንዲጎበኙ የተደረገበት ዋናው ምክንያት፣ የውኃ አያያዝና አለቃቀቅን በተመለከተ ልምድ እንዲወስዱ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሑቨር ግድብ በኒቫዳ ግዛት በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባ ነው፡፡ ይህ ወንዝ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካና በሰሜን ምዕራብ ሜክሲኮ መካከል 1,450 ማይልስ የተዘረጋ ሲሆን፣ እርጥበት አጠር የሆኑ ስድስት የአሜሪካ ግዛቶችንና ሁለት የሜክሲኮ ግዛቶችን የሚያዳርስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ሁኔታን፣ እንዲሁም የአካባቢያዊና የማኅበራዊ ተፅዕኖዎችን ለማጥናት ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎችን መቅጠር የሚችሉበትን ሁኔታ እያመቻቹ ይገኛሉ፡፡
ጥናቱን ለማስጀመርም የመጨረሻው ጫፍ ላይ እንደሚገኙና ከዚህ አስቀድሞ ግን በጉዳዩ ላይ በመሪዎች ደረጃ በቅርቡ እንደሚመክሩ መዘገባችን ይታወሳል፡፡